Thursday, February 26, 2015

መንፈስ የሆነው ቃል!

ዲቮሽን .169/07፣ ሐሙስ የካቲት 19/07 ..
(
በዶ/ር በቀለ በላቸው)


መንፈስ የሆነው ቃል!

… ከአፌ የሚወጣ ቃሌ … የምሻውን ያደርጋል የላክሁትንም ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም (ኢሳ 5510-11)

የእግዚአብሔር ቃል እጅግ ብዙ ሥራን ይሠራል፡፡ የጌታ መንፈስ በነቢዩ ኢሳይያስ ከእኔ የሚወጣው ቃል፣ መንፈስ የሆነው ቃል፣ ወይም የጊዜው ቃል፣ የምሻውን ያደርጋል፣ የላክሁትን ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም (ኢሳይያስ 5510-11) ብሎ ተናግሯል፡፡

እውነት ነው መንፈስ የሆነው ቃል ከእግዚአብሔር አፍ ይውጣ እንጂ በከንቱ አይወድቅም፡፡ የዕብራውያን ጸሐፊ የእግዚአብሔርን ቃል ሲገልጸው የሚሠራ እና ሁለት አፍ ካለው ሰይፍ ይልቅ የተሳለ እና ወደ ጠለቀው ማንነታችን ዘልቆ ልባችንን እንደሚመረምር እና በእርሱ ፊት ሁሉ ነገር የተገለጠ እና የተራቆተ (ዕብራውያን 412-16) እንደ ሆነ ይናገራል፡፡

አዎ ትክክል! የእግዚአብሔር ቃል የሚሠራ ነው፣ ነፍስን ይመልሳል፣ ሰላምንና ደስታን ይሰጣል፣ ከብዙ ጥፋት ያወጣል ያድናልም፣ መንገድንም ያቀናል፡፡ በግሌ የቃሉን ኃይል በሕይወቴ አይቼዋለሁ፡፡ መንፈስ የሆነው ቃል ከብዙ ጉድ ሊያወጣን እንደሚችል በድፍረት መናገር እችላለሁ፡፡ በተግባር ደረጃ ይህ የሕይወት ቃል ወደ ውስጤ በመግባቱ ከመጠጥ፣ ከጫት፣ ከሲጋራ ሱስ እና ብልሹ ከሆነ ማኅበራዊ ሕይወት መንጭቆ አውጥቶኛል፡፡

እጅግ በጣም ይገርማል፡፡ እላዬ የነበረው የሱስ ቀንበር ቀላል አልነበረም፡፡ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፤ ይህ ኃይል ያለው ቃል ነፃ አድርጐኝ፣ ተለቅቄ ያለ ምንም ባርነት እየኖርኩ እገኛለሁ፡፡ ወደ እሱ ከመጣሁ በኋላም ተነግሮ የማያልቅ ሥራን በሕይወቴ እየሠራ ይገኛል፡፡

ይህ የሚሠራ ቃል የጠላትን ተግዳሮት እንድናሸንፍ ያደርገናል፤ መጽሐፉ እንዲህ ይላልና፡-“ኃያል ሆይ፣ ፍላጻዎችህ የተሳሉ ናቸው፤ እነርሱም በንጉሥ ጠላቶች ልብ ውስጥ ይገባሉ፤ አሕዛብም በበታችህ ይወድቃሉ።” (መዝሙር 455) ይህ ምንባብ የሚናገረው እንደ ተሳለ ፍላጻ፣ በመንፈስ የሚነገር ቃል የሚያመጣውን ውጤት ነው፡፡

አዎ! በሕይወታችን መንፈስ የሆነው ቃል ማንኛውንም ተግዳሮት ጥሶ የመግባትና ነገሮችን የመለወጥ ችሎታ አለው፡፡

ነገር ግን እዚህ ሊታሰብ የሚገባው ጉዳይ፣ ወደ ውስጣችን በተለያየ መንገድ የሚገባው ቃል እንዴት ይሳላል የሚለው ነው፡፡ በጆሮአችን የምንሰማቸውና በዓይናችን የምናነባቸው የእግዚአብሔር መዛግብቶች፣ ወደ ልባችን የሚያልፉት በአእምሮአችን በኩል ነው፡፡

ለቃሉ ያልተከፋፈለ ልብን በመስጠት ስናጠናውና ስናሰላስለው፣ ብሎም በተግባር ደረጃ ስንለማመደው፣ በልባችን ጽላት ላይ በማይረሳ መልኩ ይጻፋል፤ ከሕይወታችን ጋር በሚገባ ይዋሃዳልም፡፡

ታዲያ ቃሉ በውስጣችን በእምነት ሲዋሃድ ተሳለ ማለት ይቻላል፡፡ ይህ የተሳለ ቃል ነው አሸናፊና ባለ ድል የሚያደርገን! ስለዚህ ለቃሉ ያልተከፋፈለ ልብን እንስጥ !
--------------------------------

(ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፣ ጌታ ይባርክዎ!)

No comments:

Post a Comment