ዲቮሽን ቁ.175/07፣ ረቡዕ፥ የካቲት 25/07 ዓ.ም.
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
በነፍስ መወራረድ!
ናቡከደነፆርም። ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም ሆይ፥ አምላኬን አለማምለካችሁ፥
ላቆምሁትም ለወርቁ ምስል አለመስገዳችሁ እውነት ነውን? (ዳን 3፡14)
እግዚአብሔርን ብቻ ማምለክ፣ ለእርሱ ብቻ መስገድ የሕይወት ወይም
ሞት ውሳኔ የሚጠይቅ ምርጫ ነው! ተጽፏልና፣ አምላካችንን እግዚአብሔርን በፍጹምም ልባችን እንወድደው ዘንድ፣ በፍጹምም ነፍሳችን እናመልከው
ዘንድ ይገባል፡፡ እንዲህ ዓይነት መውደድ፣ እንዲህ ያለ ማምለክ የሕይወት ወይም የሞት ውሳኔ ይጠይቃል!
ወገኖች ሆይ፣ የእምነት ምርጫ ፈተና የሚመጣው ዘወትር ከአቅም
በላይ በሆነ መንገድ ነው! ጌታን ማምለክ ወይም ሌላ አምላክ ማምለክ፣ እንዲሁም ለእርሱ መስገድ ወይም ለሌላ አምላክ መስገድ፣ በሕይወትና
በሞት መካከል የሚደረግ ምርጫ ነው!
ወገኖች ሆይ፣ አንዳንዴ ከአቅማችን በላይ የሆነ የአምልኮና ስግደት
ፈተና ይመጣብናል፡፡ የምናመልከውን ትተን ሌላ አምላክ እንድናመልክ፣ የምንሰግድለትን ትተን ለሌላ እንድንሰግድ የሚያስገድድ ፈተና፣
ከአቅም በላይ በሆነ ሁኔታ ሊመጣብን ይችላል፡፡
ታውቃላችሁ፣ እግዚአብሔርን ማምለክ፣ ለእርሱ ብቻ መስገድ መስዋዕትነት
ይጠይቃል!
ታውቃላችሁ፣ እግዚአብሔርን ማምለክ ወይም ሌላ አምላክ ማምለክ፣
ለእግዚአብሔር ብቻ መስገድ ወይም ለሌላ አምላክ መስገድ፣ በሕይወትና ሞት መካከል የሚደረግ ምርጫ ነው!
ወገኖች ሆይ፣ ጌታን ለመከተል መወሰን በሕይወትና ሞት መካከል
የሚደረግ ምርጫ ነው! ጌታን ለመከተል መወሰን በመኖርና ባለመኖር፣ በማግኘትና በማጣት፣ በትርፍና በጉዳት መካከል የሚደረግ ምርጫ
ነው!
ወገኖች ሆይ፣ ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎን አስቡ! ንጉሡ ናቡከደነፆር
አምላኩ እንዲሆነው ላሠራውና በባቢሎንም ላቆመው የወርቁ ምስል ሰዎች እንዲያመልኩትና እንዲሰግዱለት፣ ይህን የማያደርግ በእሳት እቶን
ውስጥ እንዲጣል ማስጠንቀቂያ ተሰጠ፡፡
ወገኖች ሆይ፣ በአዋጁ መሠረት መኳንንቱና ሹማምቶቹ፥ አዛዦቹና
አዛውንቶቹ፥ በጅሮንዶቹና አማካሪዎቹ፥ መጋቢዎቹና አውራጃ ገዦቹ ሁሉ፣ ሰዎች ሁሉ ናቡከደነፆር ላቆመው ለወርቅ ምስል ሰገዱ። ሦስቱ
ወጣቶች ግን ወድቀው አልሰገዱም!
ወገኖች ሆይ፣ ለሌሎች አማልክት አለመስገድ ዋጋ ያስከፍላልና፣
ወጣቶቹ ተያዙ፣ ወድቀው እንዲሰግዱ አሊያም በእቶኑ እሳት ውስጥ እንደሚጣሉ ተጠየቁ፡፡ ወጣቶቹ ግን፣ ከአምላካቸው በቀር ማንንም
አምላክ እንዳያመልኩ ለእርሱም እንዳይሰግዱ ሰውነታቸውን ለእቶን እሳት አሳልፈው ሰጡ!
