Wednesday, March 11, 2015

የእግዚአብሔር ቱንቢ!

ዲቮሽን .182/07፣ ረቡዕ የካቲት 2/07 ..
(
በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)

የእግዚአብሔር ቱንቢ!

እንዲህም አሳየኝ እነሆም፥ ጌታ ቱንቢውን ይዞ በቱንቢ በተሠራ ቅጥር ላይ ቆሞ ነበር። እግዚአብሔርም፦ አሞጽ ሆይ፥ የምታየው ምንድር ነው? አለኝ። እኔም። ቱንቢ ነው አልሁ። ጌታም፦ እነሆ፥ በሕዝቤ በእስራኤል መካከል ቱንቢ አደርጋለሁ ከእንግዲህም ወዲህ ደግሞ አላልፋቸውም (አሞጽ 7፡7-8)።

ወገኖች ሆይ፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃን የተጠራ ሕዝብ ነው! ሕዝቡ የእርሱን በጎነት እንዲናገር የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ነው! ሕዝቡ በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰለ እንዲኖር የተጠራ ሕዝብ ነው!

ወገኖች ሆይ፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ መውጊያ ሰይፉ እየያዘ፣ በቃሉ መስተዋት ራሱን እየተመለከተ፣ በቃሉ ብርሃን ዙሪያውን እያበራ እንዲመላለስ የተጠራ ሕዝብ ነው!

ወገኖች ሆይ፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ ቃሉን እንደ ጫማ፣ እንደ ራሱ ቁር፣ የደረቱ ጥሩር፣ የአንገቱ ድሪ፣ ቃሉን ቃል ኪዳኑ፣ ቃሉን ቃለ መሐላው፣ የቤቱ ምሰሶ፣ ጣራና ግድግዳው እንዲያደርግ የተጠራ ሕዝብ ነው!

ወገኖች ሆይ፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ሕገ መንግሥት፣ እንደ ደንብ መመሪያው፣ ከአፉ እንዳይለየው፣ የተጻፈውን ሁሉ ይጠብቅ ዘንድና ደግሞም እንዲያደርገው በቀንና ሌሊት እንዲያሰላስለው የተጠራ ሕዝብ ነው!

ወገኖች ሆይ፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ የእግዚአብሔርን ቃል በልቡ እንዲይዝ፣ በእጆቹ እንዲያስር፣ ለልጆቹ እንዲያስተምር፣ ለሰው እንዲመሰክር፣ በቤቱ ሲቀመጥ፣ በመንገድም ሲሄድ፣ ሲተኛ ሲነሣ ሁሌ እንዲጫወተው፣ የእጆቹ ምልክት፣ የአይኖቹ ክታብ፣ በቤቱ መቃኖች፣ በደጃፉ በሮች፣ በጣራ ግድግዳው ጽሁፍ እንዲሆነው የተጠራ ሕዝብ ነው!

ወገኖች ሆይ፣ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በእጁ ቱንቢ ይዞ የሕዝቡን መንፈሳዊ ሕይወት ሊለካ ይመጣል! የሠራዊት ጌታ የተጠራ ሕዝቡ ቃሉን እንዴት እንደያዘ፣ በቃሉ መሠረት በምን ዓይነት መንገድ እንደተመላለሰ በቱንቢው ይለካል!

ወገኖች ሆይ፣ የሕዝቡ መንፈሳዊ ሕይወት፣ የት ቦታ ላይ ስህተት፣ የትኛው ጋ ክፍተት እንዳለበት በቱንቢው ይለካል! የእግዚአብሔር ቱንቢ ከእግዚአብሔር ጋራ ያለ ግንኙነታችንን፣ ለቃሉ ያለንን ታዛዥነታችንን፣ ከወገኖች ጋራ ያለ ኅብረታችንን፣ የመንፈሳዊ ዕድገት ቀጥተኝነታችንን፣ ወርድና ስፋቱን፣ ከፍታ ጥልቀቱን ይገመግመዋል!

ወገኖች ሆይ፣ እነሆ፥ እግዚአብሔር በሕዝቡ መካከል ቱንቢውን ያደርጋል! ከተሰጠን ድንበር፣ ከተፈቀደልን መስመር መግባት መውጣታችን፣ መወላገዳችን፣ መንገራገጫችን፣ መወናበዳችን፣ ወለም ዘለማችን ሁሉ ይፈተሻል፡፡

ቱንቢ ሆይ !

እንዴት ነው – ነገሬ?
ምሰሶ – ማገሬ?
ወርድና – ስፋቴ?
ጎንና – ቁመቴ?
ከፍታ – ጥልቀቴ?
የቱ ላይ ነው – ስህተቴ?
--------------------------------
(ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፣ ጌታ ይባርክዎ!) 

No comments:

Post a Comment