Wednesday, January 7, 2015

የምሥራች!


ዲቮሽን ቁ.119/07     ረቡዕ፣ ታህሳስ 29/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


የምሥራች!

… እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ … መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና›› (ሉቃ 2፡10-11)።

መልአኩ ‹‹የምሥራች!›› ሲላቸው፣ እረኞቹ ወይ ‹‹ምስር ብላ!›› ወይንም፣ ‹‹ምስጋና!›› ሳይሉ አልቀሩም፡፡ ግን የምን ‹‹የምሥራች?›› መልአኩ እያበሰረ ያለው ‹‹የምሥራች?›› ለሰው ሁሉ የሚሆን መድኃኒት የመገኘቱን የምሥራች ነው! ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን መድኃኒት በመገኘቱ የሚሰማ ታላቅ ደስታ!

ወገኖች ሆይ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ሁሉ የሚሆን መድኃኒት፣ ለማናቸውም የነፍስና የሥጋ ሕመም መድኃኒት ነው! ደረጃ ሳይለያይ፣ መደብ ሳይከፋፍል፣ እረኛ ምሁር ሳይል፣ የተማረ ያልተማረ ሳይል፣ መሐይም ጠቢብ ሳይል…ለሰው ሁሉ የሚሆን፣ ለሁሉም የሚጠቅም የነፍስና የሥጋ መድኃኒት ነው!

ወዳጄ ሆይ፣ ነፍስዎን የሚያስጨንቅ ሕመም አለብዎ? የምሥራች! ኢየሱስ ክርስቶስ የሚባል የነፍስ መድኃኒት አለልዎ! የሚጨነቁበት ማናቸውም አይነት የሥጋ ሕመም አለብዎ? የምሥራች!  ኢየሱስ ክርስቶስ የሚባል ለሥጋዎ ፈውስ የሚሆን ፍቱን መድኃኒት አለልዎ!

ወገኖች ሆይ፣ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ለሰው ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች ነው! ይህን በዓል ስናከብር፣ ለነፍስና ሥጋ የሚሆን ፍቱን መድኃኒት የሆነውን ጌታ የማግኘታችንን የምሥራች ለሌሎች የማብሰሩን ኃላፊነት ልንዘነጋ አይገባም!

ወገኖች ሆይ፣ ይህ በዓል የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ነው! ይህ ልደት ለነፍስና ሥጋ ፍቱን መድኃኒት የሆነውን ጌታ የምናከብርበት ነው! ይህን ታላቅ በዓል፣ ከበዓሉ ጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ነጥቀን ለሳንታ ክላውስ ሰጥተን፣ ‹‹የገና አባት›› ምስል ሰቅለን ልደቱን ማሳሳት ትልቅ በደል ነው!

መልካም በዓል!
--------

ትምህርቱ ጠቅሞዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!

--------------------------------

‹‹የወንጌላዊ እጮኛ›› በሙሉጊዜ አገልጋዮች ላይ የሚያጋጥሙ እውነተኛ ታሪኮች የያዘ በሺዎች የተደነቀ ልብ አንጠልጣይ መጽሐፍ፣ በገበያ ላይ ውሏል፡፡ ለተጨማሪ መረጃ በ0911 678158 ወይም 0911 813092 ይደውሉ፡፡

No comments:

Post a Comment