Saturday, January 3, 2015

የሙሉጊዜ አገልጋዮች ክፍያ – በኢትዮጵያ! 7

ዲቮሽን .115/07     ቅዳሜ ታህሳስ 25/07 ..
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


ሙሉጊዜ አገልጋዮች ክፍያ – በኢትዮጵያ! 7

ነገር ግን አሁን ከጊዜ በኋላ ስለ እኔ እንደ ገና ልታስቡ ስለ ጀመራችሁ፥ በጌታ እጅግ ደስ ይለኛል፤ ጊዜ አጣችሁ እንጂ፥ ማሰብስ ታስቡ ነበር። …የፊልጵስዩስ ሰዎች ሆይ፥ ወንጌል በመጀመሪያ ሲሰበክ፥ ከመቄዶንያ በወጣሁ ጊዜ፥ ከእናንተ ብቻ በቀር ሌላ ቤተ ክርስቲያን በመስጠትና በመቀበል ስሌት ከእኔ ጋር እንዳልተካፈለች እናንተ ደግሞ ታውቃላችሁ (ፊል 4፡10-15)

ዘርፉ ደርሶ ስሜታዊ ሆነ! የየውብዳር አምሳለን ጨዋታ አቋርጦ በመግባት አትጠገብ ላይ አፈጠጠና፡-

<<ቃሉ ሲናገር <አንዳንዶቹ ሐዋርያት፥ ሌሎቹም ነቢያት፥ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፥ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ለቤተክርስቲያን ሰጠ> ይላል፡፡ ሚስጥሩ ገብቶሻል? በቃ እኛ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች እንደ ምርኮኛ ለቤተክርስቲያን የተሰጠን ምርኮኛ ሠራዊት ነን፡፡>> ማለት ነው፡፡

<<ምርኮኛ የተሰጠውን ጉርሻ አመስግኖ ከመቀበል ሌላ ምን ሊያመጣ ይችላል? አጥቢያዎች ትኩረታቸው በሕንጻ ግንባታ ላይ፣ በ<ሳውንድ ሲስተም> ላይ፣ በኮንፍራንስ ላይ፣ በመዘምራን ዩኒፎርም ላይ ሲሆን ስለምርኮኞቹ ኑሮ ማሻሻያ ግን አያስቡም፡፡>>

<<በዚህ ጉዳይ ሐዋሪያ ጳውሎስ ለቆሮንቶሳዊያን በ1ቆሮ 4፡8-13 ላይ አንጀት በሚያቃጥል ቋንቋ ጽፎላቸው ነበር፡፡ <አቤት የጥጋባችሁ ብዛት፣ እኛ ባሳየናችሁ መንገድ ገብታችሁ፣ እኛን ጥላችሁ ለብቻችሁ መንገሳችሁ! ምናለበት እኛም አብረናችሁ ብንደሰት?> ይላቸዋል፡፡>>

<<ለዓለምና ለሰዎች መጫወቻ ሆነን ቀረን እኮ! ይላቸዋል፡፡ እግዚአብሔር እኛን የሞት ፍርድ የፈረደብን ያህል የኋለኞች ሆነን ቀረን እኮ! እኛ ሞኞች፣ እናንተ ግን ብልጦች ሆናችሁ፡፡ እኛ ደካሞች፣ እናንተ ግን ኃይለኞች፤ እኛ የተዋረድን፣ እናንተ ግን የከበራችሁ ሆናችሁ። እኛ እስከዚህ ሰዓት ድረስ እንራባለን፥ እንጠማለን፥ እንራቆታለን፥ እንጐሰማለን፥ እንንከራተታለን፥ የዓለም ጥራጊ፣ የሁሉም ጉድፍ ሆነናል> ይላል!!>>

ዘርፉ ፊቱን ወደ የውብዳር አምሳለ በማዞር አፈጠጠባት!

<<ቆሮንቶሳዊያን ይህን መልዕክት በምን አንጀታቸው ችለው ይሆን ያነበቡት? አቤት ጌታ ሆይ፡፡ የእኛዎቹ የአንጋፋ አብያተክርስቲያናት ቆሮንቶሳዊያን ደግሞ ከዚህ ብሰዋል! የኛዎቹ ቆሮንቶሳዊያን መሪዎች አንጀታቸው ለሙሉ ጊዜ አገልጋዮች የተዘጋ ነው! ሕዝባችንም በመሪዎቻችን ወጥቶ <አሳሰበኝ> ማለትን አያውቅም፡፡ እንዲያውም ብዙ ጊዜ እኛ አገልጋዮች ነን፣ ከእኛም ለባሰባቸው የሚያሳስበን፡፡

ዘርