Wednesday, February 4, 2015

በዝሙት የመውደቅ አደጋ (#1)

ዲቮሽን .147/07     ረቡዕጥር 27/07 ..
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


በዝሙት የመውደቅ አደጋ (#1)

እንዲህም ሆነ በዓመቱ መለወጫ ነገሥታት ወደ ሰልፍ በሚወጡበት ጊዜ፥ ዳዊት ኢዮአብን ከእርሱም ጋር ባሪያዎቹን እስራኤልንም ሁሉ ሰደደ። ... ዳዊት ግን በኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር። እንዲህም ሆነ ወደ ማታ ጊዜ ዳዊት ከምንጣፉ ተነሣ፥ በንጉሥም ቤት በሰገነት ላይ ተመላለሰ በሰገነቱ ሳለ አንዲት ሴት ስትታጠብ አየ ሴቲቱም መልከ መልካም ነበረች። …ዳዊትም መልእክተኞች ልኮ አስመጣት ወደ እርሱም ገባች፥ … ከእርስዋ ጋር ተኛ ወደ ቤትዋም ተመለሰች(2 ሳሙ 1-4)።

አገልጋዮች ብዙ የእግዚአብሔር አደራ የተጣለባቸው ሰዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ከሕዝብ ጋር በተለይም ከተቃራኒ ጾታ ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት በእያንዳንዲቱ ዕለት በጥንቃቄ ሊመላለሱ ይገባል፡፡ ይህ ጥንቃቄ የጎደለ ቀን፣ በዝሙት አደጋ ላይ የመውደቁ ዕድል ሰፊ ይሆናል፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ንጉሥ ዳዊትን አስቡ! ዳዊት አገልጋዮቹንና አጃቢዎቹን ሁሉ ወደ ሰልፍ ልኮ፣ በቤተመንግሥቱ ውስጥ ብቻውን ከሴቶች ጋር መቅረቱ በዝሙት አደጋ ላይ እንዲወድቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ አገልጋይ ብቻውን ሲሆን አደጋ አለው፡፡ አገልጋይ ከተመልካች እይታ ውጭ ሲሆን አደጋ አለው፡፡ አገልጋይ ግልጽ ሕይወት ይዞ ሊመላለስ ይገባል፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ዮሴፍን አስቡ! የጶጥፋር ሚስት ሆን ብላ እርስዋ ለብቻዋ ወዳለችበት ክፍል እያስገባች እንዲያገለግላት ታደርገው ነበር፡፡ ባሪያ በጌታው የታዘዘውን ከማድረግ ሌላ አማራጭ አልነበረውምና ለዝሙት ተግባር ወደተዘጋጀለት የአደጋ ቀጠና ሊገባ ችሏል፡፡ በርግጥ፣ ዮሴፍ ከዝሙት አደጋ ያመጠለ ቢሆንም፣ ከሴትዮዋ ብቸኛ ቦታ ገባ ወጣ ማለቱ ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሎታል፡፡

ወገኖች ሆይ፣ እኤአ በ1986 ዓ.ም. ታዋቂው የወንጌል ሰባኪ ጂሚ ስዋገርት በሌሎቹ ታዋቂ የቴሌ ወንጌላዊያን በማርቪን ጎርማንና በጂም ቤከር ላይ ራሱ በሚስተዳድረው የቴሌቪዥን የስርጭት ጣቢያ ከጋብቻ ውጭ ጾታዊ ግንኙነት እንዳላቸው በመክሰስ ጥቃት ማድረስ ጀመረ፡፡

ጎርማን በወቅቱ የጓደኛው ማኅበረ ምዕመናን አባል ከሆነች ሴት ጋር ድብቅ ጾታዊ ግንኙነት እንዳለው ጠቅሷል፡፡ ጂሚ ስዋገርት በዚህም ብቻ ሳይወሰን፣ የቤከርን ከጋብቻ ውጭ ጾታዊ ግንኙነት ለሌሎች አካላት በማጋለጡ ሒደት ላይም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ይህ ሁኔታ በሌሎቹ የብዙሃን መገናኛ አውታሮች ሰፊ ሽፋን ያገኘ በመሆኑ የብዙዎች ቀልብ ለመሳብ ችሏል፡፡

በጂም ስዋገርት ጥቃት እንቅልፍ ያጣው ጎርማን ስዋገርትን ለመበቀል እንዲያስችለው በስውር የስዋገርትን እንቅስቃሴ የሚከታተል ሰው ቀጥሮ መረቡን ዘረጋ፡፡ ስውሩ መረብ ታዲያ የተፈለገውን ዒላማ የመታው ወዲያው ነበር፡፡ ልክ አሳቻ ቦታ ላይ የተጠመደች ወጥመድ የልክስክስ አይጥ ማንቁርት እንደምትይዝ ሁሉ፣ የጎርማን ስውር ወጥመድ ጂሚ ስዋገርት ደብራ መርፍሪ ከተባለች አንዲት ሴተኛ አዳሪ ጋር ያለውን ቅጥ ያጣ ዘማዊ ንሁለላ እጅ ከፍንጅ ይዛ በማጋለጥ ለአመት ያህል ከመድረግ እንዲወርድ በማድረግ የመበቃቀያውን ሒሳብ አወራርዳለች፡፡

