ዲቮሽን
ቁ.170/07፣
አርብ፥
የካቲት
20/07 ዓ.ም.
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
የጨለማ ሽንፈት!
ብርሃንም በጨለማ ይበራል፥ ጨለማም አላሸነፈውም (ዮሐ 1፡5)
የብሉይ ኪዳኑ ነቢይ ኢሳይያስ (9፡2) እንደተነበየው፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህች ምድር ሲመጣ፥ "በጨለማ ይሄድ የነበረው ሕዝብ ብርሃን አየ፥ በሞት ጥላ አገርም ለሚኖሩ ብርሃን ወጣላቸው፡፡
ወገኖች ሆይ፥ ጌታችን ኢየሱስ ወደዚህ ምድር የመጣው መንፈሳዊ ብርሃን ሊሰጠን ነው፡፡ መንፈሳዊ ጭለማን ገፍፎ፥ መንፈሳዊ ብርሃን ሊሰጠን! ኦ፥ ሃሌሉያ! ጌታ ወደ ሕይወታችን የገባው ጨለማችንን ገፍፎ፥ በጨለማ ውስጥ ብርሃን ይሁን ሊል፥ የጨለማን ስራ ሊያፈርስ፥ በብርሃን እንድንመላለስ ነው!
ጌታን ስንቀበል ውጦን የነበረው ትብታብ፥ ጫካና አረንቋው፥ የአጋንንት ስንክሳር፥ ጥንቆላ መተቱ፥ አፍዝ አደንግዙ፥ በጌታ ኢየሱስ ብርሃን መታሰቢያው ጠፍቶ ነጻ እንድንወጣ ነው!
ታውቃላችሁ፥ ብርሀኑ በጨለማ ሲበራ ጨለማ አያሸንፈውምና፥ በዘር በግንዳችን፥ በደም በስጋችን፥ በአቻ ጋብቻችን የተጣበቀብን የጨለማ መንፈስ ድራሹ ይጠፋል! የአባት የአያታችን፥ ቅማያት ምንጅላት ምንትስ ያደረጉት ኪዳን፥ የፈጸሙት መሃላ፥ የቀረጹት ጣዖት፥ የተከሉት ሐውልት፥ ብትንትኑ ይወጣል!
ታውቃላችሁ፥ ጌታን ስንቀበል፥ የኢየሱስ ብርሃን በእኛ ላይ ሲበራ፥ "ወልጄ አሳድጌ፥ ወግ ማዕረግ አድርሼ፥ ለፍቻለሁና አልለቀውም እያለ የሚጎርር መንፈስ በዝረራ ይወድቃል! ሃሌሉያ!
ታውቃላችሁ፥ በሕይወታችን ላይ ብርሃን በርቷልና፥ አወቅን አላወቅን፥ ገባንም አልገባን፥ እኛን እንዲያጠፋ የተላከ መንፈስ፥ ጠንቋይ ሞራ ገላጭ፥ ሰላቢ ገጣቢ፥ ፈልፈላ ድግምቱን ኤልሻዳዩ ጌታ ከእግራችን በታች ጥሎ ይረግጠዋል!
ታውቃላችሁ፥ ብርሃኑ ሲበራ እርግማን ነጋሪ፥ ጨረር አስቀባሪ፥ ኮረኮንች ወርዋሪ፥ ኮከብ አስቆጣሪ፥ መድሀኒት ቀማሚ፥ ጥላ ወጊ መንፈስ በጌታ በኢየሱስ ተመትቶ ይወድቃል! በያዕቆብ ላይ አስማት፥ በእስራኤልም ላይ ሟርት የለምና፥ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ የጨለማ ስራ በፍጹም አይሰራም!
ወገኖች ሆይ፥ የኢየሱስ ብርሃን በእኛ ላይ ከበራ፥ ተኛንም ተነሳን፥ ነቃንም አልነቃን፥ ሕዝቡን የሚጠብቅ አይተኛም፥ አያንቀላፋምና የጨለማ ስራ ሊያሰጋን አይችልም!
ታውቃላችሁ፥ ብርሃኑ በጨለማ ሲበራ፥ ጨለማ አያሽንፈውምና በዙሪያችን ያለ የትኛውም ጨለማ ይህን ብርሃን ማቆም፥ ኢየሱስን መቃወም፥ በጨለማው ግዛት ወንጌል እንዳይሰበክ፥ ምርኮ እንዳይማረክ ማገድ፥ መገዳደር በፍጹም አይችልም!
No comments:
Post a Comment