ዲቮሽን ቁ.179/07፣ እሁድ፥ የካቲት 29/07 ዓ.ም.
(በዶ/ር በቀለ ብርሃኑ)
(በዶ/ር በቀለ ብርሃኑ)
ሰማያዊ
ሸክም!
በውስጣችን እውነተኛ የሆነ ከአርያም የተቀበልነው ሸክም ሲኖር አያስተኛንም፤ በፍጹም ዕረፍት አይሰጠንም፡፡ ስለሆነም የመንፈስ መለቀቅ እስኪመጣና እስኪሰማን ድረስ ያስቃትተናል፣ ያስጮኸናል፣ የእግዚአብሔርንም ፊት እንድንፈልግ ያደርገናል፡፡
ታዲያ በመሰጠት፣ በጽኑነት፣
በትጋትና በውሳኔ የሚጸለይ ጸሎት ደግሞ ብዙ ፍሬን ማፍራቱ አይቀሬ ነው፡፡ ይህም ባለፉት ዘመናት በነበሩ ብዙ የእንባ ሰዎች ላይ ታይቷል፡፡
ለምሳሌ ያህል የሒፖው ኦገስቲን(Augustine of Hippo) እናት የሆነችውን
ሞኒካን እንውሰድ፡፡ ኦገስቲን
በዓለማችን በመንፈሳዊ ሕይወቱና ሥራው እጅግ ታዋቂ የሆነ የእግዚአብሔር ሰው ነበር፡፡ ከሞተ በኋላ እንኳ በተወልን ወደር የሌላቸው የጽሑፍ ሥራዎቹ አሁንም ድረስ የሚባርከን ታላቅ የቤተክርስቲያን አባት ነው፡፡
ይሄ ሰው ወደ ዓለም መድረክ ብቅ ከማለቱ በፊትና ዓለም አቀፍ መንፈሳዊ ተጽእኖ ከማምጣቱ በፊት፣ ለልጇ የሕይወት ለውጥ በትጋት ትጸልይ ነበር፡፡ የእርሷ ለረጅም ጊዜ የማያቋርጥ፣ የውሳኔና የእንባ ጸሎት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደ ነበረው ታሪክ ዘክሮታል፡፡
ወደ ጌታ የምናደርገው ከልብ የሆነ ጩኸትና መቃተት እውነተኛ ትሕትናን ያሳያል፡፡ ያለ ምንም ሁኔታ ራስን ለጌታ መስጠትንም ያመለክታል፡፡ ‹‹ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉም›› (ዮሐንስ 15፡5) የሚለውን የጌታ የኢየሱስን ቃል አጥብቆ መረዳትንም ይጠቁማል፡፡ ንጉሥ ዳዊት እንዲህ በመሰለ እውነተኛ ትሕትና ከልብ የሆነ ጩኸትና መቃተት ወደ ጌታ ያቀርብ ነበር፡፡
ለዚህም ነው መዝሙረኛው በእውነትና
በመንፈስ የተጸለየ ጸሎት ከጣሪያ እንደሚያልፍ፣ ደግሞም ውጤትና ፍሬ እንዳለው ‹‹በጨነቀኝ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፣ ወደ አምላኬ ጮኽሁ፣ ከመቅደሱ ቃሌን ሰማኝ፤ ጩኸቴም ወደ ጆሮው ገባ›› (መዝሙር 18፡6) በማለት የመሰከረው፡፡
አዎ! እንደ ንጉሥ ዳዊት እውነተኛ ሸክም ያላቸው፣ በዙሪያቸው በሚያዩት አሳዛኝ ነገር ግድ የሚላቸው፣ ራእይን ያረገዙ፣ ላሉበት ትውልድ ውስጥ የሕይወት ጉዞ የሚያስቡና ለቤተ ክርስትያን ዕድገት የሚጨነቁ ሰዎች እንቅልፍ አይኖራቸውም፡፡
እንደ ንጉሥ ዳዊት እውነተኛ ሸክም ያላቸው፣ ይማልዳሉ፣ ይቃትታሉ፣ ይጮኻሉ፣ ያለቅሳሉ፣
በመንፈስ ኃይል ወደ እግዚአብሔር ማደሪያ ይገሠግሣሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት የተሰጡ ሰዎች ሲበዙ፣ ቤተ ክርስቲያን በፍሬ እንደምትሸፈን ምን ጥርጥር አለው?
