ዲቮሽን
ቁ.172/07፣
እሁድ፥
የካቲት
22/07 ዓ.ም.
(በዶ/ር በቀለ ብርሃኑ)
(በዶ/ር በቀለ ብርሃኑ)
ቅርብነቱ!
ጌታ ቅርብ ነው። በነገር
ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ (ፊሊጵ 4፡6)።
“ጌታ ቅርብ ነው” የሚለውን ቃል ዕውነታነትና ተጨባጭነት ለማረጋገጥ መንገዱ ቀላል ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳችንን በሰከነ ሁኔታና በትሕትና ስናነበው፣ ወደ ውስጣችን የሚነፍሰው ደስታና ሰላም በሚገባ ያረጋግጥልናል፡፡
አንዳንዴ ነፍስን ከሚታገሉ የኑሮ ሐሳቦችና ውጣ ውረዶች የተነሣ ባዶነት ተሰምቶን ግራ ይገባናል፡፡ ያኔ በነፍስ መታገሉን አቁመንና ድንገት ሁሉን ትተን፣ በጸጋው ዙፋን ፊት በርከክ ስንል፣ መንፈሱ ሲያረጋጋንና በረከት ወደሞላበት ዓለም ውስጥ ሲከተን ይታወቀናል፡፡ በዚህን ጊዜ በመደነቅ ማንም ሊሰጠን የማይችለውን ሕክምና በሰከንድ ውስጥ ስናገኝ ቅርብነቱ ይበራልናል፡፡
ለዚህም ነው፣ ሐዋርያው ጴጥሮስ በ1ጴጥ 1፡8-9 ላይ፣ ‹‹እርሱንም ሳታዩት ትወዱታላችሁ፤ አሁንም ምንም ባታዩት በእርሱ አምናችሁ፣ የእምነታችሁን ፍጻሜ እርሱም የነፍሳችሁን መዳን እየተቀበላችሁ፣ በማይነገር ክብር በሞላበት ሐሤት ደስ ይላችኋል›› ብሎ የተናገረው፡፡
አዎ፣ ምንም እንኳ በአካል ባናየውም፣ አሠራሩን መንፈሳዊ ዓይናችን በርቶ ስናየውና ውስጣዊ ለውጡ ልባችንን ሲያሞቀን፣ መደነቅ እንጂ፣ ወድቆ መስገድ እንጂ፣ ክብር በሞላበት ሐሤት ዝማሬ እንጂ፣ ሌላ ምንም ቋንቋ የማናገኘው! እነዚህ የውስጥ ምስክርነቶች ሲበዙልን ነው እየተሳብን፣ ሕብረታችን እየጠለቀና ሌሎች ነገሮች እያነሱብን የሚመጡት፡፡
ንጉሥ ዳዊት በመዝ 54፡4
ላይ፣ ‹‹ጌታዬ ለነፍሴ ደጋፊዋ ነው›› ያለውም ለዚህ ነው፡፡ በኑሮ ውስብስብ ውስጥ ሲያረጋጋው ስላየ! ከረግረግ ጭቃ ውስጥ ሲያወጣው ስላየ! ከብዙ ሞቶች ሲያስመልጠው ስላየ! ወገኖቼ ቅርብነቱ አስደናቂ ነው፡፡
ያለንበት ሁኔታ ለእኛ የራቀ ቢያስመስለውም፣ በፍጹም ሊዘገይ በማይችልበት ሁኔታ ለያንዳንዳችን ቅርብ ነው፡፡ በእርሱ ፊት ‹‹ረፈደ›› የሚባል ነገር የለም፡፡ በግሌ ለክብሩ መገለጫነት ይሆን ዘንድ፣ የሞተ ነገርም ሕያው ሲሆን አይቻለሁ፡፡ ‹‹አለቀ›› በተባለ ነገር ውስጥ ‹‹ሰበር ሰሚ›› ሆኖ ሲገባ ደጋግሜ አይቻለሁ፡፡
ደግሞም ብዙ ጊዜ ጌታ የራቀኝና የተወኝ መስሎኝ ግራ ገብቶኝ ያውቃል፡፡ ‹‹አለቀልኝ›› ብዬም ደንብሬ አውቃለሁ! ግን ቅርብ ነውና በተግባር የደጋፊነት በረከቱን ነፍሴ ደጋግማ አይታለች፡፡ ዘማሪው ዳንኤል በአገልግሎቱና በኑሮው ቅርብነቱንና ደጋፊነቱን በሚገባ ስላየ፣ ‹‹ይረዳል ይደግፋል፣ ጉልበት ይሆናል ጌታ›› ብሎ የዘመረው፣ ቸርነቱና ታማኝነቱ ጠልቆ ገብቶት ይመስለኛል!
አዎ! የጌታ ቅርብነትና ደራሽነት አስገራሚ ነው፡፡ ድንቅ ነው፡፡ ባልተጠበቀ መንገድ ሲደርስ፣ ባላየነው ስሌትና ቀመር ቋጠሮአችንን ሲፈታ፣ በመለኮታዊው ቅንብሩ ቅጥሩን ሲያዘልለን አይተን ነው ቤቱ የቀረነው፡፡ መዝ 48፡8 እንደሚል፣ ‹‹እንደ ሰማን እንዲሁ አይተን›› ነው ተገርመን የተከተልነው፡፡
ከወንድም አብልጦ የሚጠጋጋ ወዳጅ መሆኑን ቀምሰንና ተማርከን ነው በቤቱ ያለነው! እጅግ ቅርብ ነውና፣ አልተውህም አልለቅም ብሎናልና (ዕብ 13፡5) ስሙ ከዘላለም እስከ ዘላለም የተባረከ ይሁን!!
--------------------------------
(ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ
ያድርጉ፣ ጌታ ይባርክዎ!)
No comments:
Post a Comment