Saturday, March 7, 2015

ኑ፥ በእግዚአብሔር ብርሃን እንሂድ!

ዲቮሽን .178/07፣ ቅዳሜ የካቲት 28/07 ..
(
በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)


ኑ፥ በእግዚአብሔር ብርሃን እንሂድ!

ሕግ ከጽዮን የእግዚአብሔርም ቃል ከኢየሩሳሌም ይወጣልና … ኑ፥ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፥ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፡ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፥ በጎዳናውም እንሄዳለን … እናንተ የያዕቆብ ቤት ሆይ፥ ኑ፥ በእግዚአብሔር ብርሃን እንሂድ (ኢሳ 2፡3-5)።

ወዳጆች ሆይ፣ ‹‹ክርስቲያን›› ተብለው ከሚጠሩ ሰዎች መካከል አንዳንዶች የጨለማ ሥራ ሲሰሩ፣ ሲቅበዘበዙ፣ ሲደናገሩና ግራ ሲጋቡ እናያለን፡፡ አንዱ በሌላው ላይ ሰይፍ ሲመዝዝ፣ ጦር ሲሰብቅና ጦር ሲወረውር፣ ሰልፍ ሲያነሣና ሰልፍ ሲያዘምት እናያለን፡፡ ወዳጆች ሆይ፣ ይህ ለምን ይመስላችኋል?

ታውቃላችሁ፣ ‹‹ክርስቲያን›› ተብለው ከሚጠሩ ሰዎች መካከል አንዳንዶች የጨለማ ሥራ ሲሰሩ፣ ሲቅበዘበዙ፣ አንዱ በሌላው ላይ ሰልፍ ሲያስነሱ የምናየው የእግዚአብሔር ብርሃን ስላልበራላቸው ነው!

ወዳጆች ሆይ፣ ‹‹ክርስቲያን›› ከሚጠሩ ሰዎች መካከል አንዳንዶች የእግዚአብሔር ብርሃን የማይበራላቸው ለምንድነው?

ታውቃላችሁ፣ ‹‹ክርስቲያን›› ተብለው እየተጠሩ ነገር ግን የእግዚአብሔር ብርሃን የማይበራላቸው ሰዎች፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስለማይሰሙ፣ ወደ እግዚአብሔር ማደሪያ ስለማይገቡ፣ በመንገዱም ስለማይሄዱ ነው!

ታውቃላችሁ፣ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር ቤት ሲገቡ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ይሰማሉ! የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰሙ ክፉና ደጉን ይለያሉ! በጸሎት ወደ ማደሪያው የሚገቡ እግዚአብሔርን ያያሉ! እግዚአብሔርን የሚያዩ ደግሞ ራሳቸውን ያዋርዳሉ! ራሳቸውን የሚያዋርዱ የእግዚአብሔርን መንገድ ያውቃሉ!

ታውቃላችሁ፣ የእግዚአብሔርን መንገድ የሚያውቁ በእግዚአብሔር ብርሃን ይሄዳሉ! በብርሃኑ የሚሄዱ ደግሞ ሰይፋቸውን ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ!

ታውቃላችሁ፣ በብርሃኑ የሚሄዱ አንዱ በሌላው ላይ ሰይፍ መምዘዛቸውን፣ ሰልፍ ማስነሳታቸውን እርግፍ አድርገው ያቆማሉ!

ወዳጆች ሆይ፣ ወደ እግዚአብሔር ቤት በመምጣትና መንገዱን በመማር/በማወቅ በእግዚአብሔር ብርሃን መሄድ እንችላለን? ስለሆነም፣ እናንተ እግዚአብሔር ሰዎች ሆይ፥ ኑ፥ በእግዚአብሔር ብርሃን እንሂድ።
--------------------------------
(ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፣ ጌታ ይባርክዎ!) 

(1) ኤግል የሬዲዮ አገልግሎት በአማርኛ ቋንቋ መጀመሬን በደስታ አሳውቃለሁ፡፡ በየትኛውም ዓለም የሚገኙ አማርኛ አድማጮች http://zenoradio.com/en/listeners/ET/Eagle+Amharic+Radio/ በመጫን ሊያዳምጡ ይችላሉ፡፡ አሜሪካና ካናዳ የሚኖሩ በነጻ ስልክ (605) 562 4274 ማዳመጥ ይችላሉ፡፡

(2) ዲቮሽኖቹን በብሎግ ለመከታተል የሚከተለውን ሊንክ ይጫኑ፡፡ https://draft.blogger.com/blogger.g?blogID=7832170107481561272#allposts


(3) ዲቮሽኖቹን በፌስቡክ ለመከታተል የሚከተለውን ሊንክ ይጫኑ፡፡ https://www.facebook.com/tesfahun.hatia

No comments:

Post a Comment