Monday, March 9, 2015

ቡራኬ ይቀበሉ!

ዲቮሽን ቁ.180/07፣ ሰኞ፥ የካቲት 30/07 ዓ.ም.
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)

ቡራኬ ይቀበሉ!

በባህር ዳር ባለች ዛፍ ላይ የነበረች ዝንጀሮ፣ ኃይለኛ ማዕበል ያሰቃያት የነበረችውን ዓሣ ትመለከታለች፡፡ ወጀቡ ወደላይ አጉኖ ወደታች ሲያፈርጣት፣ መልሶም ከአንድ ጥግ ወደሌላ ጥግ ሲያሽቀነጥራት ትመለከትናም ታዝንላታለች፡፡ ከሐዘኔታዋም ብዛት ወደማትወድደው ባህር ዘልላ በመግባት ዓሣዋን ይዛት ትወጣለች፡፡ ከዚያም ከባህሩ ዳር ራቅ አድርጋ ደረቅ መሬት ላይ ታስቀምጣታለች፡፡ ከማዕበል ከአደጋው ውስጥ አውጥታት በደረቅ መሬት በማስቀመጥ የረዳቻት መስሏታል!

ነገር ግን በደረቅ መሬት ላይ የተቀመጠችው ዓሣ እንደ እንዝርት ትሽከረከር ጀመር፡፡ የዚያኔ ዝንጀሮዋም ከዓሣዪቷ ጋር አብራ ትጨፍር ጀመር፡፡ ዓሣዋ እንደዚያ የምትሆነው ከማዕበል ከአደጋው ውስጥ መውጣት በመቻሏ ደስ ያላት መስሏታል፡፡ ዓሣዪቱ ለሰከንዶች ትሽከርክራ ትሽከርክራ ስታበቃ ፀጥ ረጭ አለች፡፡ የዚያኔ ዝንጀሮዋ በድጋሚ ደስ አላት፡፡ ዓሣዪቱ ቀደም ሲል በማዕበሉ አሁን ደግሞ በጭፈራው ደክሟት እረፍት ያደረገች መስሏታልና፣ ትታት ደስ እያላት ወደ ዛፏ ወጣች፡፡

ወገኖች ሆይ፣ የሰው ልጅ የውስጥ የአንጀታችንን ስሜት ጠልቆ ሊረዳልን አይችልም፡፡ ይህም በመሆኑ፣ ከሰው የምናገኘው እርዳታ ወይም ድጋፍ የምንፈልገውን ያህል እርካታ ሊሰጠን አይችልም፡፡

ታውቃላችሁ፣ አንዳንዴ እንደ ዝንጀሮዪቱ በዓሣዪቱ ላይ እንዳደረገችው ሁሉ፣ ሰዎች የሚያደርጉልን ድጋፍ ከድጡ ወደ ማጡ የሚጨምረን አጋጣሚም አለ!

ወገኖች ሆይ፣ እውነተኛ እርዳታ የሚመጣው ከላይ ከሰማይ ነው! እውነተኛ በረከት ከላይ ከሰማይ ነው! ጨለማችንን ሊገፍፍ የሚችል እውነተኛ ብርሃን የሚመጣው ከላይ ከሰማይ ነው! ሊረዳን፣ ሊራራልንና፣ ሊደግፈን የሚችል እውነተኛ ረዳት እግዚአብሔር ብቻ ነው!

ወዳጄ ሆይ፣ ዛሬ ቡራኬ የሚቀበሉት ዕለት ነው! በጸሎት መንፈስ ሆነው የሚቀጥለውን ጥቅስ ሲያነብቡ በየመሃሉ ‹‹አሜን›› እያሉ በማንበብ ቡራኬውን ይቀበሉ፡፡

‹‹እግዚአብሔር ይባርክህ፥ ይጠብቅህም፤ እግዚአብሔር ፊቱን ያብራልህ፥ ይራራልህም፣ እግዚአብሔር ፊቱን ወደ አንተ ያንሣ፥ ሰላምንም ይስጥህ (ዘሁ 6፡24-26)።

ወዳጄ ሆይ፣ ቡራኬውን መቀበልዎን ‹‹አሜን›› ብለው ታይፕ በማድረግ ያሳውቁን፡፡ ይህንን ዕለት በማስታወሻዎ ላይም ያስፍሩ! ጌታ ይባርክዎ፡፡

No comments:

Post a Comment