Friday, January 9, 2015

አቤት መሸወድ!


ዲቮሽን .121/07     አርብ ጥር 1/07 ..
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


አቤት መሸወድ!

… የገባዖን ሰዎች ግን ኢያሱ በኢያሪኮና በጋይ ያደረገውን በሰሙ ጊዜ፥ እነርሱ ደግሞ ተንኰል አደረጉ፣ ለራሳቸውም ስንቅ ያዙ፥ በአህዮቻቸውም ላይ አሮጌ ዓይበትና ያረጀና የተቀደደ የተጠቀመም የጠጅ አቁማዳ ጫኑ።…ሰዎቹም ከስንቃቸው ወሰዱ፥ እግዚአብሔርንም አልጠየቁም።…ከእነርሱም ጋር ቃል ኪዳን ካደረጉ ከሦስት ቀን በኋላ ጎረቤቶቻቸው እንደ ሆኑ፣ በመካከላቸውም እንደ ኖሩ ሰሙ። (ኢያሱ 9 3-27)፡፡

ወገኖች ሆይ፣ የገባኦን ሰዎች ኢያሱንና መላው እስራኤልን ሸውደው የአጋርነት ቃል ኪዳን ያደረጉበት መንገድ የሚገርም ነው፡፡ ገባኦናዊያን ከቤታቸው ሲወጡ፣ ሆን ብለው ደህና ልብሳቸውን አውልቀው ጥለው፣ ያረጀ፣ የቆሸሸና የተቦጫጨቀ ልብስ ለበሱ፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ደህና ደህና ጫማዎቻቸውን አውልቀው በመጣል፣ ያረጀና የተለጣጠፈ ጫማ አደረጉ፡፡ ለስንቅም የያዙት እንጀራ ሁሉ የደረቀና የሻገተ ነበረ። በአህዮቻቸውም ላይ አሮጌ ዓይበትና ያረጀና የተቀደደ የተጠቀመም የጠጅ አቁማዳ ጫኑ።

ወገኖች ሆይ፣ በእንዲህ ዓይነት ሽወዳ፣ ገባኦናዊያን የሩቅ አገር አምባሳደሮች፣ የሩቅ ምድር መዕልክተኞች መሰሉ፡፡ ጎረቤቶቻቸው ቢሆኑም፣ በመካከላቸውም ቢኖሩም፣ ከሩቅ አገር መጥተናል ከእኛ ጋር የሰላም ኪዳን አድርጉ አሉ። ተንኮላቸው ሰርቶ፣ ምኞታቸውም ሰምሮ፣ ከእስራኤላዊያን ጋር የሰላም ኪዳን አደረጉ፡፡


ታውቃላችሁ፣ ገባኦናዊያን ቃል ኪዳን ካደረጉ ከሦስት ቀን በኋላ ጎረቤቶቻቸው እንደ ሆኑ በመካከላቸውም እንደ ኖሩ ሰሙ። ገባኦናዊያን ይህን ያህል ሸፍጥ ሲሰሩ፣ እስራኤላዊያን አልነቁም፡፡ እግዚአብሔርንም አልጠየቁም፡፡

ታውቃላችሁ፣ እግዚአብሔርን ሳይጠይቁ፣ ተሸውደው ቀለበት ያሰሩ፣ ትዳር የመሠረቱ፣ ውሎች የፈረሙ፣ ግዴታ የገቡ፣ ቃለመሐላ የፈጸሙ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ጌታን ሳይጠይቁ፣ በሰው የተንኮል ወጥመድ የተተበተቡ፣ በሰው ተሸውደው ከማይወጡት ገደል፣ ከማይሸሹት በደል የወደቁ እጅግ ብዙ ናቸው፡፡

ወዳጄ ሆይ፣ ከኢያሱ ይማሩ! ቃል ኪዳን ሲገቡ ጌታን ይጠይቁ! ጌታን ሳይጠይቁ የሚይዙት ትዳር፣ የሚያደርጉት ኪዳን፣ የሚጨብጡት ሥልጣን፣ አደጋው ብዙ ነው! ስለሆነም፣ ጌታን ሳያማክሩ በሰው ምክር ገብተው እንዳይሸወዱ ጥንቃቄ ያድርጉ!
-----
ትምህርቱ ጠቅሞታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!
--------------------------------
‹‹የወንጌላዊ እጮኛ›› በሙሉጊዜ አገልጋዮች ላይ የሚያጋጥሙ እውነተኛ ታሪኮች የያዘ በሺዎች የተደነቀ ልብ አንጠልጣይ መጽሐፍ፣ በገበያ ላይ ውሏል፡፡ ለተጨማሪ መረጃ በ0911 678158 ወይም 0911 813092 ይደውሉ፡፡


No comments:

Post a Comment