ዲቮሽን
ቁ.132/07 ማክሰኞ፣ ጥር 12/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)
የሕጻናት – ዕጣ ፈንታ!
ከሌዊ ወገንም አንድ ሰው ሄዶ የሌዊን ልጅ አገባ። ሴቲቱም
ፀነሰች፥ ወንድ ልጅም ወለደች መልካምም እንደሆነ ባየች ጊዜ ሦስት ወር ሸሸገችው። ደግሞም ልትሸሽገው ባልቻለች ጊዜ፥ የደንገል
ሣጥን ለእርሱ ወስዳ ዝፍትና ቅጥራን ለቀለቀችው ሕፃኑንም አኖረችበት፥ በወንዝም ዳር ባለ በቄጠማ ውስጥ አስቀመጠችው(ዘጸ 2፡1-3)፡፡
ሕጻናት ግራ ቀኛቸውን የማያውቁ ፍጥረታት ናቸው፡፡ ሕጻናት ራሳቸውን የማያውቁ ሕዝቦች
ናቸው፡፡ ሕጻናት ስለራሳቸው መወሰን የማይችሉ፣ ዕጣ ፈንታቸውን መገመት የማይችሉ የዋህ ፍጥረታት ናቸው፡፡ ሕጻናት መኖርንም ሆነ
ሞትን በቅጡ ለይተው የማያውቁ ትንንሽ ‹‹መላዕክት›› ናቸው!
ታውቃላችሁ፣ ሕጻናት አቅም የሌላቸው ምስኪን ፍጥረታት ናቸው! ሕጻናት ሲራቡ ከማልቀስ፣
ሲጠግቡ ከመሳቅ ያለፈ ታሪክ የማያውቁ ንጹህ ‹‹መላዕክት›› ናቸው!
ታውቃላችሁ፣ የሕጻናት ዕጣ ፈንታ ያለው ከእግዚአብሔር በታች በወላጆቻቸው እጅ ነው!
የማሳደግ፣ የመግደል፣ የማንሳት የመጣል ዕድሉ ያለው በወላጆች እጅ ነው! አቅም ጉልበታቸው፣ ዕጣና ክፍላቸው፣ ኑሮና ሞታቸው በወላጅ
እጅ ነው!
ወገኖች ሆይ፣ ሙሴን አስቡ! ተጸንሶ ሲወለድ፣ ተወልዶም ሶስት ወር ሲሞላው ከእናቱ
ፍቅር ውጭ፣ ከእናቱ እቅፍ ውጭ፣ ከእናቱ ጡት ውጭ፣ በግብጽ ምድር ስላለው አዋጅ የሚያውቀው ታሪክ የለም፡፡ ሞቅ ካለው ከእናት
ፍቅርና ፈገግታ ጋር፣ ከደረቷ ላይ የሚፈስሰውን ወተት ትንንሽ እግቶቹን እያወራጨ ከመጥባት በስተቀር፣ የሚያውቀው ታሪክ የለም፡፡
ወገኖች ሆይ፣ ሕጻኑ ሙሴ ሊበላው ፈልጎ ለድፍን ሶስት ወራት በዙሪያው ሲያንዣብብ የነበረውን
አሞራ አይቶትም አያውቅም!
ታውቃላችሁ፣ እናትየው ልጇን ሙሴን ከሞት መልአክ የመሸሸግ ዕድል ፈጠረች! ተሳካላትና
ሙሴ ከሞት የማምለጥ ዕድል አገኘ! ይህም ሁኔታ ታወቀና፣ እናትየው ከሶስት ወራት በላይ ልትሸሽገው እንዳልቻለች እርግጠኛ ሆነች!
ስለሆነም ተጨነቀች! ተጨንቃ ብቻም ዝም አላለችም! ዓይኗ እያየ የምትወድደውን ልጇን የሞት መልዐክ ሊነጥቅባት ነውና፣ ሌላ ዕድል
ፈጠረች! ሕጻኗን የደንገል ሣጥን ሠርታና፣
ውሃ እንዳያስገባ አዘጋጅታ፣ ሕፃኑን አኖረችበትና፥ በወንዝ ዳር ባለ በቄጠማ ውስጥ አስቀመጠችው።
ታውቃላችሁ፣ ይህን
ዕድል ሌላ ዕድል ፈጠረ! እናቱ የፈጠረችለት ይህ ዕድል ሌላ ዕድል የወለደለት ሕጻኑ ሙሴ ከሞት የማምለጥ ዕድል አገኘ! ሙሴ ወደ
ፈርዓን ቤተመንግሥት ገባ! የፈርዖን የልጅ ልጅ የመባል ዕድልም አገኘ!
ወገኖች ሆይ፣
የሕጻናት የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል አይታወቅምና፣ ለልጆች ዕድል እንፍጠርላቸው! ልጆች ወልዶ ማሳደግ ቢከብድም፣
ይህን ፈርተን ልጅ ከመውለድና ከማሳደግ ወደኋላ አንበል! ወላጅ የሌላቸውን፣ የተጣሉ፣ ድሃ አደግ ልጆችን ከወደቁበት ለማንሳት አንፍራ!
መወለድ ቋንቋ ነውና፣ የሌላ ሰው ልጅ በሕጋዊ መልኩ ወስደን የራሳችን አድርገን ለማሳደግ አንፍራ! ለሕጻናት ተገቢውን የትምህርት
ዕድል ከመፍጠር ወደኋላ አንበል! በዚህ ልጅ ምክንያት፣ ነገ የሚሆነው አይታወቅምና፣ ከሙሴ እናት እንማር!
-----
ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!
ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!
--------------------------------
‹‹የወንጌላዊ እጮኛ›› አዲስ መጽሐፍ፣ በገበያ ላይ ውሏል፡፡ ለተጨማሪ መረጃ
በ0911 678158 ወይም 0911 813092 ይደውሉ፡፡
No comments:
Post a Comment