Monday, January 12, 2015

ጽድቃችን – እንደ ‹‹ሞዴስ››!


ዲቮሽን .123/07     እሁድጥር 3/07 ..
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


ጽድቃችን – እንደ ‹‹ሞዴስ››!

… ሁላችን እንደ ርኩስ ሰው ሆነናል፥ ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው ሁላችንም እንደ ቅጠል ረግፈናል፥ በደላችንም እንደ ነፋስ ወስዶናል(ኢሳ 64፡6)፡፡

እግዚአብሔር ሰማያትን ቀድዶ ቢወርድና፣ ቢመለከተን እንዴት ያገኘን ይሆን? ከሰማያት ሲወርድ ሰማያት የተንቀጠቀጡለት፣ ተራሮች የጬሱለት፣ ባህር ውቅያኖሱ የተናወጠለት ጌታ እግዚአብሔር ሰማዮችን ቀድዶ ወደእኛ ቢወርድ እንዴት ያየን ይሆን?

ወገኖች ሆይ፣ ሙሽራው ሙሽሪትን ሊወስድ ሲመጣ ሰው ሁሉ ለማየት እንደሚጋፋ፣ ጌታ ሲመጣ ጌታን ለማየት እንጋፋ ይሆን? ሙሽራውን ሙሽሪትን ለማየት እንደምንጠራራው፣ ጌታ ሲመጣ እርሱን ለማየት እንጓጓ ይሆን?

ወገኖች  ሆይ፣ እግዚአብሔር ጻድቅ ነው! እኛ ደግሞ ኃጢአተኞች ነን! የእግዚአብሔር ጽድቅ ፍጹም ሲሆን፣ የእኛ ኃጢአት ደግሞ እንደ ሞዴስ ጨርቅ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ጽድቅ በቃላት ሊገልጡት ከሚችሉት በላይ ፍጹም ሲሆን፣ የእኛ ኃጢአት በእግዚአብሔር ዓይን ሲታይ ደግሞ አስነዋሪነቱ እንደ ሞዴስ ጨርቅ ነው! ሺህ ጊዜ ሺህ ስንጸድቅ ብንውል፣ እንፍ ጊዜ እልፍ እልፍ ስንቀደስ ብንውል፣ በእግዚአብሔር ዓይን ሲታይ ያ ሁሉ ልፋት እንደ ሞዴስ ጨርቅ ነው!

ማንም ሰው በእግዚአብሔር ሊጸድቅ አይችልም! ጽድቃችን ክርስቶስ ነው! ይህንን የክርስቶስን ጽድቅ በንስሐ ተቀብለን፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ደም ታጥበን፣ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃንና ቅዱሳን ሆነን ልንገኝ ይገባል!

ወገኖች ሆይ፣ ነቢዩ ኢሳይያስ አገልግሎቱን የጀመረ አካባቢ፣ የሌሎች ሰዎችን ኃጢአት እየተመለከተ፣ ይል ነበር፡፡ ነገር ግን፣ ከምዕራፍ ስድስት በኋላ መልዕክቱ ተቀይሮ፣ ‹‹ወዮልኝ፣ ወዮልኝ!›› ማለት ጀመረ፡፡ ይህም ለውጥ የመጣው፣ በቅድስናው ከፍ ያለ እግዚአብሔር ከፍ ባለ ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ስለታየው ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ነቢዩ ኢሳይያስ በምዕራፍ 6 ላይ የታየው የከንፈሮቹ እርኩሰት ነበር፡፡ ይህን ኃጢአቱን ተናዘዘና ጌታ በደሉን አስወግዶለት፣ ለኃጢአቱም ስርየት ሰጠው፡፡ ከዚያም የእግዚአብሔር መልዕክተኛ ሆኖ ተላከ! ወገኖች ሆይ፣ ኃጢአት የማያቋርጥ ትግል ይጠይቃልና፣ ነቢዩ ኢሳይያስ በምዕራፍ 64 ላይ፣ የእርሱም ሆነ የእስራኤላዊያን ጽድቅ፣ እንደ ሞዴስ ጨርቅ መሆኑን እየመሰከረ በማናዘዝ ላይ ነው!

ወዳጄ ሆይ፣ እግዚአብሔር ሰማያትን ቀድዶ ቢወርድና፣ ቢመለከትዎ እንዴት ባለ ሕይወት ያገኘዎ ይሆን? አለኝ የሚሉት ‹‹ጽድቅ›› እንደ መልካም ሽቱ የሚያውድና ይጣፍጠው ይሆን? ወይስ እንደ ሞዴስ ጨርቅ የሚጸየፈው?
-----
ትምህርቱ ጠቅሞታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!
--------------------------------
‹‹የወንጌላዊ እጮኛ›› በሙሉጊዜ አገልጋዮች ላይ የሚያጋጥሙ እውነተኛ ታሪኮች የያዘ በሺዎች የተደነቀ ልብ አንጠልጣይ መጽሐፍ፣ በገበያ ላይ ውሏል፡፡ ለተጨማሪ መረጃ በ0911 678158 ወይም 0911 813092 ይደውሉ፡፡


No comments:

Post a Comment