Saturday, January 10, 2015

በእኛና በልጆቻችን ላይ – መርገም እንዳናመጣ!

ዲቮሽን .122/07     ቅዳሜጥር 2/07 ..
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


በእኛና በልጆቻችን ላይ – መርገም እንዳናመጣ!

… ጲላጦስም ሁከት እንዲጀመር እንጂ አንዳች እንዳይረባ ባየ ጊዜ፥ ውኃ አንሥቶ። እኔ ከዚህ ጻድቅ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ፤ እናንተ ተጠንቀቁ ሲል በሕዝቡ ፊት እጁን ታጠበ። ሕዝቡም ሁሉ መልሰው። ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን አሉ። በዚያን ጊዜ በርባንን ፈታላቸው፥ ኢየሱስን ግን ገርፎ ሊሰቀል አሳልፎ ሰጠ። (ማቴ 27 24-26)፡፡

አንዳንዴ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የምንፈጽማቸው ኃጢአቶች በእኛ ላይ፣ እንዲሁም በልጅ ልጆቻችን ላይ እርግማን ያስከትላሉ፡፡ በእግዚአብሔር ላይ የሚሠራ ኃጢአት ደግሞ ከኃጢአቶች ሁሉ የከፋ ኃጢአት ሲሆን፣ በትውልድ ላይ የሚያስከትለው እርግማን ለብቻው ነው!

ወገኖች ሆይ፣ ኢየሱስን አስቡ! ጌታችን ኢየሱስ በደል የሌለበት ጻድቅና ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው! ነገር ግን ይህን ጻድቅ ሰው ከምድር ለማስወገድ በአይሁድ እምነት መሪዎች ዘንድ የተልኮል አድማ ተጠነሰሰ፡፡ ይኼው ጥንስስ አድጎ፣ የሕዝብ ንቅናቄ ሆነ፡፡ ሕዝቡም ጻድቅ ከሆነው ከእግዚአብሔር ልጅ ይልቅ፣ ሀገር ያሸበረውን ወንጀለኛ በርባንን መረጠ፡፡ ይህ የሕዝብ ጥያቄ፣ የሕዝብ ንቅቃቄ ነውና ምን ማድረግ ይቻላል!

ታውቃላችሁ፣ የሕዝብ ጥያቄ፣ የሕዝብ ንቅናቄ፣ በሀገር ላይ ውጥረት ይፈጥራልና፣ የሀገር መሪዎች ጉዳዩ ያሳስባቸዋል! ጎመን በጤና እንዲሉ፣ የሀገር መሪዎች ከሐይማኖት ሐቀኝነት ይልቅ፣ ለሀገር ሰላምና መረጋጋት ቅድሚያ ይሰጣሉ፣ ከዚህም ተስተው አቋም ይወስዳሉ!

ወገኖች ሆይ፣ በሐይማኖት መሪዎች ተጠንስሶ፣ የሕዝብ ጥያቄ፣ የሕዝብ ንቅናቄ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስን ከምድር የማስወገድ ጥያቄ፣ በሀገሪቱ ህገመንግሥት እንዲፈተሽ፣ በፍርድ ቤትም እንዲታይ ተደረገ፡፡ ፍርድ ቤቱ የኢየሱስን ጻድቅነት ቢመርምር፣ አንዳች ስህተት አላገኘም! ስለሆነም፣ በዚህ ጻድቅ ሰው ላይ የተከፈተው ዘመቻም ሐሰት በመሆኑ፣ ጥያቄው እንዲቀር ሐሳብ አቀረበ፡፡ ጻድቁን ማጥፋቱም በምድሪቱ ላይ መርገም እንዳያመጣ ተጠንቀቁ አለ! ነገር ግን መሪዎቹ ስለኢየሱስ ንጽህና መስማት አልፈለጉም! ስለሆነም፣ ሁከቱን ቀጠሉ!

ወገኖች ሆይ፣ ጲላጦስም ሁከት እንዲጀመር እንጂ አንዳች እንዳይረባ ባየ ጊዜ፥ ውኃ አንሥቶ። እኔ ከዚህ ጻድቅ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ፤ እናንተ ተጠንቀቁ ሲል በሕዝቡ ፊት እጁን ታጠበ። ሕዝቡም ሁሉ መልሰው። ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን አሉ። በዚያን ጊዜ በርባንን ፈታላቸው፥ ኢየሱስን ግን ገርፎ ሊሰቀል አሳልፎ ሰጠ።

ወገኖች ሆይ፣ አንዳንዴ ከኢየሱስ ይልቅ በርባንን እንመርጣለን፡፡ ከጽድቅ ሥራ ይልቅ ለክፋትና አመጽ ድጋፍ እንሰጣለን፡፡ ለግል ጥቅማችን፣ ለዝና ክብራችን የንጹሐንን ደም በከንቱ እናፈስሳለን፡፡ አመጽ በመጠንሰስ፣ ሕዝብ በመቀስቀስ፣ ቡድን በማዋቀር የምንጠላውን ሰው ሰቅለን እንገድላለን፡፡ ይህንም በማድረግ በእኛና በልጆቻችን ላይ መርገም እናመጣለን!

ወዳጄ ሆይ፣ ከዚህ መንፈስ ይራቁ! የጻድቃንን ደም ለማፍሰስ ከሚደረግ አመጽ አይቀላቀሉ! የንጹህ ሰው ደም በከንቱ አያፍስሱ! ከኢየሱስ ይልቅ በርባን አይምረጡ! የሰው አገልግሎት ለማደናቀፍ ከሚሠራ ተንኮል እራስዎትን ያውጡ! የሌሎችን ራዕይና አገልግሎት፣ ትዳርና ሕይወት፣ ስኬትና ውጤት ለማበላሸት በሚደረግ አድማ አጋፋሪ አይሁኑ! በራስዎና በልጅ ልጆችዎ ላይ መርገም አያስከትሉ!
-----
ትምህርቱ ጠቅሞታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!
--------------------------------

‹‹የወንጌላዊ እጮኛ›› በሙሉጊዜ አገልጋዮች ላይ የሚያጋጥሙ እውነተኛ ታሪኮች የያዘ በሺዎች የተደነቀ ልብ አንጠልጣይ መጽሐፍ፣ በገበያ ላይ ውሏል፡፡ ለተጨማሪ መረጃ በ0911 678158 ወይም 0911 813092 ይደውሉ፡፡

No comments:

Post a Comment