Saturday, February 21, 2015

እጆችህ ሠሩኝ አበጃጁኝም!

ዲቮሽን .164/07፣ ቅዳሜ የካቲት 14/07 ..
(
በዶ/ር በቀለ በላቸው)

እጆችህ ሠሩኝ አበጃጁኝም!

‹‹እጆችህ ሠሩኝ አበጃጁኝም›› (መዝ 11973)

የእግዚአብሔር ቃል እጅግ ብዙ ሥራን ይሠራል፡፡ የጌታ መንፈስ በነቢዩ ኢሳይያስከእኔ አፍ የሚወጣው ቃል፣ መንፈስ የሆነው ቃል ወይም የጊዜው ቃል የምሻውን ያደርጋል የላክሁትን ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም” (ኢሳይያስ 5510-11 አጽንኦት የእኔ) ብሎ ተናግሯል፡፡

እውነት ነው መንፈስ የሆነው ቃል ከእግዚአብሔር አፍ ሲወጣ በከንቱ አይወድቅም፡፡ አብዛኞቻችን ወደ ጌታ የመጣነው በአንድ ወቅት ይህ የተሳለ ቃል ውስጣችን መተከያና መብቀያ ቦታ ስላገኘ ነው፡፡ የዕብራውያን ጸሐፊ የእግዚአብሔርን ቃል ሲገልጸው የሚሠራ እና ሁለት አፍ ካለው ሰይፍ የተሳለ እና ወደ ጠለቀው ማንነታችን ዘልቆ ልባችንን እንደሚመረምር እና በእርሱ ፊት ሁሉ ነገር የተገለጠ እና የተራቆተ (ዕብራውያን 412-16) እንደሆነ ይናገራል፡፡

አዎ የሚሠራ ነው፤ ነፍስን ይመልሳል፣ ደስታን ይሰጣል፣ ከብዙ ጥፋት ያወጣል፣ መንገድን ያቀናል ወዘተ፡፡ በምሳሌ መጽሐፍ ላይቃልም በጊዜው ምንኛ መልካም ነው፡፡ በታች ካለው ከሲዖል ያመልጥ ዘንድ የሕይወት መንገድ አስተዋዩን ሰው ወደ ላይ ይወስደዋል” (ምሳሌ 1523-24) የሚል ቃል እናገኛለን፡፡

ቃልም በጊዜው ምንኛ መልካም ነውየሚለው አሳብ በጊዜው ወይንም በሚፈለግበት ሰዓት በእግዚአብሔር መንፈስ ስለተነገረ የእግዚአብሔር ቃል ነው የሚጠቁመው፡፡ የእንደዚህን አይነት ቃል ውድነት ሲናገርምንኛ መልካም ነውይለዋል፡፡ ማለትም ሥራን የሚሠራ፣ለውጥን የሚያመጣ፣ ካለንበት ማጥ የሚያወጣ ባለውለታ የሆነ ቃል እንደሆነ ነው የሚያሳየን፡፡ ይህ ቃልበታች ካለው ከሲዖል ያመልጥ ዘንድ የሕይወት መንገድ አስተዋዩን ሰው ወደ ላይ ይወስደዋልከሚለው አሳብ ጋር ተያያዥነት ያለው ይመስላል፡፡

አዎ!ይህ የጊዜው ቃል ነው ከሲዖል የሚያስመልጠው፡፡ሲዖልየሚለው ቃል ማንኛውንም እኩይ የሆነ ነገር ሁሉ ይወክላል፡፡ወደ ላይ ይወስደዋልየሚለው አሳብ ደግሞ መንፈስ የሆነው ቃል ብርቱ እንደሆነና ከብዙ ጉድ ማውጣት እንደሚችል ያሳየናል፡፡ ይህ ቃልሰው ከሞት ወጥመድ ያመልጥ ዘንድ የጠቢብ ሰው ትምሕርት የሕይወት ምንጭ ነው” (ምሳሌ1314) ከሚለው ቃል ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ እርግጥ ነው፣ ቃሉ እያስጠነቀቀን፣ ማስተዋልን እየቸረን፣ የመለየትን ጸጋ እየሰጠንና አቅጣጫንና ጎዳናን እያስለወጠን፣ ከብዙ የሞት ወጥመዶች ያስመልጠናል፡፡

ኢየሱስ ቃሉ ውስጣችን ገብቶ ስለሚሠራው ግሩም ሥራ ሲናገርእናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል” (ዮሐንስ 831-32) ብሏል:: ከጽኑ ባርነት ይገላግላል ነው ያለን፡፡ በግሌ የቃሉን ኃይል በሕይወቴ አይቼዋለሁ፡፡ መንፈስ የሆነው ቃል ከብዙ ጉድ እንደሚያወጣን ሕያው ምስክር ነኝ እላለሁ፡፡

