Monday, March 2, 2015

የመክሊት መካነመቃብር!

ዲቮሽን .173/07፣ ሰኞ የካቲት 23/07 ..
(
በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)


የመክሊት መካነመቃብር!

አምስት መክሊትም የተቀበለው ሄዶ ነገደበት ሌላም አምስት አተረፈ፤ እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ። አንድ የተቀበለው ግን ሄዶ ምድርን ቈፈረና የጌታውን ገንዘብ ቀበረ(ማቴ 25፡16-18)።

እያንዳንዱ አማኝ፣ እንደየ ዓቅሙ፥ ከጌታ የተሰጠው መክሊት አለው! ጌታ እያንዳንዱ አማኝ፣ እንደየ ዓቅሙ፥ መክሊት የሚሰጠው እያንዳንዱ አማኝ እንደየመክሊቱ እንዲያገለግልበት ነው!

ታውቃላችሁ፣ በሁኔታና ቦታ ሳይገደቡ፣ በተሰጣቸው መክሊት የሚያገለግሉ ጥቂት አማኞች ሲኖሩ፣ በሁኔታዎች አለመመቸትና በሚታየው ነገር አለመደሰት የተነሣ መክሊታቸውን የቀበሩ ብዙ አማኞች አሉ፡፡ በእነዚህ የመክሊት ቀባሪዎች  የተቀበሩ ብዙ የመክሊት መካነመቃብሮች በየቦታው አሉ!

ታውቃላችሁ፣ የመክሊቱ ጌታ መክሊት ተቀባዮቹን ይቆጣጠራልና፣ በጥቂቱ ታምነው፥ በመክሊታቸው ሠርተው ያተረፉ አማኞች በብዙ ይሾማሉ፣ ብዙ ደስታና ክብር ይጎናጸፋሉ፡፡ በመክሊታቸው ያልተጠቀሙና መክሊታቸውን የቀበሩ አማኞች፣ ቅጣትና ፍርድ ይቀበላሉ!

ወዳጄ ሆይ፣ በተቀበሉት መክሊት ምን እያደረጉበት ይሆን? እንደተሰጠዎት ጸጋ በልዩ ልዩ የአገልግሎት ቦታ ተሰማርተው እግዚአብሔርን እያገለገሉ? ወይንስ ከአገልግሎት ርቀውና ዳር ላይ ቆመው እየታዘቡ?

ስለተቀበሉት መክሊት ጌታ ይጠይቅዎታል! በተቀበሉት መክሊት ምን እንዳደረጉበት፣ በተሰጠዎት ጸጋ ምን ያህል አገልግሎት እንዳበረከቱበት ጌታ ይጠይቅዎታል!

ወጃጄ ሆይ፣ ሁኔታዎች ቢመቹ ባይመቹ፣ የሚታየው ነገር ቢያስደስት ባያስደስት፣ የአገልግሎት ቦታው ቢማርክ ባይማርክ፣ በተገኘው ዕድል፣ እንደተቀበልነው መክሊት የማገልገል ግዴታ እንደተጣለብን መርሳት አይገባም!

--------------------------------

(ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፣ ጌታ ይባርክዎ!)

No comments:

Post a Comment