ዲቮሽን
ቁ.148/07
ሐሙስ፥
ጥር
28/07 ዓ.ም.
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
በዝሙት
የመውደቅ አደጋ (#2)
የዝሙት አደጋ የአገር መሪዎችንም በየአጋጣሚው ጠልፎ ከመጣል የማይመለስ ወጥመድ መሆኑን በየጊዜው የምንሰማው እውነታ ነው፡፡ የቅርብ ታሪኮችን እንኳ ስንመረምር የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን ከሞኒካ ሊዊንስኪ ጋር፥ የቀድሞዋ የኔልሰን ማንዴላ ባለቤት ዊኒ፥ ከቤት ሰራተኛዋ ከፓፉ ጋር በፈተናው ወድቀዋል፡፡ በ2009 ደግሞ የኡጋንዳውን ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሶቬኒንና ባለቤታቸውን ወደጌታ በማምጣት ከፍተኛ አክብሮት የተጎናጸፈው ሮበርት ካያንጃ የተባለ ፓስተር "ሁለት ወንድ ወጣቶችን አስገድዶ ደፍሯል" የሚል ክስ ተመስርቶበት በመላ ሀገሪቱ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ ሰንብቷል፡፡
በኡጋንዳ ሕግ መሰረት ግብረሰዶማዊነት በሞት የሚያስቀጣ ወንጀል ነው፡፡ በርግጥ ሁለቱ ወጣቶች ክሳቸውን አንስተዋል፡፡ ሆኖም ወጣቶቹ ክሱን እንዲሰርዙ የተገደዱት በዩቬሪ ሙሶቬኒና በባለስልጣኖቻቸው ግፊት ነው እየተባለ ብዙ ትችት ቀርቦበቶ ነበር፡፡ የሙሶቬኒ ቃል አቀባይ ግን ፕሬዚዳንቱም ሆኑ ባለስልጣኖቻቸው በጉዳዩ ላይ ጣልቃ አለመግባታቸውን ተናግረዋል፡፡
በርግጥ በአፍሪካ ውስጥ አንድን መሪ በዚህ መሰል ወንጀል ለማጋለጥ ቀላል አይሆንም፡፡ ከዚህም የተነሳ ነው፥ ብዙ ሰዎች ተመሳሳይ ችግር በየጓዳው አይተው እንዳላዩ፥ ሰምተውም እንዳልሰሙ የሚሆኑት፡፡
በአገራችንም ያለው ሁኔታ ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ የመሪዎችን ሀጢአት ከኋላ ኋላ ሆኖ ከማማት አልፈን ፊትለፊት ለመጋፈጥ ያለን አቅም ገና አልዳበረም፡፡ ሁኔታው አስቀያሚ ከመሆኑ ጋር ተዳምሮና፥ ሽፍንፍን የሆነው ባህላችን ተጨምሮበት፥ በቤተክርስቲያን ውስጥ በምናያቸው አስቀያሚ ነገሮች ውስጥ እጃችንን እንዳናስገባና ዝም ብለን እንድናይ ይገፋፋናል፡፡
አንዳንዴ በጉዳዩ ላይ ድፍረት አሳይተው ለመጋፈጥ የተነሱ ሰዎችም ከሕዝብ ዘንድ ድጋፍ ስለማያገኙ ወይንም አብራቸው የሚቆም ስለማይኖር፥ ችግሩን እንዳለ ከመተው ሌላ የተሻለ አማራጭ አይወስዱም፡፡
የንጉስ ዳዊት የዝሙት ሀጢአት የተገለጠው ለናታን ብቻ አልነበረም፡፡ ሌሎችም ያውቃሉ፡፡ ነገር ግን ከዚያ ሁሉ ሕዝብ መካከል ደፍሮ ዳዊትን ሊቃወመው የቻለ አንድም አልነበረም፡፡ በአገራችንም፥ በዚህ ረገድ፥ እንደ ናታን ያለ ደፋር ብዙም ባለመኖሩ፥ ጉዳዩ ወደ አደባባይ አይወጣም እንጂ፥ የነገርዬው መኖር "እዚያም ቤት እሳት አለ" እንደሚባለው ነው፡፡
እነዚህን የመሳሰሉ ታላላቅ የዓለማችን ሰዎች እንዲህ በመሰለ ፈተና መውደቃቸው እውነት ከሆነ፥ ታዋቂ አገልጋዮች በዝሙት የሚወድቁበትን ምክንያቶች መመርመሩ ሳይሻል አይቀርም፡፡ በእውነቱ ታዋቂ አገልጋዮች ለምን በዝሙት ይወድቃሉ?
