ዲቮሽን ቁ.128/07 አርብ፥ ጥር 8/07 ዓ.ም
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
ከተቀቡ - ይወገራሉ!
እስጢፋኖስም ጸጋንና ሀይልን ተሞልቶ በሕዝቡ መካከል ድንቅንና ታላቅ ምልክትን ያደርግ ነበር… አንዳንዶቹ ተነስተው እስጢፋኖስን ይከራከሩት ነበር፥ ይናገርበት የነበረውንም ጥበብና መንፈስ ይቃወሙ ዘንድ አልቻሉም… የናዝሬቱ ኢየሱስ ይህን ስፍራ ያፈርሰዋል፥ ሙሴም ያስተላለፈልንን ስርዓት ይለውጣል ሲል ሰምተነዋልና የሚሉ የሐሰት ምስክሮችን አቆሙ (የሐዋ 6፡8-15)
እስጢፋኖስ መልካም ምስክርነት የነበረው ሰው ነበር፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ፥ እምነትና ጥበብም የሞላበት ሰው ነበር፡፡ በነዚህ ማንነቱ ምክንያት እስጢፋኖስ ከሌሎች ሰባት ሰዎች ጋር ለድቁና አገልግሎት ተመረጠ! የድቁናው ምርጫ ያስፈለገበት ምክንያት በምግብ ማደል አሰራር ላይ ለተፈጠረው ማጉረምረም መፍትሔ እንዲሆን ነው፡፡
ወገኖች ሆይ፥ የምዕመናን ቁጥር እየበዛ ሲሄድ፥ የግሪክ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑት አይሁድ ማጉረምረም ጀመሩ! ምክንያታቸውም፥ በየዕለቱ ምግብ በሚታደልበት ጊዜ ባሎቻቸው ለሞቱባቸው ግሪክ ተናጋሪ አይሁድ ሴቶች የሚሰጠው ምግብ፥ ባሎቻቸው ለሞቱባቸው ዕብራይስጥ ተናጋሪ የአይሁድ ሴቶች ከሚሰጠው ያነሰ ነው፥ የሚል ክስ ነው!
ወገኖች ሆይ፥ እስጢፋኖስ የምግብ እደላውን ፍትሐዊ ለማድረግ እምነት ከተጣለባቸው ሰባት ሰዎች አንዱ ነበረ፡፡ በዚህ አገልግሎቱ ቀደም ሲል ተፈጥሮ የነበረው ጉርምርምታ ዳግመኛ አለመደመጡም ሆነ ስሙን በክፉ የሚያነሳ ሰው አለመገኘቱ እስጢፋኖስ በድቁና አገልግሎቱ ስኬታማ እንደነበር መናገር ይቻላል!
ታውቃላችሁ፥ የእስጢፋኖስ ስም በክፉ መነሳት የጀመረው ጸጋና ሀይል ተሞልቶ እጅግ አስደናቂ የሆኑ ተአምራትን በሕዝቡ ፊት ማድረግ ሲጀምር ነው!
ታውቃላችሁ፥ በሕይወታችን ጸጋና ተአምራት፥ ድንቅና ምልክት መሆን ሲጀምር ክርክር ይነሳል! ተራ አባል ሆነን ያልተወራ ወሬ፥ ቅባት ተቀብለን ማገልገል ስንጀምር መጦዝ ይጀምራል! ተራ ምዕመን ሆነን ያልተሰማ ዜና፥ ድንቅና ምልክት ማድረግ ስንጀምር የሰበር ይሆናል!
ታውቃላችሁ፥ ተቀብቶ መውጣት ሰልፈኛ ያስነሳል! ድንቅና ምልክት ማድረግ ክርክር ያመጣል! ጥበብና መንፈስ መግለጥ ተቃውሞ ያስነሳል!
ታውቃላችሁ፥ ቅባት ተቀብሎ በቅባት ማገልገል ቅናት ይቀሰቅሳል፥ በሐሰት ያስከስሳል፥ ውግዘት ያስከትላል!
ወገኖች ሆይ፥ ቅባት ተቀብሎ በቅባት ማገልገል ቅናት ምቀኝነት ክፉ ወሬ ብቻ ሳይሆን፥ ክርክር ጭቅጭቅ የሐሰት ክስ ብቻ ሳይሆን፥ መወገር፥ መደብደብ፥ መሰቀል ያመጣል!
-------
ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!
ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!
No comments:
Post a Comment