በተግባር ደረጃ ይህ የሕይወት ቃል ወደ ውስጤ በመግባቱ ከመጠጥ፣ ከጫት፣ ከሲጋራ ሱስ እና ከብልሹ ማኅበራዊ ሕይወት መንጭቆ አውጥቶኛል፡፡ ሳስበው ይገርመኛል፣ እላዬ ላይ የነበረው የሱስ ቀንበር ቀላል አልነበረም:: ቢሆንም ይህ ኃይል ያለው ቃል ነፃ አድርጎኝ በነፃነት ተለቅቄ ያለ ምንም ባርነት እየኖርኩ እገኛለሁ፡፡

የጠላትን ተግዳሮት የምናሸንፍበት ዋና መሣሪያችን ይህ ኃይል ያለው የእግዚአብሔር ቃል ነው፤ መጽሐፍ እንዲህ ይላልና፡- “ኃያል ሆይ ፍላጻዎችህ የተሳሉ ናቸው፤ እነርሱም በንጉሥ ጠላቶች ልብ ውስጥ ይገባሉ አሕዛብም በበታችህ ይወድቃሉ”(መዝሙር 455) ይህ ቃል የሚናገረው ተስሎና ተዘጋጅቶ በአፋችን ላይ የተዘጋጀ ቃል ሊያመጣ ስለሚችለው ውጤት ነው፡፡

በሕይወታችን መንፈስ የሆነው ቃል ማንኛውንም ተግዳሮት ጥሶ የመግባትና ነገሮችን የመለወጥ ችሎታ አለው፡፡ የአጋንንትን መረብና እቅድንም መቆራረጥ ይችላል፡፡ አንድ ወቅት የምሠራበት ቦታ የማይመች ነበረና ወደ ጌታ በዛ ጉዳይ እጸልይ ነበር፡፡

አንድ ፓስተር ወደ ምሠራበት ቢሮ መጥቶ ልጸልይልህ አለኝና ‹‹የጌታ መንፈስ ጠላቶችን ጣልሁልህ ይልሃል››ብሎ አጭር ትንቢታዊ መልእክት ነግሮኝ ሄደ፡፡ መልእክት የጊዜው መልእክት ስለነበር ልረሳው በማልችለው ሁኔታ አሁንም ልቤ ውስጥ ተቀርቅሮ አለ፡፡ ከዚያ በኋላ በትንሽ ጊዜ ውስጥ ያን አስቸጋሪ ቦታ ለቅቄ በብዙ መስፈርት የሚሻል ቦታ መሥራት ጀመርሁ፤ የጊዜው ቃል ሲመጣ ነገሮችን በፍጥነት ሊለውጥ ይችላልና፡፡

ቃሉ ለሕይወታችን ውበትን የመስጠት ችሎታ አለው፡፡ ንጉሥ ዳዊት ‹‹እጆችህ ሠሩኝ አበጃጁኝም›› (መዝ 11973) እንዳለው፣ ቃሉ እያቀና እና እያስተካከለ ሕይወታችንና ፍጻሜያችንን ይለውጣል፡፡ በጥበብ፣ በሞገስ፣ በእምነት እና በፍቅር እንድናድግ እያደረገ ደምቆ የሚታይ መልእክት ያደርገናል፡፡ እንዲሁም መንፈስ የሆነው ቃል ውስጣችንን በመሥራትና በመቀየር እንደ ጌታ ፈቃድ የሆነ መስዋዕትን እና አምልኮ እንድንሰዋ ያደርገናል፤ ቃሉ እንደዚህ እንደሚል፡- “አቤቱ በውዴታህ ጽዮንን አሰማምራት የኢየሩሳሌምን ቅጽሮች ሥራ፡፡

የጽድቁን መስዋዕት መባውንም የሚቃጠለውንም መስዋዕት በወደድህ ጊዜ ያን ጊዜ በመሰዊያህ ላይ ፍሪዳዎችን ይሰዋሉ” (መዝሙር 5118-19) እውነት ነው፡፡ ውስጣችን በሚገባ ሳይሠራ የምንሰዋው መስዋዕት ምሥጋናም ሆነ አምልኮ ከጣራ አያልፍም፡፡ ነገር ግን ለቃሉ ያልተከፋፈለ ልብን ሰጥተን በበቂ ሁኔታ ከከተመገብነው፣ ካጠናነው እና ካሰላሰልነው ውስጣችንን ከምናስበው በላይ ይሠራዋል፣ ያሠማምረዋል፡፡


ስለዚህም አምልኮአችን እና ስግደታችን እውነተኛ(authentic) እና በጌታ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ይሆናል፡፡ ጌታ ሆይ ፍጻሜያችንን የሚያሳምረውን የቃልህን ደጆች ክፈትልን፤ በቃልህ ውስጥ ያለውን እንቁ እንድናይ አይኖቻችንን አብራልን!

No comments:

Post a Comment