Tuesday, March 24, 2015

ኢትዮጵያን – እንገንባ!

ዲቮሽን .195/07፣ ማክሰኞ መጋቢት 15/07 ..
(
በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)

ኢትዮጵያን እንገን!

…እኛ ያለንበትን ጕስቍልና ኢየሩሳሌም እንደ ፈረሰች፥ በሮችዋም በእሳት እንደ ተቃጠሉ ታያላችሁ አሁንም ከእንግዲህ ወዲህ መሳለቂያ እንዳንሆን ኑና የኢየሩሳሌምን ቅጥር እንሥራ … (ነህ 2፡17)።


በቅድሚያ የማንኛውም ፖለቲካ ፓርቲ አባል አለመሆኔ– ሆኜም አለማወቄ፣ ነገር ግን በሀገር ግንባታ፣ በሰላምና መልካም አስተዳደር ላይ ነጻ የሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተያየት ከመስጠት እንደማልታቀብ ይታወቅልኝ፤ አመሰግናለሁ! 


ወገኖች ሆይ፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ ለብዙ ዓመታት መታወቂያዋ ኋላቀርነት፣ ድህነትና ጦርነት ሆኖ ቆይቷል፡፡ በዚህም መላው ዓለም ሲሳለቅብን ኖረናል፡፡ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ የሚሰደዱ ዜጎቻችን በሚሄዱባቸው ሀገሮች ሁሉ ተገቢ ክብር አይሰጣቸውም! 


ታውቃላችሁ፣ የሀገራችን የኢትዮጵያ ውድቀትና ትንሣኤ፣ ውርደትና ክብር የሚወሰነው በእኛ በክርስቲያኖቹ ነው! የእኛ መንፈሳዊ ተፅዕኖ በሁሉም የሀገሪቱ ጉዳዮች ላይ ሊንጸባረቅ ይችላል፡፡


ታውቃላችሁ፣ የሕዝባችን ዕድገትም ሆነ ውድቀት፣ የምድራችን በረከትም ሆነ መርገም፣ የዜጎቻችን ድህነትም ሆነ ብልጽግና የሚወሰነው በምድራችን ላይ ባለች ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ተጽዕኖ ነው! 


ወገኖች ሆይ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ አማኞች ሁሉ ሥልጣን ሁሉ ከላይ እንደሚገኝ፣ የፖለቲካ ባለሥልጣናት የሚሾሙት ከእግዚአብሔር እንደሆነ እናምናለን! ባለ ሥልጣንን የሚቃወም የእግዚአብሔርን ሥርዓት እንደሚቃወም፣ የሚቃወሙትም በራሳቸው ላይ ፍርድን እንደሚቀበሉም እናውቃለን፡፡ ገዥዎች ለክፉ አድራጊዎች እንጂ መልካም ለሚያደርጉ የሚያስፈሩ አይደሉምና …መልካሙን ብናደርግ ምስጋና እንደሚሆንልን እናምናለን (ሮሜ 13፡1-3)።


ወገኖች ሆይ፣ ነህሚያን አስቡ! የሕዝቡን ጕስቍልና፣ የምድሩንም መፍረስ ዜና ሲሰማ ‹‹ምን አገባኝ፣ አይመለከተኝም›› ብሎ አልተቀመጠም፡፡ ይልቁንም፣ ለወገኖቹ ሁሉ ‹‹ከእንግዲህ ወዲህ መሳለቂያ እንዳንሆን ኑና የኢየሩሳሌምን ቅጥር እንሥራ›› በማለት የሀገር ግንባታ ጥሪ ሲያስተላልፍ እናስተውላለን!


ታውቃላችሁ፣ የቤተክርስቲያን ክብር የአካሉ ግንባታ እንደሆነው ሁሉ፣ የዜግነት ክብር የሀገር ግንባታ ነው! አካል ሲገነባ የክርስቶስ ሙላት እንደሚፈስስ ሁሉ፣ ሀገር ሲገነባ በሕዝባችን ኑሮ ላይ መሻሻል ይመጣል! ስለሆነም በየሀገሩ ያለን ኢትዮጵያን ለሀገራችን ግንባታ መንቀሳቀስ ይገባል፡፡


ታውቃላችሁ፣ ዛሬ ለኑሮ ምቹ የሆኑት አውሮፓና አሜሪካ የተገነቡት በቤተክርስቲያን ሰዎች ነው! እነዚህን ሀገሮች ለኑሮ የተመቹት ሀገር ወዳድ ዜጎቻቸው ስለገነቧቸው ነው! 


ወገኖች ሆይ፣ በእነዚህ ሀገሮች የሚኖሩትን የእኛን ዜጎች፣ በተለይም የፖለቲካ አጀንዳ አንግበው የሚንቀሳቀሱትን እስኪ አስቧቸው! ንግግራቸውን፣ መፈክራቸውን፣ ዜና ዘገባቸውን እስኪ በደንብ ስሙ! ምንድነው ቋንቋቸው? ምንድነው ሥራቸው? 


ወገኖች ሆይ፣ ለሀገራችን ያለን ፍቅር ሊገለጽ የሚችለው በወሬ ግንባታ ሳይሆን በሀገር ግንባታ፣ በሰላም ግንባታ፣ በመልካም አስተዳደር ግንባታ ነው! ሰላምና ልማት ለሀገራችን ዕድገት ወሳኝ ሚና አለው! ሰላም ከሌለ ልማት የለም፡፡ ሰላም የሌለበት የአምልኮ ነጻነት የለም፡፡ የአምልኮ ነጻነት የሌለበት የቤተክርስቲያን ተቋማት ሊቢሩ አይችሉም ወይንም ይፈራርሳሉ፡፡


ወገኖች ሆይ፣  ሰላም ከሌለ ሀገርም ይፈርሳል፡፡ ሀገር ከፈረሰ የዜግነት ክብር ሕግና መንግሥቱ አብረውት ይፈርሳል፡፡ ሀገር የፈረሰ እንደሁ የዓለም መሳቂያና መሳለቂያ ይሆናል፡፡ እዚህ ላይ ነው ጥበብ ከእዚህ ላይ ነው መማር!


ወገኖች ሆይ፣ የፖለቲካ ልዩነቶቻችንን ወደ ጎን ትተን፣ የግራና ቀኙን ክንፎቻችን ወደ ጎን ትተን፣ ያልተሟሉና የጎደሉ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎቻችንን ወደ ጎን ትተን፣ ከእንግዲህ ወዲህ የሌሎች መሳቂያ መሳለቂያ እንዳንሆን ኑና ኢትዮጵያን እንገንባ! 


ወገኖች ሆይ፣ በየቤተክርስቲያኖቻችን ያለ መከፋፈላችንን ትተን፣ በየብሔሩና በየቋንቋዎቻችን ያለ ጥላቻችንን ትተን፣ የየሹመቱና የየሥልጣኖቻችንን ሽኩቻዎች ትተን፣ በየችሎቶቹ የተደራረቡ ክሶቻችንን ትተን፣ በእኛም ምክንያት በአሕዛብ አንደበት የእግዚአብሔርን ስም ማሰደባችንን ትተን፣ የሌሎች መሳቂያ መሳለቂያ እንዳንሆን ኑና ኢትዮጵያን እንገንባ!


--------------------------------
(ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፣ ጌታ ይባርክዎ!)

No comments:

Post a Comment