Tuesday, February 3, 2015

በእኛና በልጆቻችን ላይ – መርገም እንዳይመጣ!

ዲቮሽን .146/07     ማክሰኞጥር 26/07 ..
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


በእኛና በልጆቻችን ላይ – መርገም እንዳይመጣ!

ጲላጦስም (ሁኔታው) ሁከት እንዲጀመር እንጂ አንዳች እንዳይረባ ባየ ጊዜ፥ ውኃ አንሥቶ። እኔ ከዚህ ጻድቅ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ፤ እናንተ ተጠንቀቁ ሲል በሕዝቡ ፊት እጁን ታጠበ። ሕዝቡም ሁሉ መልሰው። ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን አሉ (ማቴ 27፡24-25)።

ትናንትና አንድ ክርስቲያናዊ አገልግሎት ተቋም ጎብኝቼ ነበር፡፡ በዚህ ጉብኝቴ ወቅት በተዋቂው የእግዚአብሔር ሰው በዴሪክ ፕሪንስ የተጻፈና ወደ አማርኛ የተተረጎመ ‹‹ለእስራኤል ያለብን ዕዳ›› የሚል ባለ አስራ ሁለት ገጾች ብሮሸር አግኝቼ አነበብሁ፡፡ ይህ አጭር መጽሐፍ በመካከለኛው ዘመን ‹‹ቅድስት አገርን ነጻ ለማውጣት›› በመስቀል ጦረኞች በተደረገ ዘመቻ ወንድ፣ ሴት፣ ሕጻን፣ ሽማግሌ፣ አሮጊት ሳይመርጡ በአውሮፓ የነበሩ የአይሁድ ማህበረሰቦች መጨፍጨፋቸውን ይገልጻል፡፡ ችግሩ በዚህ ብቻም ሳያበቃ፣ ናዚዎች ከስድስት ሚሊዮን በላይ አይሁዳዊያንን መግደላቸውን ያስረዳል፡፡

የዴሪክ ፕሪንስ፣ ዋና መልዕክት፣ አሕዛቦች ሁላችን ከእስራኤል በኩል እግዚአብሔር ካዘጋጀልን ምሕረት የተነሣ፣ እኛም በተራችን ለእስራኤላዊያን ቅን ፍቅር እንስጣቸው፣ የተቀበልነውን መዳን እናካፍላቸው፣ እንጸልይላቸው፣ ተግባራዊ የሆነ ምሕረትና በጎነት እናድርግላቸው የሚል ነው፡፡ ይህን ልብ የሚነካ ጽሁፍ ወዲያው አንብቤ እንደጨረስሁ ለዛሬው ዲቮሽኔ የሚሆን መልዕክት ውስጤ ስለሞላ እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡

ወገኖች ሆይ፣ በማቴዎስ ወንጌል 27፡24-25 አይሁድ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የከፈቱት የወንጀል ክስ ቻርጅ፣ በመዝገቡም ላይ የቀረበው ዝርዝር የቅጣት ነጥቦች እርባና የሌላቸው፣ ውሃ የማያነሱ የሐሰት ክሶች መሆናቸውን ከክፍሉ  መረዳት እንችላለን፡፡ የክሱ መንፈስ በጻድቁ ሰው ላይ ሕዝብን አስነስቶ የሀገሪቱን ጸጥታ ከማወክ በስተቀር አንዳች ፋይዳ ያለው ሆኖ አልተገኘም፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ሀገረ ገዢው ጴንጤናዊው ጲላጦስ ኢየሱስን መርምሮ ምንም በደል ስላላገኘበት ሊፈታው ቢፈልግ፣ ሕዝቡ ተቃወመ፡፡ ‹‹እኔ ከደሙ ንጹህ ነኝ፣ ጻድቁን በመግደል ኃላፊነቱን እናንተ ትወስዳላችሁ›› ብሎ ቢያስጠነቅቃቸውም፣ ‹‹ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን›› ብለው ጻድቁን ገደሉት!

ታውቃላችሁ፣ አይሁዶች የጻድቁን ደም በከንቱ የማፍሰሳቸው በደል በራሳቸውና በልጆቻቸው ላይ እንዲደርስ ያወጁት ይህ መርገም ከዚያ ትውልድ ጀምሮ ሥራውን ቀጠለ፡፡ በዚያ ትውልድ የታወጀው ይኼ መርገም ከታወጀ በሰላሳ ዓመት ልዩነት ውስጥ በማርሻል ቲቶ በትር ቤተመቅደሱን ጨምሮ እስራኤል ወደመች፡፡ ይህ መርገም ለልጆችም እንዲተላለፍ ተነግሯልና፣ ከዚያ ዘመን ጀምሮ እጅግ አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ መላው የአይሁድ ዘር ከየተገኘበት እየተለቀመ ተጨፍጭፏል!

ወገኖች ሆይ፣ ኦሽዊትዝን አስቡ! ከስድስት ሚሊዮን በላይ አይሁዳዊያን ሊነገር በሚዘገንኑ ጭካኔዎች ተገልድለዋል! በባለጨረቃዎቹም ሆነ በባመስቀሎቹ ሰይፎች የአይሁድ ሕዝቦች የዘር እልቂት ወንጀል ተፈጽሞባቸዋል!

ታውቃላችሁ፣ እስከዛሬም ድረስ በመላው ዓለም የሚገኙ የአይሁድ ሕዝቦች በጥቃት ዒላማ ስጋትና ፍርሃት እየኖሩ ናቸው! አባቶቻቸው ጻድቁን ለመግደል ኃላፊነት ወስደው፣ ‹‹ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን›› ብለው ለራሳቸውና ለዘር ማንዘራቸው ያስተላለፉት መርገም እስከ ዛሬም ድረስ እየተከተላቸው ነው!

ወገኖች ሆይ፣ ከእስራኤል እንማር! የጻድቃንን ደም በከንቱ አናፍስስ! የምንሠራው ሥራ በእኛና በልጆቻችን ላይ መርገም እንዳያደርስ ጥንቃቄ እናድርግ! በምንሠራው ኃጢአት፣ በምንፈጽመው ድርጊት፣ በእኛና በልጆቻችን ላይ መርገም እንዳይመጣ ጥንቃቄ እናድርግ! ለእስራኤል እንጸልይ! አባቶቻቸው ያፈሰሱት የኢየሱስ ክርስቶስ ደም በመላው እስራኤል ዘር ላይ ለኃጢአታቸው ምሕረት፣ የዘላለም ሕይወት እንዲያመጣ ለእስራኤል እንጸልይ!
-----
ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!

--------------------------------

‹‹የወንጌላዊው እጮኛ›› አዲስ መጽሐፍ፣ በገበያ ላይ ውሏል፡፡ ለተጨማሪ መረጃ በ0911 678158 ወይም 0911 813092 ይደውሉ፡፡

No comments:

Post a Comment