ዲቮሽን ቁ.171/07፣ ቅዳሜ፥ የካቲት 21/07 ዓ.ም.
(በጌታሁን ሓለፎም)
(በጌታሁን ሓለፎም)
የጥበብና የመገለጥ መንፈስ!
‹‹የክብር አባት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እርሱን በማወቅ የጥበብን እና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ እለምናለሁ›› (ኤፌ 1:17)፡፡
ይህ መልእክት ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፈሶን ቤተክርስቲያን እና በዚያን ዘመን በአካባቢው ላሉ ምእመናን እየተዘዋወረ እንዲነበብ ታስቦ የጻፈው ደብዳቤ ነው:: ምእመኑ ዲያና (አርጠምስስ ) ትባል ከነበረች የጣኦት አምልኮ ፊቱን አዙሮ ክርስቶስን በማመን እና እርስ በርስ በመዋደድ ያሳየው እድገት መልካም ነበር፡፡ ይህ መልእክት እግዚአብሔር ምእመኑን ወደ በለጠ ከፍታ ይዞአቸው እንዲገባ የጸለየበት እና የቃተተበት መልእክት ነው::
እግዚአብሔርን በማወቅ የጥበብ እና የመገለጥ መንፈስ እንዲሰጣችሁ እጸልያለሁ፡፡›› እግዚአብሔርን በጥቂቱ እንዳታውቁት ሌላ ብዙ የከበረ እቅድ እና ፕሮግራም ለናንተ አለው:: በቅድስናና ያለ ነውር እንድትሆኑ ታስቦ ነው በክርስቶስ የተፈጠራችሁት፣ ስለዚህ ነውርን አርቁ::
እግዚአብሔር በሰማይ ያዘጋጀላችሁ ስፍራ የከበረ ነው እና ነገራችሁን ምድራዊ በሆነ ከንቱ ነገር አትለኩት፡፡ የጌታ የሃይሉ ታላቅነት የቱን ያህል እንደሆነ እወቁ እንጂ አትፍሩ፣ አትደንግጡ፡፡ የትንሳኤው ሃይል ሙታንን ያስነሳ፣ መቃብርን የፈነቀለ ዲያቢሎስን የረታ ነውና በጌታ ታመኑ፣ ጽኑ::
የሽንፈት ኑሮ አትኑሩ! ጌታን ማወቃችሁ መልካም ነው፣ ነገር ግን ሌላ ክብር አለ! ሌላ እውቀት አለ! ሌላ ከፍታ አለ! ያን ለማየት ደግሞ የልቦናችሁ አይኖች እንዲከፈቱ ያስፈልጋል::
ወገኖቼ፣ ይህ ደብዳቤ አሁን የኛ ደብዳቤ ነው:: በዚህ ዘመን ለምንኖር አማኞች የተጻፈ መልእክት ነው! የተጠራንበት አላማ ሊገባን ያስፈልጋል:: ከመብላት፣ ከመጠጣት፣ ከመልበስ ያለፈ የዘላለም ክብር እግዚአብሔር ለእኔ እና ለእናንተ እንዳለው መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ስብከታችን፣ መልእክታችን፣ ኑሮአችን ምድርን ያማከለ እንዳይሆን፣ የልቦናችን አይኖች ተከፍተው፣ የመጥራቱ ተስፋ ምን እንደሆነ ልናውቅና ልንረዳ ያስፈልጋል!
--------------------------------
(ትምህርቱ
ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፣
ጌታ ይባርክዎ!)
No comments:
Post a Comment