ዲቮሽን
ቁ.127/07 ሐሙስ፣ ጥር 7/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)
እግዚአብሔር ፊርማ ሲቀድድ!
እግዚአብሔር እንዲህ
ይላል፦ ያከበሩኝን አከብራለሁና፥ የናቁኝም ይናቃሉና (1 ሳሙ 2፡30)
እግዚአብሔር በተለያዩ
ጉዳዮች ላይ፣ ከሰው ልጆች ጋር ውል ይመሠርታል፡፡ እግዚአብሔር ከሰው ልጆች ጋር የመሠረተውን ውል በእርሱ በኩል እስከ መጨረሻው
ይጠብቃል፡፡ ሆኖም ውል ተቀባይ የሆነው ግለሰብ ውሉን በሚያፈርስበት ጊዜ፣ እግዚአብሔር የቃል ኪዳን ፊርማውን ይቀድዳል!
እግዚአብሔር ፊርማ ሲቀድድ
ሶስት መሰረታዊ ነገሮችን ያደርጋል! (1ኛ) ውሉን ያፈርሳል፣ (2ኛ) በአጥፊው ግለሰብ ላይ የቅጣት
እርምጃ ይወስዳል፣ (3ኛ) ከእርሱ ጋር ተስማምቶ ሊሠራ የሚችል ሌላ ሰው ለራሱ ያስነሳል
ወገኖች ሆይ፣ በልዩ
ልዩ የአገልግሎት ዘርፎች ጌታን የምናገለግል ሰዎች ከዔሊ ታሪክ የምንማረው ብዙ እውነት አለ፡፡ ዔሊ የታላቁ ካህን የአሮን ቤተሰብ
ነበር፡፡ ለአሮን ቤተሰብ በብሉይ ኪዳን ዘመን የክህነት አገልግሎት ለዘላለም የተሰጠው ቤተሰብ ነው (ዘሌ 7፡35-36)፡፡ ይሁንና
ዔሊ የገዛ ልጆቹን ኮትኩቶ ማሳደግ ያልቻለ ካህን ነበር (1ሳሙ 2፡12)፡፡
ታውቃላችሁ፣ ‹‹የራሷ
እያረረባት የሰው ታማስላለች›› እንዲሉ፣ ካህኑ ዔሊ ከቤቱ ውጭ መላውን የእስራኤልን ሕዝብ ለማገልገል ደፋ ቀና ይላል፣ በቤቱ ውስጥ
ግን ምናምንቴ ልጆች ያሳድጋል፡፡
ወገኖች ሆይ፣ የዔሊ
ክህነት፣ የዔሊ አገልግሎት ለገዛ ልጆች አልጠቀማቸውም፡፡ የእርሱ መንፈሳዊነት የገዛ ልጆቹን መለወጥ አልቻለም፡፡ ስለሆነም ልጆች
ምናምንቴዎች ሆኑ፣ ማለትም ምንም የማይረቡ ክፉዎች ነበሩ!
ታውቃላችሁ፣ ስለ ቤተ
ሰዎቹ የማያስብ ማንም ቢሆን፥ ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው(1ጢሞ 5፡8)!
ወገኖች ሆይ፣ ብዙዎቹ
የኢትዮጵያ አገልጋዮች የዚህ ዓይነቱ አደጋ የተደቀነባቸው ናቸው፡፡ በሀገራችን፣ ብዙዎቹ አገልጋዮች ከቤት ውጭ አርበኞች ናቸው፡፡
ከቤታቸው ውጭ፣ ከሰማይ እሳት የሚያወርዱ፣ ከቤታቸው ውጭ ብዙ ተከታዮች የሚያፈሩ፣ ከቤታቸው ውስጥ ግን ከገዛ ልጆቻቸው የሚከተላቸው
የሌላቸው ሞልተዋል!
ወገኖች ሆይ፣ የዔሊ
ልጆች አፊንና ፍንሐስ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ሲያገለግሉ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ እግዚአብሔርን ሊያገለግሉ ሲገባ፣ አይፈሩትም
ነበር! ምናምንቴዎቹ አገልጋዮች ሚስቶች እያሏቸው፣ በመገናኛው ድንኳን ከሚያገለግሉ ሴቶች ጋር ዝሙት
ይፈጽሙ ነበር፡፡ ይህ ትልቅ ጥፋት፣ እግዚአብሔርን መናቅ ነው!
ወገኖች ሆይ፣ ካህናቱ
የዔሊ ልጆች፣ በማደሪያው ያቀርቡት ዘንድ ጌታ ያዘዛቸውን መሥዋዕቱንና ቍርባኑን ረገጡ!
የሚቃጠል መስዋዕት ከሚያቀርቡ ሰዎች እጅ ስቡ ገና ሳይቃጠል አስገድደው በመውሰድ የጮማ ቁርጥ ይበሉ ነበር፡፡ ከእግዚአብሔር ከልክለው
የሕዝቡን የእስራኤልን ቍርባን ሁሉ ቀድመው እየበሉ ወፈሩ! ይህ ትልቅ ጥፋት፣ እግዚአብሔርንም መናቅ ነው!
ወገኖች ሆይ፣ በዚህ
ዓይነት መንገድ ስላላከበሩትና ስለናቁት እግዚአብሔር ከዔሊ ጋር የተዋዋለውን ውል አፈረሰ፡፡ በዚህም ሳያበቃ፣ ያለ ርህራሄ በሞት
ቀጣቸው፡፡ በዚህም አላበቃም፣ ካህኑን ዔሊንም ያለ ርህራሄ በሞት ቀጣው፡፡
ወገኖች ሆይ፣ የምናገለግለውን
አምላክ እግዚአብሔርን እየፈራነው ነው? ወይስ እየናቅነው? እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ያከበሩኝን አከብራለሁ፥ የናቁኝም ይናቃሉ!
-----
ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!
ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!
--------------------------------
‹‹የወንጌላዊ እጮኛ›› አዲስ መጽሐፍ፣ በገበያ ላይ ውሏል፡፡ ለተጨማሪ መረጃ
በ0911 678158 ወይም 0911 813092 ይደውሉ፡፡
No comments:
Post a Comment