Monday, January 5, 2015

የነበረው እንዳልነበረ ሲሆን!

ዲቮሽን .117/07     ሰኞ ታህሳስ 27/07 ..
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


የነበረው እንዳልነበረ ሲሆን!

በግብፅም ዮሴፍን ያላወቀ አዲስ ንጉሥ ተነሣ (ዘጸ 1፡8)

ዮሴፍ ለመላው የግብጽ ሕዝብ ባለውለታቸው ነው፡፡ ሕልማቸውን የፈታላቸው፣ የረሀባቸውን ድግስ የቀለበሰ፣ የሞታቸውን ዜና የገለበጠ ባለውለታቸው ነው፡፡

ወገኖች  ሆይ፣ ከዮሴፍ መልካም አገልግሎት የተነሳ ቤተሰቡ የሆነው መላው የእስራኤል ሕዝብ ጭምር በግብጻዊያን ሁሉ ተወድዶና ተከብሮ፣ በሰላምና በደስታ ይኖር ነበር፡፡ 

ወገኖች  ሆይ፣ ይህ ወቅት ተለወጠና ሌላ ጊዜ መጣ! ዮሴፍ የረሳ፣ የዮሴፍን ታሪክ ጭራሽ የማያወሳ፣ ለእስራኤል ሕዝብም መልካም ፊት የነሳ ሌላ ጊዜ መጣ! ዮሴፍ ያበረከተውን አስተዋጽኦ ከግምት ያላስገባ፣ ድካሙን ልፋቱን ላብና ጥረቱን ከምንም ያልቆጠረ አዲስ ሰው ተነሣ!

ታውቃላችሁ፣ ለሁሉ ጊዜ አለው፡፡ ለመጠላት–ለመወደድ፣ ለመውጣት–ለመውረድ፣ ለመታወቅ–ለመረሳት፣ ለመታወስ–ለመዘንጋት፣ ለመዋረድ–ለመክበር፣ ለማትረፍ ለመክሰር፣ ለሁሉ ጊዜ አለው፡፡

ታውቃላችሁ፣ ለሁሉ ጊዜ አለውና ለሙገሳም ለወቀሳም፣ ለጭብጨባም ለድብደባም ለመፈወስም ለመቁሰልም ለመድማትም ለሁሉ ጊዜ አለው፡፡

ወዳጄ ሆይ፣ ለሁሉ ጊዜ አለውና ውለታዎ ተረስቶ፣ ወሮታዎ ቀርቶ፣ ሊያዝኑ ይችላሉ፡፡ ባከሙት ሊቆስሉ፣ ባመኑት ሊካዱ፣ በሚወዱት ሊጠሉ፣ በሚያጎርሱት ሊነከሱ፣ ይችላሉ፡፡ 

ወዳጄ ሆይ፣ ይህ ሲደርስብዎት፣ ጌታን ያስቡ! ጊዜ ሲለዋወጥ የማይለዋወጥ፣ ወዳጅ ሲቀያየር የማይቀያየር፣ የሁልጊዜ ወዳጅ፣ የሁልጊዜ ረዳት ጌታ ከእርስዎ ጋር ነውና በጌታ ይጽናኑ፡፡ ልብዎትን ያበርቱ፣ መንፈስዎን ያበርቱ!
--------
ትምህርቱ ጠቅሞዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!

--------------------------------

‹‹የወንጌላዊ እጮኛ›› በሺዎች የተደነቀ ልብ አንጠልጣይ መጽሐፍ፣ ፒያሳ ከሚገኘው በእምነት መጻሕፍት መደብር፣ በራዕይ መጻሕፍት መደብሮች፣ መካነየሱስ መጻሕፍት መደብር፣ የምሥራች ድምጽ መጻሕፍት መደብሮች፣ መሠረተክርስቶስ መዝሙር ቤት ስቴዲዮም ያገኛሉ፡፡ የመጽሐፉ ዋጋ 40 ብር ነው፡፡ በአዲስ አበባ የምትገኙ ወገኖች መጽሐፉ ያሉበት ድረስ እንዲመጣላችሁ ከፈለጋችሁ፣ በ0911 678158 ወይም 0911 813092 ይደውሉ፣ በሰዓታት ውስጥ ይመጣላችኋል፣ ነገር ግን ለትራንስፖርት 10 ብር ጭማሪ ይከፍላሉ፡፡

No comments:

Post a Comment