Saturday, January 17, 2015

የመግለጥ – አገልግሎት (#1)!

ዲቮሽን .129/07     ቅዳሜጥር 9/07 ..
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


የመግለጥ – አገልግሎት (#1)! 

አሁን ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ወደ እናንተ መጥቼ በልሳኖች ብናገር፥ በመግለጥ ወይም በእውቀት ወይም በትንቢት ወይም በትምህርት ካልነገርኋችሁ ምን እጠቅማችኋለሁ?(1ቆሮ 14፡6)፣ … ደግሞ የወንጌልን ምሥጢር በግልጥ እንዳስታውቅ አፌን በመክፈት ቃል ይሰጠኝ ዘንድ ስለ እኔ ለምኑ፤ ስለ ወንጌልም በሰንሰለት መልእክተኛ የሆንሁ፥ መናገር እንደሚገባኝ ስለ እርሱ በግልጥ እናገር ዘንድ ለምኑ (ኤፌ 6፡19-20)፡፡

ሐዋርያው ጳውሎስ ከላይ በቀረቡ ጥቅሶች ውስጥ የተናገራቸው የመግለጥ ዓይነቶች ሁለት ናቸው፡፡ ከነርሱም፣ አንደኛው ‹‹የወንጌል ምስጢር›› ሲሆን ሁለተኛው ‹‹የእግዚአብሔር ምስጢር›› ተብለው የተጠቀሱ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ‹‹መግለጥ›› ነባራዊ የሆነውን የወንጌልን ምስጢር ተርትሮ የመስበክን ወይም የማስተማርን ብቃት ሲያመለክት፣ ሁለተኛው ‹‹መግለጥ›› ደግሞ ቅጽበታዊ የሆነውን እግዚአብሔር ለሕዝቡ የሚገልጠውን ምስጢር ተረድቶ ለሰው የማስተላለፍ ችሎታን ያመለክታል፡፡

ታውቃላችሁ፣ አንድ አገልጋይ ‹‹ባለመግለጥ›› ሊባል የሚችለው እነዚህን ሁለቱን ነገሮች አጣምሮ፣ ወይንም ከሁለቱ አንዱን ይዞ ሲገኝ ነው!

ታውቃላችሁ፣ ‹‹መግለጥ›› ማለት እግዚአብሔር ለልጆቹ መግለጥ የሚፈልገውን ነገር አጉልቶ ማሳየት፣ ዘርዝሮ ማብራራት እና ተንትኖ ማስረዳት ነው!

ታውቃላችሁ፣ ‹‹መግለጥ›› ማለት የወንጌልን ምስጢር በግልጥ ማስታወቅ፣ የተገለጠውን ነገር በድፍረት መናገር፣ ያለፍርሃት ማስታወቅ፣ ያለፍርሃት ማስተላለፍ ነው!

ወገኖች ሆይ፣ የመግለጥ አገልግሎት በተፈጥሮው ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ነው! ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ ካልተደረገበት አገልግሎቱ በቀላሉ ለስህተት የመጋለጥ ዕድሉ የሰፋ ነው!

ወገኖች ሆይ፣ ‹‹አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ›› እንዲሉ፣ በአገራችን ካለው ካልዳበረው የመግለጥ አገልግሎት የተነሳ በአጠቃላይ የመግለጥ አገልግሎቱን ልናንቋሽሽ አይገባም፡፡ የሰውን ልምድ ከእግዚአብሔር ቃል እውነት ለያይተን መመልከት መቻል ይኖርብናል፡፡ በመግለጥ አገልጋዩ በኩል የአያያዝ ችግር ወይንም ስህተት ቢገኝ፣ ‹‹ከአያያዝ ሊቀደድ…›› መቻሉ ያለና የሚኖር እውነት መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል!

ታውቃላችሁ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊው እውነት ቋሚና ከስህተት ነጻ ሲሆን፣ የሰው ልምድ ግን ተለዋዋጭና ለስህተት የተጋለጠ ነው! ስለሆነም፣ መጽሐፍ ቅዱስን በሰው ልማድ መተርጎም አደገኛ ነው!

ወገኖች ሆይ፣ ልማዳችንን መሠረት በማድረግ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን የምንተረጉም ከሆነ ለስህተት አሰራር ልንጋለጥ እንችላለን፡፡ ከዚህም የተነሳ፣ ለቃሉ ታማኝ ሆኖ በማገልገል ከሚገኘው መለኮታዊ በረከት ሳንካፈል እንቀራለን፡፡ በተጨማሪም፣ ልምምዳችንን ለቃሉ ሥልጣን ባለማስገዛታችን ምክንያት አንድ ቀን በእግዚአብሔር ፊት ምላሽ እንሰጣለን!
-----
ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!

--------------------------------

‹‹የወንጌላዊ እጮኛ›› አዲስ መጽሐፍ፣ በገበያ ላይ ውሏል፡፡ ለተጨማሪ መረጃ በ0911 678158 ወይም 0911 813092 ይደውሉ፡፡

No comments:

Post a Comment