Wednesday, February 11, 2015

አመድ አፋሽነት!

ዲቮሽን .154/07፣ ረቡዕ የካቲት 4/07 ..
(
በፓ/ ተስፋሁን ሐጢያ)


አመድ አፋሽነት!

እነሆ፥ ዘሪ ሊዘራ ወጣ። ሲዘራም አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀና ወፎች መጥተው በሉት። ሌላውም ብዙ መሬት በሌለበት በጭንጫ ላይ ወደቀና ጥልቅ መሬት ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፤ ፀሐይም ሲወጣ ጠወለገ፥ ሥርም ስላልነበረው ደረቀ። ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፥ እሾህም ወጣና አነቀው፥ ፍሬም አልሰጠም። ሌላውም በመልካም መሬት ላይ ወደቀና ወጥቶ አድጎ ፍሬ ሰጠ፥ አንዱም ሠላሳ አንዱም ስድሳ አንዱም መቶ አፈራ። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ አለ (ማር 4፡3-9)።

በማንኛውም መስክ ወይንም ሥራ ላይ ስንሰማራ እጅግ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ካለብን ነገሮች መካከል አንዱ የተሰማራንበት ቦታ ጉዳይ ነው! ‹ሥራ ለሠሪው እሾኽ ላጣሪው› እንዲሉ፣ ትክክለኛ ሰው በትክክለኛ ቦታ ላይ ካልተሰለፈ በስተቀር ውጤቱ የዜሮ ብዜት ነው! ትክክለኛ ነገር በትክክለኛ ቦታ ላይ ካልተሰማራ በስተቀር ውጤቱ የዜሮ ድምር ነው!

ታውቃላችሁ፣ በተሰማራንበት ቦታ ውጤታማነታችንን ይወስናል! የተሰለፍንበት የአገልግሎት ወይንም የሥራ መስክ ፍሬያማነታችንን ይወስናል! ያለቦታችን ተሰልፈን፣ ያለመስካችን ተሰማርተን፣ ውጤት እናገኛለን ማለት ‹ላም ካልዋለበት ኩበት› ለመልቀም እንደ መሞከር ነው!

ታውቃላችሁ፣ እጃችን አመድ አፋሽ የሚሆነው ያለ ቦታችን ስንዘራ፣ ያለ መስካችን ስንሰማራ ነው!

ወገኖች ሆይ፣ የዘር ዘሪውን ታሪክ አስቡ! ይኼ ዘር ዘሪ በመጀመሪያዎቹ ሦስት ቦታዎች ኪሣራ ላይ ጥለውታል! ያለቦታቸው የተዘሩት ዘሮች፣ አንድም ለወፍ፣ አንድም ለጀንበር፣ አንዱም የእሾኽ ሲሳይ ሆነ! በሶስቱም ቦታዎች የወደቁት ዘሮች ሁሉ ውጤታቸው ዜሮ፣ ባዶ ድምር ሆነ!

ወገኖች ሆይ፣ ዘር ዘሪው መሥራቱ አልቀረ፣ መልፋቱ አልቀረ፣ ሆኖም ግን በትክክለኛ ቦታ ላይ አልተሰማራምና ትርፉ ዜሮ ዜሮ፤ ለፍቶ መና ቀረ!

ወገኖች ሆይ፣ በሕይወታችንም ብዙ ጊዜ ሲያጋጥመን የምናስተውለው ነገር ይኸው እውነት ነው! እንሮጣለን፣ እንወርዳለን፣ እንወጣለን፣ እንሠራለን እንደክማለን፣ ትርፋችን ኪሳራ፣ እጃችን አመድ አፋሽ ይሆናል!

ወገኖች ሆይ፣ ለፍተን ፍሬ ካጣን፣ ቦታችንን እንፈትሽ! ሠርተን ውጤት አልባ፣ ዘርተን ፍሬ አልባ ከሆንን የተሰማራንበትን ሥፍራ እንመርምር!  ምናልባት ያለቦታችን እየለፋን፣ ያስፍራችን ተሰማርተን ሊሆን ይችላልና ቦታችንን እንቀይር!


ወገኖች ሆይ፣ ለዘራችን መብቀል፣ ማፍራትና መብዛት የሚስማማ ቦታ በጥንቃቄ እንምረጥ! ለአገልግሎታችን የሚስማማ ስፍራ፣ ፍሬ ልናፈራ ልንለመልም ከምንችለው ቦታ ብቻ እንሰማራ! ከዘር ዘሪው እንማር! በሶስት ቦታ ከስሮ በአራተኛው ቦታ ፍሬው እንደበዛ እንደተደሰተው፣ ፍሬ ልናፈራ በምንችለው ስፍራ ብቻ እንሰማራ! ይህን እውነት ጆሮ ያለው ይስማ!

No comments:

Post a Comment