ከየትኛውም ዘመን ይልቅ የጌታ ጉልበት በጸሎት ሊያዝበት የሚገባው ዘመን መቼ ነው ካላችሁኝ፣ ይህ የአሁኑ ዘመን ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ሁኔታው እጅግ እየጨላለመ ነውና ነው፡፡
ይህም ብቻ አይደም፣ ሰይጣንም
በታላቅ ቁጣ ምድሪቷን ሊያተራምስ እንደ ወጣ ግልጽ እየሆነ መጥቷልና ነው፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ ብዙ ቅጥሮች ፈርሰዋል፡፡ ብዙ አሳዛኝ ነገሮችን በየእለት ኑሯችን ማየታችን እጅግ እየተለመደ ነው፡፡
ታዲያ በዚህ ሰዓት እግዚአብሔር ከአማኞች ምን ይፈልጋል የተባለ እንደ ሆነ፣ የፈራረሱ ቅጥሮችን በመንፈስ ዐይተው፣ አያሌ ቀን የሚያዝኑ፣ በሰማይ አምላክ ፊት የሚጾሙና የሚጸልዩ (ነህምያ 1፡4) ሰዎችን እንደሚፈልግ ምንም አያጠያይቅም፡፡ ጌታ ከክርስቲያኖች ተግባራዊ ርምጃዎችን ይፈልጋል፡፡ በልቅሶና በምጥ በእርሱ ፊት ወድቀው በመቃተት፣ በተግባር ለሥራ የሚነሡ ሰዎችን ይፈልጋል፡፡
ለሕዝቡ የሚገደው ጌታ (በኢሳ 62፡6-7) ላይ፣ ‹‹ኢየሩሳሌም ሆይ፣ ጕበኞችን በቅጥርሽ ላይ አቁሜአለሁ፤ ቀንና ሌሊት ከቶ ዝም አይሉም፤ እናንተ እግዚአብሔርን የምታሳስቡ፣ ኢየሩሳሌምን እስኪያጸና በምድርም ላይ ምስጋና እስኪያደርጋት ድረስ አትረፉ ለእርሱም ዕረፍት አትስጡ›› ብሏልና።
አዎ! ጌታ እግዚአብሔር ለቤተ ክርስትያን ትክክለኛ ጉዞ፣ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ተጽእኖ፣ ቀንና ሌሊት ዝም የማይሉ ትጉሕ ጉበኞችን ይፈልጋል፡፡ በረድኤቱ ታምነው የሚጠሩት፣ የሚጮኹ፣ የሚቃትቱ፣ ያለ መታከትና ያለ መሰልቸት ፊቱን የሚፈልጉ የተሰጡ ሰዎችን ይሻል፡፡
ጌታ በመዝ 50፡15 ‹‹በመከራ ቀን ጥራኝ፣ አድንህማለሁ፣ አንተም ታከብረኛለህ›› የሚል የከበረ የተስፋ ቃል የሰጠንም ለዚህ ነው፡፡ ስለዚህ ታማኝ የሆነው ጌታ እስኪጐበኘንና ቤተ ክርስትያንን ምስጋና እስኪያደርጋት ድረስ ሸክሞቻችንን ይዘን በፊቱ እንውደቅ! ጌታ ይባርካችሁ!
--------------------------------
(ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፣ ጌታ
ይባርክዎ!)
(1) ኤግል የሬዲዮ አገልግሎት በአማርኛ ቋንቋ
መጀመሬን በደስታ አሳውቃለሁ፡፡ በየትኛውም ዓለም የሚገኙ አማርኛ አድማጮች
http://zenoradio.com/en/listeners/ET/Eagle+Amharic+Radio/
በመጫን ሊያዳምጡ ይችላሉ፡፡ አሜሪካና ካናዳ የሚኖሩ በነጻ ስልክ (605) 562 4274 ማዳመጥ ይችላሉ፡፡
(2) ዲቮሽኖቹን በብሎግ ለመከታተል የሚከተለውን ሊንክ ይጫኑ፡፡
https://draft.blogger.com/blogger.g?blogID=7832170107481561272#allposts
(3) ዲቮሽኖቹን በፌስቡክ ለመከታተል የሚከተለውን ሊንክ ይጫኑ፡፡ https://www.facebook.com/tesfahun.hatia
No comments:
Post a Comment