ዲቮሽን ቁ.174/07፣ ማክሰኞ፥ የካቲት 24/07 ዓ.ም.
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
ታሪክ እንዲያወሳዎ!
በዚያም ሌሊት እንቅልፍ ከንጉሡ ሸሸ የዘመኑንም ታሪክ መጽሐፍ
ያመጡ ዘንድ አዘዘ፥ በንጉሡም ፊት ተነበበ። ደጁንም ከሚጠብቁት ከንጉሡ ጃንደረቦች ሁለቱ ገበታና ታራ እጃቸውን በንጉሡ በአርጤክስስ
ላይ ያነሡ ዘንድ እንደ ፈለጉ፥ መርዶክዮስ እንደ ነገረው ተጽፎ ተገኘ (አስቴር 6፡1-2)።
ወዳጄ ሆይ፣ እየሠሩት ያሉት ነገር ታሪክ የሚያስበው፣ ትውልድ
የሚያስታውሰው ነውን? እያከናወኑት ያለው ሥራ ለሌሎች የሚተርፍ፣
የሚፈለግና የሚወደስ ነውን? የሚሠሩት ሥራ ከራስዎ ምህዋር፣ ከግል ጥቅምዎ አልፎ ለቀጣይ ዘመናት ምሣሌ የሚሆን የሚታወስ ነውን?
ወዳጄ ሆይ፣ ለቀጣዩ ትውልድ የእርስዎን ‹ሌጋሲ› እየተዉ ነውን?
ሲታሰብ የሚኖር፣ የእጅዎትን አሻራ እየተዉ ነውን?
ወዳጄ ሆይ፣ መርዶክዮስን ያስቡ! በምድብ ሥራው ላይ ፍጹም ታማኝነት
በማሳየቱ ምክንያት፣ ታላቅ ጀብደኝነት ሊያስመዘግብ ቻለ! በጥበቃ ሥራ የተሰጠውን ድርሻ በከፍተኛ ትጋት በማከናወኑ ታሪክ አስመዘገበ፡፡
ታውቃላችሁ፣ መርዶክዮስን የተሰጠውን ሥራ በትጋት ባይፈጽም፣
ሥራውን ለእንጀራ ብቻ ቢያከናውን ኖሮ ንጉሡን ለመግደል የተቃጣውን ሴራ ባላከሸፈም ነበር፡፡
ታውቃላችሁ፣ በተሰጠን በማናቸውም ሥራ ታሪክ ለማስመዝገብ በደንብ
እንችላለን፡፡ በመደበኛው ሥራ ላይ ትጋት በመጨመር፣ በትጋታችን ላይ ታማኝነት በመደመር ታሪክ ለማስመዝገብ እንችላለን፡፡
ወገኖች ሆይ፣ ተግተን እየሠራን፣ እየለፋንና ሥራችንን በታማኝነት
እየተወጣን ወዲያው የሚታይና የሚለካ ውጤት አናገኝ ይሆናል! ቢሆንም፣ ታሪክ እንደሚያስታውሰን መርሳት አይገባም፡፡ በመልካም ሥራችን
እንግፋበት እንጂ፣ ጊዜው ሲደርስ፣ የሠራነው ሥራ አፍ አውጥቶ ሊጮኽ፣ ሊመሰክርና ሊናገር ይችላል!
ወገኖች ሆይ፣ መርዶክዮስን አስቡ! የተሰጠውን ሥራ በትጋት ፈጸመ፡፡
በሥራ ገበታው ታማኝነትና አስደናቂ ውጤት ሊያስመዘግብ ቻለ! ነገር ግን ይህንን አድርጎ የተሻለ ደመወዝ አልተከፈለውም! ከነበረው
የጥበቃ ሥራ አልተነቃነቀም! ከንጉሡን ሞት ታድጎ፣ ሹመትና ሽልማት ሊሰጠው ሲገባ ምንም አላገኘም!
ታውቃላችሁ፣ መልካም ሥራ ሁሉ በታሪክ ይታወሳልና መርዶክዮስን
ታሪክ አስታወሰው! የመርዶክዮስ ሌጋሲ፣ የሥራ ትጋቱና ታማኝነቱ በታሪክ ታወሰ! ታሪክ ሲያስታውስ ሹመት ሽልማቱ ይከተላልና ዘበኛው
መርዶክዮስ ባልጠበቀው ጊዜ በማዕረግ ተሾመ!
ወገኖች ሆይ፣ ንጉሡ ሊያከብረው ለሚወድደው ሰው እንዲደረግ ሁሉ
ለዘበኛው ሰውዬ እንዲደረግለት አዋጅ ተነገረ! በበር አጥር ሥር በጥበቃ ሥራ የተሰማራው ሰውዬ በንጉሥ ፈረስ ላይ ተቀምጦ በከተማው
አደባባይ ዞረ፡፡
ወዳጄ ሆይ፣ የዕለት ሥራዎን እንዴት እያከናወኑ ነው? በሚሠሩት
ሥራ እያሳዩት ያለው ትጋት ምን ያህል አጥጋቢ ነው? በምንም ዓይነት ቦታ፣ ምንም ዓይነት ሥራ ይሥሩ ነገር ግን ሥራዎን በታማኝነትና
በትጋት ከመወጣት አንጻር እንዴት እየያዙ ነው?
ወዳጄ ሆይ፣ መርዶክዮስን ያስቡ! በሥራ ገበታው በነበረው ትጋት
ታሪክ አስመዝግቧል! ይህን በመሆኑ ታሪክ አስታወሰው! እርስዎስ ወዳጄ ሆይ፣ ታሪክ የሚያወሳው ምን እየሠሩ ነው?
--------------------------------
(ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ
ያድርጉ፣ ጌታ ይባርክዎ!)
No comments:
Post a Comment