ዲቮሽን
ቁ.125/07 ማክሰኞ፣ ጥር 5/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)
እግዚአብሔር ሲያረፍድ!
ኢየሱስም በራሱ አዝኖ ወደ መቃብሩ መጣ፤ እርሱም ዋሻ ነበረ፤ ድንጋይም ተገጥሞበት ነበር። ኢየሱስ፦
ድንጋዩን አንሡ አለ። የሞተውም እኅት ማርታ። ጌታ ሆይ፥ ከሞተ አራት ቀን ሆኖታልና አሁን ይሸታል አለችው። ኢየሱስ፦ ብታምኚስ
የእግዚአብሔርን ክብር እንድታዪ አልነገርሁሽምን? አላት(ዮሐ
11፡38-40)።
የቢታኒያዎቹ
ማርያምና ማርታ ወንድማቸውም አልዓዛር በኢየሱስ ክርስቶስ በጣም የሚወደዱ ቤተሰቦች ናቸው፡፡ ወንድማቸውም አልዓዛር ሲታመም ታዲያ
በጣም ለሚወዱትና ለሚወዳቸው ጌታ ‹‹እነሆ የምትወደው ታሞአል›› በማለት የቶሎ ድረስልን ጥሪ አደረጉለት፡፡ ጌታ ግን እንኳን ቶሎ
ሊደርስላቸውና ወንድማቸውን ሊፈውስላቸው፣ በቀብሩ ላይም እንኳ ሳይገኝላቸው ቀረ! እንዴት የሚያሳዝን ነገር ነው!
ታውቃላችሁ፣
የሚወዱትን ሰው ታምሞ ካልጠየቁ፣ ሳይጠይቁም ቢሞት፣ ሞቶም ካልቀበሩ የሚያሳዝን ነገር ነው! ታውቃላችሁ፣ ማርያም ጌታን ሽቱ የቀባችው እግሩንም በጠጕርዋ ያበሰችው
ነበረች! ሆኖም፣ በእንዲህ ዓይነት ፍቅር የምትወድደው ጌታ ለገዛ ወንድሟ እንኳ ሳይደርስላት ቀረ!
ወገኖች ሆይ፣ ለእህትማማቾቹ ጥሪ ጌታ
ኢየሱስ ክርስቶስ ምላሽ ሳይሰጥ ቀረ፡፡ ይህም በመሆኑ፣ ወንድማቸው ሞተ፣ ሞቶም ተቀበረ፣ ከተቀበረም በኋላ አራት ቀን አለፈ!
ታውቃላችሁ፣ የተቀበረ ነገር አብቅቶለታል!
የተቀበረ ነገር ከአራት ቀን በኋላ ከመሽተትና፣ ከመበስበስ በቀር፣ ሌላ ታሪክ አይጠበቅበትም! ነገር ግን፣ ጌታ ኢየሱስ አልዓዛር
ከተቀበረ ከአራት ቀን በኋላ ወደማርያምና ማርታ መጣ!
ወገኖች ሆይ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ አልዓዛር ከተቀበረ ከአራት ቀን በኋላ ወደማርያምና ማርታ ሲመጣ፣ ማርያምና ማርታ ጌታን
የፈለጉበትና የጠበቁበት ጊዜ አልፎ ሄዷልና፣ በጌታ ያላቸው ተስፋ ከወንድማቸው ጋራ ሞቶ ተቀብሯልና፣ ሌላ ታሪክ በመጠበቅ ላይ አልነበሩም!
ነገር ግን የሚወዱት ጌታ ሌላ ታሪክ ይዞ ነበር የመጣው!
ታውቃላችሁ፣ ጌታ ሲመጣ ታሪክ ይቀየራል! ጌታችን ሲመጣ፣ ተስፋ የቆረጥነው፣ ሞቶ የቀበርነው ትንሣኤ ያገኛል! የጠበቅነው ጊዜ ቢያልፍ፣
የጸለይነው ዘመን ቢያበቃ፣ ተስፋ ያደረግነው እንደ ጉም ቢተንን ልባችን አይውደቅ! ጌታ ሲመጣ ግን ሁሉም ቦታ ቦታውን ይይዛል!
ጌታ ሲመጣ፣ የሞተው ድምጹን ይሰማል! የጌታ ድምጽ ሲመጣ ደግሞ መቃብር የዋጠውን ይተፋል! መቃብር የዋጠውን ሲተፋ፣ የሞተው ይነሳል!
የሞተው ሲነሳ ክብርና ምስጋና ውዳሴና ስግደት ለእግዚአብሔር ይሆናል!
ወዳጄ ሆይ፣ በእርስዎም ሕይወት ይህ ተአምር ሊሆን እንደሚችል ያምናሉ? ተስፋ የቆረጡት እንዲለመልም፣ ሞቶ የቀበሩት
ትንሣኤ እንዲያገኝ፣ በገዛ ሕይወትዎ፣ በዓይን በብሌንዎ የእግዚአብሔርን ክብር ማየት እንዲችሉ ይህንን ያምናሉ? የሚያምኑ
ከሆነ ታዲያ፣ እግዚአብሔር ሲያረፍድ የቀረ እንዳይመስልዎ!
-----ትምህርቱ ጠቅሞታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!
--------------------------------
‹‹የወንጌላዊ እጮኛ›› በሙሉጊዜ አገልጋዮች ላይ የሚያጋጥሙ እውነተኛ ታሪኮች
የያዘ በሺዎች የተደነቀ ልብ አንጠልጣይ መጽሐፍ፣ በገበያ ላይ ውሏል፡፡ ለተጨማሪ መረጃ በ0911 678158 ወይም 0911
813092 ይደውሉ፡፡
No comments:
Post a Comment