ዲቮሽን
ቁ.118/07 ማክሰኞ፣ ታህሳስ 28/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)
ከእግዚአብሔር
ጋር ስንጣላ እንዳንገኝ!
…‹‹አሁንም እላችኋለሁ። ከእነዚህ ሰዎች ተለዩ ተዉአቸውም፤ ይህ አሳብ ወይም ይህ ሥራ ከሰው
እንደ ሆነ ይጠፋልና፤ ከእግዚአብሔር እንደ
ሆነ ግን ታጠፉአቸው ዘንድ አይቻላችሁም፥ በእርግጥ ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ ምናልባት እንዳትገኙ (የሐዋ 5፡34-39)።››
በአገራችን በተለይም በአዲስ አበባ ውስጥ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ እምነት ላይ፣ የመንፈስ
ቅዱስ የጸጋ አገልግሎትና አገልጋዮች ላይ በተደራጀ ሁኔታ ከፍተኛ ጥቃት እየደረሰ ነው፡፡ ይህ ጥቃት ከሚዲያ አንስቶ እስከ ከፍተኛ
የቤተክርስቲያናት መሪዎች ድረስ የተቀናጀ ነው፡፡ ዋና ዓላማውም፣ የጴንጠቆስጤ ልምምዶችንና የቃል እምነት እንቅስቃሴዎችን ማዳከምና
ከምድሪቱ ገጽ ማጥፋት ነው፡፡
ታውቃላችሁ፣ ታሪክ ራሱን ይደግማል ! በኮሚኒስቱ ዘመን፣ የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተክርስቲያናት
ሁሉ በጥቅል ስም ‹‹ጴንጤዎች›› ተብለው ይታወቁ ነበር፡፡ እነዚህን ‹‹ጴንጤዎች›› ደርግ ከኢትዮጵያ ምድር ለማጥፋት የሚችለውን
ሁሉ አድርጓል፡፡ ነገር ግን ‹‹ጴንጤዎቹ›› እንደ ወይራ ቀንበጥ እየበረከቱና እየሰፉ ምድርን ሲሞሉ፣ ምድሩን ሞልቶ የነበረው ደርግ
ደግሞ በተቃራኒው እየመነመነ፣ እየጫጨ፣ እየኮሰመነና እየደከመ፣ ጭራሽ ከምድሪቱ ላይ ተወገደ፡፡ ዛሬ ግን አንጋፋዎቹ ‹‹ጴንጤዎች››
ወጣቶቹን ‹‹ጴንጤዎች›› ከምድሪቱ ላይ ለመጥረግ እያሳደዱ ነው!
ወገኖች ሆይ፣ የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተክርስቲያናት መሪዎች የወጣቶቹን አገልጋዮች ራዕይና ጥሪ
ሊረዱ ይገባል! ይህም ብቻ አይደለም፣ አባቶቹ መሪዎች ወጣቶቹን አገልጋዮች ከማሳደድ ይልቅ፣ የመንፈሳዊ አባትነትን ሞዴል በመሆን፣
በፍቅር አቅርቦ በምክር ማሳደግ፣ የሚታዩ ስህተቶች አቅጣጫም በፍቅር እየገሰጹና መንገድ እያሳዩ ማስተካከል ይገባል!
ወገኖች ሆይ፣ ለዘመናት ስንጸልይበት የነበረው የእግዚአብሔር ክብር በምድራችን ሊገለጥ ጀምሯል፡፡
ይህ ክብር እንዳይጠፋ ሁላችንም ልንንከባከብ ይገባል፡፡ ነቢያት ሲነሱ ማውገዝ መፍትሔ አይሆንም፡፡ የአስተምህሮ ልዩነት ሲታይ በፍቅር
ለማረምና ለማስተካከል ከመፈለግ ይልቅ፣ ለውግዘትና ለውግረት መሮጥ መፍትሔ አይሆንም፡፡
ወገኖች ሆይ፣ ዛሬም ነቢያትና ሐዋርያት ተቀብተው ይነሳሉ! ተቀብቶ መነሳት ብቻውን አይበቃምና፣ ሊሳሳቱ፣
ሊያጠፉ፣ ሊስቱም፣ ሊያስቱም ይችላሉ! ነገር ግን፣ አገልጋዮቹን እንቅረባቸው፣ ወዳጅ እናድርጋቸው፣ ቤተሰብ እንሁናቸው፣ ሲሳሳቱ
ከእንቁላሉ እንገስጻቸው፣ ወደተጠሩበት ዓላማ እንዲደርሱ፣ ወደተቀቡበት አቅጣጫ እንዲያድጉ ድጋፍ እንስጣቸው!
ወገኖች ሆይ፣ ወጣቶቹ በታላላቅ አዳራሾች፣ በስቴዲዮሞች፣ በሕዝብ አደባባዮችና በሚዲያ
የሚያደርጉትን አገልግሎት ከቻልን ድጋፍ እስጥ እንጂ፣ ከዳር ላይ ቆመን አንቃወማቸው፣ አናውግዛቸው! በጉባኤዎቻቸው ላይም ሕዝብ
እንዳይገኝ ዘመቻ አንፍጠርባቸው፡፡
ወገኖች ሆይ፣ ከከበረው ከሕግ መምህር ከገማልያል እንማር! ምናልባትም ከወጣቶቹ አገልጋዮች ጋር ስንጣላ፣ ከእግዚአብሔር
ጋር ስንጣላ እንዳንገኝ ጥንቃቄ እናድርግ! ‹‹አሁንም እላችኋለሁ። ከእነዚህ ሰዎች ተለዩ ተዉአቸውም፤
ይህ አሳብ ወይም ይህ ሥራ ከሰው እንደ ሆነ ይጠፋልና፤ ከእግዚአብሔር
እንደ ሆነ ግን ታጠፉአቸው ዘንድ አይቻላችሁም፥ በእርግጥ ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ ምናልባት እንዳትገኙ (የሐዋ 5፡34-39)።››
--------
ትምህርቱ ጠቅሞዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፡፡ ጌታ
ይባርክዎ!
--------------------------------
‹‹የወንጌላዊ እጮኛ›› በሙሉጊዜ አገልጋዮች ላይ የሚያጋጥሙ እውነተኛ ታሪኮች
የያዘ በሺዎች የተደነቀ ልብ አንጠልጣይ መጽሐፍ፣ በገበያ ላይ ውሏል፡፡ ለተጨማሪ መረጃ በ0911 678158 ወይም 0911
813092 ይደውሉ፡፡
No comments:
Post a Comment