ዲቮሽን
ቁ.124/07 ሰኞ፣ ጥር 4/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)
የሽማግሎች – ወግ!
በዚያን ጊዜ ጻፎችና ፈሪሳውያን ከኢየሩሳሌም ወደ ኢየሱስ ቀረቡና። ደቀ መዛሙርትህ ስለ ምን
የሽማግሎችን ወግ ይተላለፋሉ? እንጀራ ሲበሉ እጃቸውን አይታጠቡምና አሉት።
እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ እናንተስ ስለ ወጋችሁ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ስለ ምን
ትተላለፋላችሁ?(ማቴ 15፡1-3)
ጻፎችና ፈሪሳውያን ይህን ጥያቄ ለኢየሱስ ክርስቶስ ከማቅረባቸው ቀደም ብሎ፣ የመጥምቁ ዮሐንስን በሰይፍ ተቀልቶ የመሞቱንና በደቀመዛሙርቱም
የመቀበሩን ዜና እናነባለን፡፡ ጌታችን ኢየሱስ የዮሐንስን ዜና ሰማዕት ሰምቶ እጅግ ከማዘኑ የተነሳ፣ ብቻውን ወደ ምድረ በዳ በታንኳ
ፈቀቅ አለ፡፡ ግን ሕዝቡ ይህን ሰምቶ ነቅሎ ተከተለው፡፡ ያለስንቅ ወደ ምድረ በዳ የወጣው ሕዝብ ተራበ፡፡ ጌታም አዘነላቸውና በጥቂት
ዓሳና ዳቦ የሴቶችና የልጆች ቁጥር ሳይጨምረ፣ ከአምስት ሺህ በላይ የሆኑ ወንዶችን አጠገበና ሸኘ፡፡
ወገኖች ሆይ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ አሁንም
ለብቻው መሆን ፈለገ፡፡ የዮሐንስ ሞት ሐዘን አልለቀቀውምና ሰው ለብቻው እንዲተወው ፈለገ፡፡ ስለሆነም፣ ደቀመዛሙርቱን ጨምሮ ሁሉም
ሰው ከባህር ማዶ እንዲሻገር አሰናብቶ ምሽቱንም ለብቻው ነበረ። ነገር
ግን፣ ደቀመዛሙርቱ በባህር ላይ ሲሄዱ ማዕበል ተነስቶ ሲጨነቁ ሳለ ጌታ በባህሩ ላይ እየተራመደ መጥቶ ማዕበሉን ጸጥ አደረገ፡፡
ይህም ብቻ ሳይሆን፣ ጴጥሮስም ከታንኳይቱ ወርዶ በውኃው ላይ እንዲሄድ አደረገው፡፡ ብዙ ሕመምተኞች ወደ እርሱ ሲመጡ፤ የልብሱንም
ጫፍ ሲዳስሱና፣ የዳሰሱትም ሁሉ ሲድኑ ነበር፡፡
ወገኖች ሆይ፣ ለጻፎችና ፈሪሳውያን መንግሥተ ሰማያት መቅረቧን በማብሰር መላውን እስራኤል ወደ
ንስሐ ይጠራ የነበረው የመጥምቁ የዮሐንስ በግፍ አንገቱ ተቀልቶ መሞት፣ በዮሐንስ ሞት ምክንያትም ኢየሱስ ክርስቶስ ይሰማው
የነበረው ስሜት፣ በኢየሱስ የተደረገው ይህ ሁሉ ድንቅና ተአምራት፣ ፈውስና ምልክት፣ ጉዳያቸው አልነበረም! ጻፎችና ፈሪሳውያን
ይጨነቁለት የነበረው አንድ ብርቱ ጉዳይ ብቻ ነበር– እርሱም የሽማግሎች ወግ ነው!
ወገኖች ሆይ፣ የተራበን ከመመገብ፣ የታመመን ከመፈወስ፣ ማዕበልን ከማዘዝ፣ ሰውን በባህር
ከማራመድ ይልቅ ጻፎችና ፈሪሳውያን ያስጨንቃቸው የነበረው ብርቱ ጉዳይ የሽማግሎች ወግ ነው! ደቀመዛሙርት ውሃ በሌለበት በምድረ
በዳ፣ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ራብተኞችን ሲመግቡ፣ ‹‹ጎሽ!›› ያላሏቸው ጻፎችና ፈሪሳውያን፣ እንጀራ ሲበሉ እጃቸውን
ባለመታጠባቸው ሲከስሷቸው እናያለን! የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ሲያፈርሱ ምንም የማይሰማቸው ጻፎችና ፈሪሳውያን ለእጅ መታጠብ ወግ
ሲቆረቆሩ እናያለን፡፡
ወዳጄ ሆይ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ለጻፎችና ፈሪሳውያን ክስ የሰጣቸውን ምላሽ እንስማ!
እናንተስ ስለ ወጋችሁ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ስለ ምን ትተላለፋላችሁ?
-----ትምህርቱ ጠቅሞታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!
--------------------------------
‹‹የወንጌላዊ እጮኛ›› በሙሉጊዜ አገልጋዮች ላይ የሚያጋጥሙ እውነተኛ ታሪኮች
የያዘ በሺዎች የተደነቀ ልብ አንጠልጣይ መጽሐፍ፣ በገበያ ላይ ውሏል፡፡ ለተጨማሪ መረጃ በ0911 678158 ወይም 0911
813092 ይደውሉ፡፡
No comments:
Post a Comment