Sunday, February 22, 2015

ፍቅር – ያለ ጊዜው!

ዲቮሽን .165/07፣ እሁድ የካቲት 15/07 ..
(
በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)


ፍቅር – ያለ ጊዜው!

እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ እርሱ እስኪፈልግ ድረስ ፍቅርን እንዳታስነሡት እንዳታነሣሡትም አምላችኋለሁ (8፡4)።

ጾታዊ ፍቅር መጀመሪያ ጊዜ አለው፡፡ ይህ ጾታዊ ፍቅር ወደ ጾታዊ የፍቅር ግንኙነት መግቢያም የራሱ ጊዜ አለው፡፡ ጤናማ የሆነ ጾታዊ ፍቅር ወደ ጤናማ ጾታዊ ግንኙነት ለመግባት ትክክለኛ ሰውና ትክክለኛ ቦታ ይጠይቃል፡፡ ለጤናማ ጾታዊ ፍቅር ጤናማ ጾታዊ ግንኙነት ትክክለኛው ሰውና ትክክለኛ ቦታው በጋብቻ ውስጥ ነው፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ሺህ ጊዜ ሺህ ሥልጣኔ፣ እልፍ ጊዜ እልፍ ዝማኔ ይኑር፣ ከጋብቻ በፊት ወይንም ከጋብቻ ውጭ የሚደረግ ጾታዊ ግንኙነት ሥይጣኔ ነው! ሺህ ጊዜ ሺህ አፍቃሪ ይኑር፣ ከጋብቻ በፊት ወይንም ከጋብቻ ውጭ የሚደረግ ጾታዊ ግንኙነት ሥይጣኔ ነው!

ታውቃላችሁ፣ ፍቅርን ያለጊዜው መቀስቀስ፣ ፍቅርን ያለቦታው መከስከስ ነው! የፍቅር ግንኙነት ያለወቅቱ መጀመር፣ ፍቅርን ያለወቅቱ መቅበር ነው!

ታውቃላችሁ፣ መሐልየ መሐልይ ይህን ማስጠንቀቂያ ጮኾ የሚሰብከው በተለይ ለሴት ነው! ይህን ማስጠንቀቂያ በ2፡7፣ በ3፡5 እና በ8፡4 ምዕራፎች ውስጥ እየጮኸ ያለው፣ የሱናማይቷ አዋጅ፣ የሴት ልጅ ድምጽ ነው!

የሱናማይቷ ሴት አዋጅ! ‹‹እናንት ሴቶች ሆይ፣ ፍቅርን ያለጊዜው እንዳትሞክሩት፣ ፍቅርን ያለቦታው እንዳትነካኩ፣ እሳት እንዳትነኩ›› በማለት እየጮኸች ነው! ‹‹እናንት ሴቶች ሆይ፣ በማይሆን ወቅት ላይ፣ ከማይሆን ሰው ጋራ፣ ከማይሆን ቦታ ላይ ፍቅርን እንዳትነኩ፣ አደራ አደራ›› እያለች እያወጀች ነው!

የሱናማይቷ አዋጅ! ‹አያ በሬ ሆይ፣ ሣሩን አየህና ገደሉን ሳታይ› እንዲሉ፣ ‹‹እናንት ሴቶች ሆይ፣ በሥጋዊ ፍቅር ዓይናችሁ ታውሮ፣ ገደል እንዳትገቡ በጣም ተቀንቀቁ›› እያለች ነው! ከጋብቻ በፊት፣ ከጋብቻ ውጭ በምንም ሁኔታ ጾታዊ ግንኙነት እንዳታደርጉ ራሳችሁን ጠብቁ እያለችን ነው!

ወገኖች ሆይ፣ የሱነማይቷ አዋጅ፣ ለምን ለሴት ብቻ ሆነ? ትክክለኛ ሰው፣ ትክክለኛ ጊዜ፣  ትክክለኛ ቦታ ያልጠበቀ ፍቅር፣ ጤና የጎደለው፣ ችግር ያለበት ነውና፣ በዚህ ፍቅር የተያዘች ሴት አይኗ ይታወራል! ትክክለኛ ሰው፣ ትክክለኛ ጊዜ፣  ትክክለኛ ቦታ ያልጠበቀ ፍቅር፣ ጤና የጎደለው ነውና፣ ስነልቦናዋን፣ ስነመንፈሷን፣ ምስቅልቅል ያወጣል!

ታውቃላችሁ፣ የሴት ልጅ ፈተና ቀላል አይደለምና፣ ፍቅር ያለ ጊዜው ሲሆን አደጋ ያመጣል! ፍቅር ያለ ጊዜው ሲሆን ያለጊዜው ማርገዝ፣ በዚህ ላይ መከዳት፣ በዚህ ላይ መጠላት፣ በዚህ ላይ መጎዳት አስከትሎ ያመጣል !
--------------------------------

(ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)

No comments:

Post a Comment