Sunday, February 1, 2015

መልካም ዕድል ምርጫ!

ዲቮሽን .144/07     እሁድጥር 24/07 ..
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


መልካም ዕድል ምርጫ!

…እርሱ ወደ አንዲት መንደር ገባ፤ ማርታ የተባለች አንዲት ሴትም በቤትዋ ተቀበለችው። ለእርስዋም ማርያም የምትባል እኅት ነበረቻት፥ እርስዋም ደግሞ ቃሉን ልትሰማ በኢየሱስ እግር አጠገብ ተቀምጣ ነበረች። ማርታ ግን አገልግሎት ስለ በዛባት ባከነች…(ሉቃ 10፡38-40)።

የምንኖርበት ክፍለ ዘመን የሰው ልጆችን በብዙ የኑሮ ጉዳዮች እዚህና እዚያ እያሯሯጠ የሚያባክን ሆኗል! ሩጫ ለእህልና ውሃ፣ ሩጫ ለትምህርትና ሥራ፣ ሩጫ ለሀብትና ጥሪት፣ ሩጫ ለአገልግሎትና ስኬት፣ ሩጫ ለዝናና ክብር የሰው ልጆችን ሁሉ የሚያባክን ሆኗል! ሠርቶ ለመለወጥ፣ ታግሎ ለማሸነፍ፣ ተሻግሮ ለማለፍ የሰው ልጆች ሁሉ በብዙ ነገር ይጨነቃሉ፣ በብዙ ነገር ይታወካሉ፣ በብዙ ነገር ይታመማሉ!

በአገልጋዮችም ዘንድ ያለው እውነት ተመሣሣይ ነው! አገልጋዮችም ሁሉ በሥራ መደራረብ፣ ብዛትና ክብደት ሲባክኑ ይውላሉ! አንዱ ጉዳይ ሳያልቅ ሌላው እየተከተለ፣ ይኼም መስመር ሳይይዝ ሌላ እየተግተለተለ አንዱን እያነሱ ሌላውን እየጣሉ እዚህና እዚያ እያሉ ሲባክኑ ይውላሉ!

ወገኖች ሆይ፣ ከአገልግሎት ብዛትና መደራረብ የተነሣ አንዳንድ አገልጋዮች በሥራ ውጥረት በሽታ ተቃጥለው ይሞታሉ – 'burn out' ያደርጋሉ! ከአገልግሎት ብዛት፣ ብዙ ኃላፊነት ባንዴ ይዞ ለመወጣት ከመሞከር የተነሳ፣ ከሥራ ብዛት የተነሳ እዚህና እዚያ እያሉ ከመባከን የተነሳ በርካታ መጋቢዎች ለብክነት (ውጥረት) በሽታ ይጋለጣሉ!

ወገኖች ሆይ፣ ብዙ አገልጋዮች ዕለታዊ ሥራን እንደ ቅርጫ ሥጋ በሰዓት መድበው፣ ቅደም ተከተሉን በማዋቀር ይዘው መሥራት ቢፈልጉም፣ ከአገልግሎት ብዛት የተነሣ ከጠዋት እስከ ማታ በውጥረት ይውላሉ! ቀኑን ሙሉ በዚህ ሁኔታ ውለው፣ ከውጥረት የተነሳ እራሳቸው ታምሞ፣ ጉልበታቸው ዝሎ፣ ማታ ወደ ቤት ሲገቡ እንደ አስከሬን የሆነ ሰውነታቸውን ይዘው ከአልጋ ይወጡና እንደ ሞተ ሰው ተኝተው ጠዋት ይነሳሉ፡፡ ከዚያም ወደ ቀጣዩ ዕለት ሥራ ሩጫ ይጀምራሉ!

ወገኖች ሆይ፣ ማርያምና ማርታን አስቡ! ኢየሱስ ክርስቶስ ከቤታቸው ሲገባ ማርያም ከእግሮቹ ሥር ተቀምጣ በተረጋጋ መንፈስ ከኢየሱስ መማር፣ ቃሉን መስማት መረጠች፡፡ እህቷ ማርታ ግን የሚያስፈልገውን ለማሟላት በመጨነቅ ወዲያ ወዲህ እያለች መባከን ጀመረች፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ጌታ ማርታን እንዲህ አላት፣ ‹‹ማርታ፥ ማርታ፥ በብዙ ነገር ትጨነቂአለሽ ትታወኪማለሽ፥ የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው፤ ማርያምም መልካም ዕድልን መርጣለች ከእርስዋም አይወሰድባትም።››

ታውቃላችሁ፣ የአገልግሎት ብዛት ትርፉ ብክነት፣ ውጥረትና ጭንቀት ነው! የእኛ ጭንቀትና ውጥረት፣ የእግዚአብሔርን ሥራ አይሠራምና ትርፉ መባከን ብቻ ነው! ስለሆነም፣ የአገልግሎት ሁሉ ቁንጮ፣ የምርጫ ሁሉ አውራ የሆነውን በእግሮቹ ሥር የማረፍ፣ የመረጋጋትና ቃሉን የመስማት ምርጫ ይኑረን! ይኼ ምርጫ ከሁሉ የተሻለ፣ መልካም ዕድል ምርጫ ነው!

ወገኖች ሆይ፣ ዕለታዊ ተግባራችንን ለመፈጸም ዕለታዊ መርሐግብር ስንዘረጋ፣ የዕለቱ ቁንጮ ሥራ በእግሮቹ ሥር ማረፍ፣ የመረጋጋትና ቃሉን የመስማት ምርጫ ይሁን! ይኼ ምርጫ የተሻለ፣ መልካም ዕድል ምርጫ መሆኑን አንርሳ!

ወገኖች ሆይ፣ ቃሉን የመስማት ምርጫ፣ ቃሉን በመልካምና በበጎ ልብ ሰምቶ በቃሉ መጽናትን በቃሉ በመኖር ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው። ማርያም የመረጠችው ምርጫ ይህንኑ ነው!  ጌታ የወደደው ይህንን ምርጫ ነው!

-----
ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!

--------------------------------

‹‹የወንጌላዊው እጮኛ›› አዲስ መጽሐፍ፣ በገበያ ላይ ውሏል፡፡ ለተጨማሪ መረጃ በ0911 678158 ወይም 0911 813092 ይደውሉ፡፡

No comments:

Post a Comment