ታውቃላችሁ፣ የሚያመልኩት አምላክ እንደሚያድናቸው አምነዋልና፣
ባያድናቸውም ለሌላ አምላክ ወድቆ ከመስገድ ተቃጥሎ መሞትን መርጠዋልና፣ የሚሰግዱለት ጌታ መልአኩን ልኮ ከእቶኑ እሳት ምንም ሳይጎዱ
አወጣቸው!
ታውቃላችሁ፣ ‹‹በሚነድድ እሳት እቶን
ውስጥ ትጣላላችሁ፣ ከእጄ የሚያድናችሁ አምላክ ማነው?››
ብሎ የፎከረው ንጉሥ በወጣቶቹ መዳን እጅግ ተደነቀ፡፡ እንዲህም ተናገረ፣ ‹‹መልአኩን የላከ፥ ከአምላካቸውም በቀር ማንንም አምላክ
እንዳያመልኩ ለእርሱም እንዳይሰግዱ ሰውነታቸውን አሳልፈው የሰጡትን የንጉሡንም ቃል የተላለፉትን በእርሱ የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ፥
የሲድራቅና የሚሳቅ የአብደናጎም አምላክ ይባረክ (ዳን 3፡28)።
ወገኖች ሆይ፣ ንጉሡ ይህንንም አለ፣ ‹‹እኔም እንደዚህ የሚያድን
ሌላ አምላክ የለምና በሲድራቅና በሚሳቅ በአብደናጎም አምላክ ላይ የስድብን ነገር የሚናገር ወገንና ሕዝብ በልዩ ልዩም ቋንቋ የሚናገሩ
ይቈረጣሉ፥ ቤቶቻቸውም የጕድፍ መጣያ ይደረጋሉ ብዬ አዝዣለሁ›› አለ።
ታውቃላችሁ፣ አምላካችንን እግዚአብሔርን በፍጹምም ልባችን የምንወድደው
ከሆነ፣ በፍጹምም ነፍሳችን የምናመልከው ከሆነ፣ ጌታ በእኛ ሕይወት ተአምራት ያደርጋል፡፡ በዚህ ተአምራት አሕዝብ ይደነቃል፣ ለእግዚአብሔር
ክብር፣ ምስጋናንን ያመጣል፡፡
ወገኖች ሆይ፣ አምልኳችን ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር ፍርሃት እያመጣ
ነውን? የእኛ አካሄድ፣ የእኛ አገልግሎት አሕዛብ አምላካችንን እንዲያዩ እያስቻለ ነውን? በምስክርነታችን አሕዛብ እግዚአብሔርን
እንዲያዩ በነፍሳችን እየተወራረድን፣ ሰዎች እንዲድኑ ዋጋ እየከፈልን ነውን?
--------------------------------
(ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ
ያድርጉ፣ ጌታ ይባርክዎ!)
Eagle Amharic Radio 24/7 አማርኛ ቋንቋ መጀመሬን በደስታ አሳውቃለሁ፡፡ በየትኛውም ዓለም የሚገኙ አማርኛ አድማጮችhttp://zenoradio.com/en/listeners/ET/Eagle+Amharic+Radio/ በመጫን ሊያዳምጡ ይችላሉ፡፡ አሜሪካና ካናዳ የሚኖሩ በነጻ ስልክ (605) 562 4274 ማዳመጥ ይችላሉ፡፡
Eagle Amharic Radio 24/7 አማርኛ ቋንቋ መጀመሬን በደስታ አሳውቃለሁ፡፡ በየትኛውም ዓለም የሚገኙ አማርኛ አድማጮችhttp://zenoradio.com/en/listeners/ET/Eagle+Amharic+Radio/ በመጫን ሊያዳምጡ ይችላሉ፡፡ አሜሪካና ካናዳ የሚኖሩ በነጻ ስልክ (605) 562 4274 ማዳመጥ ይችላሉ፡፡
ዲቮሽኖቹን በብሎግ ለመከታተል የሚከተለውን ሊንክ ይጫኑ https://draft.blogger.com/blogger.g?blogID=7832170107481561272#allposts
ዲቮሽኖቹን በፌስቡክ ለመከታተል የሚከተለውን ሊንክ ይጫኑ https://www.facebook.com/tesfahun.hatia
No comments:
Post a Comment