Wednesday, January 14, 2015

ነቢይ ሲሳሳት!

ዲቮሽን .126/07     ረቡዕጥር 6/07 ..
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


ነቢይ ሲሳሳት!

እሴይንና ልጆቹንም ቀደሳቸው፥ ወደ መሥዋዕቱም ጠራቸው። እንዲህም ሆነ በመጡ ጊዜ ወደ ኤልያብ ተመልክቶ። በእውነት እግዚአብሔር የሚቀባው በፊቱ ነው አለ። እግዚአብሔር ግን ሳሙኤልን፦ ፊቱን የቁመቱንም ዘለግታ አትይ ሰው እንዲያይ እግዚአብሔር አያይምና ናቅሁት ሰው ፊትን ያያል፥ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል አለው (1ሳሙ 16፡5-8)

አንዳንዴ እግዚአብሔር የናቀውን ሰው አክብረን፣ እግዚአብሔር ያከበረውን እንንቃለን፡፡
የጣለውን እናነሳለን፣ ያነሳውን እንጥላለን፣ ያጸደቀውን እናረክሳለን፣ ያረከሰውን እናጸድቃለን፡፡

ወገኖች ሆይ፣ የነቢይነት አገልግሎት ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግበት የሚገባው ነው፡፡ ጥንቃቄ ካልተደረገ በስተቀር በነቢይነት አገልግሎት ከፍተኛ አደጋ እናመጣለን፡፡

ወገኖች ሆይ፣ አንዳንዴ ለሰዎች ስንጸልይ የሥጋና የደም እይታችን የመንፈስ ቅዱስን ራዕይ ያደነግዝብናል! ለምሳሌ፣ የምንጸልይላቸው ሰዎች መልካቸው የሚያምር ሲሆን፣ በኑሮ ሀብታሞች ከሆኑ፣ ሰውነታቸው ሞላ ሞላ ያለ እንደሆነ፣ መኖሪያ ቤታቸውን፣ ልብስና ጌጣቸውን ስናይ ጌታ የሚናገረንን አጥርተን ለመስማት አቅም እናጣለን፡፡ ከሰው ግምት ወጥተን፣ ከራስ ምናብ አልፈን የጌታን አድምጠን፣ ታዝዘን ለመናገር ድፍረት እናጣለን፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ወይም ከጫፍ እስከ ጫፍ ያለው መላው የእስራኤል ሕዝብ የሚያከብረውና የሚያምነው እንዲሁም ከአፉ አንድም ቃል ከመሬት ጠብ የማይለው ነቢዩ ሳሙኤል ከስህተቶችም ሁሉ ጭልጥ ያለ ስህተት ጭልጥ ብሎ ተሳሳተ! የኤልያብን ቁመና፣ የቁመቱን ዘለግታ፣ ውጫዊ ምልከታ አየና፣ ሳሙኤል ተሳሳተ!

ታውቃላችሁ፣ ነቢዩ ሳሙኤል፣ ያልተለየውን ሰው ተለይተሃል አለ፣ ያልተመረጠውን ተመርጠሃል አለ! እግዚአብሔር ሲናገር ያላዳመጠውን፣ እርግጠኛ ሆኖ መናገር ጀመረ! ከሰማይ ተገልጦ ያልተመለከተውን በራሱ ማስተዋል እርግጠኛ ሆኖ መተረክ ጀመረ! የገዛ ራሱን ድምጽ ራሱ በማዳመጥ፣ በሥጋ ዓይኖቹ የተመለከተውን፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብሎ ተናገረ!

ታውቃላችሁ፣ ነቢይ ሲሳሳት አያድርስ ነው! ጌታ ያላለውን፣ ‹‹የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል›› ማለት በጣም አደገኛ ነው! ያላዩትን ‹‹አየሁ››፣ ያልሰሙትን ‹‹ሰማሁ›› ማለት ከባድ አደጋ ነው!

 -----
ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!

--------------------------------

‹‹የወንጌላዊ እጮኛ›› አዲስ መጽሐፍ፣ በገበያ ላይ ውሏል፡፡ ለተጨማሪ መረጃ በ0911 678158 ወይም 0911 813092 ይደውሉ፡፡

No comments:

Post a Comment