1ኛ) ሰው በመሆናቸው
አገልጋዮች ሰዎች ናቸው፡፡ የመላዕክት ስብዕና የላቸውም፡፡ ከዚህም የተነሳ ያላቸው ሰዋዊ ስብዕና በተፈጥሮው ከተቃራኒ ጾታዎች ጋር የማሳሳብ ባህርይ የተላበሰ ነው፡፡ ይህም ማለት ወንዱ በሴት፥ ሴቷም በወንድ የመሳሳብ ተፈጥሮ የተላበሰ ነው፡፡ ይህ ተፈጥሮ በመንፈስ ቅዱስ ሙላትና በጸሎትና በስነምግባራዊ ዲስፕሊን በጥንቃቄ ወጥረን ካልያዝነው በስተቀር እንደ ማግኔት ነው፡፡ ማግኔት ብረት እንዲስብ፥ ተቃራኒ ጾታ እርስ በርሱ ይሳሳባል!
ይህ ተፈጥሮአዊ መሳሳብ በማንኛውም ጤነኛ የሰው ልጅ ተፈጥሮ ውስጥ አለ፡፡ በተቃራኒ ጾታ የማይሳብ ተፈጥሮ ያለው ሰው የሆነ ችግር ያለበት ነው፡፡ ይህ ተፈጥሮአዊ የስበት ሀይል ግለሰቦችን ወዳልተዘጋጁበትና ወዳልፈለጉበት አቅጣጫ ሊመራቸው ይችላል፡፡ ከነዚህ አቅጣጫዎች አንዱ በተቃራኒ ጾታ መሸነፍ፥ ወይንም በዝሙት የመውደቅ አደጋ ሊሆን ይችላል፡፡
2ኛ) ስለሚታበዩ
ታዋቂ አገልጋዮችን በዝሙት እንዲወድቁ ከሚያደርጓቸው ነገሮች መካከል ሌላው ትዕቢት ነው፡፡ ብዙዎቹ ታዋቂ አገልጋዮች በትልቅነታቸው ምክንያት የሆነች የልዕቀት ትዕቢት አለቻችው፡፡ ከዚህም የተነሳ፥ አለ አይደል፥ ሀጢአትን የረሱ፥ አውቀው የጨረሱ፥ ከጫፍ የደረሱ …መስሎ ይሰማቸዋል፡፡ ይህም ውድቀታቸውን ያፈጥነዋል፡፡
ይህ ስሜት ብዙዎቹን አገልጋዮች ጎድቷቸዋል፡፡ ሌሎች ሰዎች እንዴት መመላለስ እንዳለባቸው ይሰብካሉ፥ ያስተምራሉ፡፡ ነገር ግን ራሳቸው ከችግሩ ነጻ እንደሆኑ አድርገው ያስባሉ፡፡ መንፈሳዊነታቸው የሀጢአትን ሀይል የሚቋቋም አድርገው ያስባሉ፡፡ ነገር ግን ሰው ሆኖ የሀጢአትን ሀይል ከረታው ከጌታችንና ከመድሃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ በምድር ላይ ማንም የለም!
ትዕቢት ውድቀትን ትቀድማለችና ታዋቂ ሰዎች በዚህ ችግር ላይ እንዳይወድቁ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡ "ትዕቢት ጥፋትን፥ ኩሩ መንፈስም ውድቀትን ይቀድማል" (ምሳ 16፡18) ተጽፏልና፥ "የሚቆም የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ!"
3ኛ) ጥንቃቄ ስለሚጎድላችው
ቃሉ ሲናገር "ጥንቃቄ ይጠብቅሃል ፥ ማስተዋልም ይጋርድሃል" ይላል (ምሳ 2፡11)፡፡
ባጠቃላይ፥ ማንኛውም አይነት ችግር የራሱ የሆነ መንስኤና ውጤት (cause & effect) አለው። መንስኤው ለችግሩ ጅማሬ ወይም መነሻ የሆነ ምክንያት ማለት ሲሆን፥ ያ ጉዳይ የሚያስከትለው መዘዝ ወይም ፍሬ ደግሞ 'ውጤት' ይባላል፡፡ ውድቀቱም ከእነዚህ ከላይ ከተጠቅሱ ሁኔታዎች ምክንያት ይጀመራል፡፡ ስለሆነም፥ በእነዚህ ነጥቦች ላይ ዕለታዊ ግንዛቤ በማጣት ምክንያት እንዳንወድቅ እንጠንቀቅ! የእኛ መውደቅ በእኛ ላይ ብቻ ሳያበቃ፥ ለሌሎች መሰናክል ይሆናልና ጌታ ይርዳን፡፡ (ተፈጸመ)
No comments:
Post a Comment