ጂሚ ስዋገርት በዚህ ወጥመድ መውደቁ ይፋ በሆነ በአራተኛው ቀን፣ ከስዋገርት ጋር ተገናኝታ ፎቶ የተነሣችው ይህችው ሴትኛ አዳሪ ለኒውስ ኦርላየንስ ቴሌቪዥን ስትናገር ‹‹ጂሚ የሁልጊዜ ደንበኛዬ ነው፤ ነገር ግን ከእኔ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት አድርጎ አያውቅም፣ ጂሚ ከእኔ ጋር ሲሆን ማድረግ የሚወደው ራቁቴን ሆኜ መመልከትን ነው›› በማለት ቃሏን ሰጥታለች፡፡

በርግጥ፣ ጂሚ ስዋገርት ፌብርዋሪ 1988 ዓ.ም. በጉባኤው አባላት ፊት ቆሞ፣ እንባውን እያራጨ፣ ‹‹በእናንተ ላይ ኃጢአት ሠርቻለሁና ይቅርታ እንድታደርጉልኝ እለምናለሁ›› በማለት ተማጽኖአል፡፡

‹‹ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስስ አይቀርም›› እንዲሉ፣ ሕዝቡ ይቅርታ ካደረገላቸው ከአምስት ዓመት በኋላ በ1991 ዓ.ም. ደግመው ሮዝመሪ ጋርሺያ ከምትባል ሌላዪቱ ሴተኛ አዳሪ ጋር ሲልከሰከስ በድጋሚ ተይዟል፡፡

ሌላም ታሪክ ልጨምር፡፡ ቴድ ሀጋር ይባላል፡፡ በኮሎራዶ ስፕሪንግስ የምትገኘው የኒው ላይፍ ቤ/ክ መሥራችና ዋና ፓስተር ነበር፡፡ ሀጋርድ እኤአ 2003 እስከ 2006 ዓ.ም. ድረስ የአሜሪካ ብሔራው የወንጌላያን አብያተክርስቲያናት ኅብረት ፕሬዚዳንትም ነበር፡፡

ሀጋርድ ከነበረው ከፍተኛ መንፈሳዊ ሀላፊነት የተነሳ ከጆርጅ ደብሊው ቡሽ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ነበረው፡፡ ሀጋርድ በ2006 ዓ.ም. ሜታም ፊተሚን የተባለ የግብረ ሥጋ አነቃቂ፣ ጉልበት ሰጭ፣ የአዕምሮ ማነቃቂያ ዕጽና ሱስ የሚያስይዝ አደገኛ መድኃኒት ካለማመደው ወንድ አዳሪ /ግብረሰዶማዊ/ ጠንካራ ግንኙነት እንዳለው ተደረሰበት፡፡

ቴድ ሀጋርድ ከችግሩ ይፋ መሆን በኋላ ከወንድ ግብረሰዶማዊ ጋር ስለነበረው ግብረሰዶማዊ ግንኙነት ይቅርታ በመጠየቅ ከነበረው የቤተክርስቲያን መጋቢነት ኃላፊነትና ከወንጌላዊያን አብያተክርስቲያናት ፕሬዚዳንትነት አመራር ራሱን አግለሏል፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ተዋቂ አገልጋዮች በጾታዊ ግንኙነት ስማቸው ሲነሳ የሕዝብ መነጋገሪያ መሆኑ ያለና የሚኖር ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ፣ ቢሊግራሃም ‹‹በመላው ዓለም በያንዳንዲቱ ደቂቃ በሺዎች የሚቆጠሩ አውሮፕላኖች፣ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አሳፍረው በሰላም እየተነሱ፣ በሰላም ያሳርፋሉ፡፡›› ይህን የሚዘግብ ዜና የለም፡፡ ነገር ከእነዚህ አውሮፕላኖች ውስጥ አልፎ አልፎ አንዱ ወድቆ ሲከሰከስ ወሬው በመላው ዓለም ይናኛል›› በማለት ተናግሯል፡፡


ወገኖች ሆይ፣ ቢሊ ግራሃም እውነቱን ነው! ሆኖም፣ ከአካሄድ ጥንቃቄ መጉደል የተነሣም፣ አንዳንዴ ውድቀት ይመጣል! ስለሆነም፣ አገልጋዮችም ሰዎች ናቸውና ከጥንቃቄ ማነስ የተነሳ በዝሙት ኃጢአት ሊወድቁ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን የወደቀ ይነሣልና የእግዚአብሔር ሕዝብ የሆንን ሁሉ በወደቁት ላይ ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም፡፡  ለወደቁት ልንጸልይላቸው ይገባል!

No comments:

Post a Comment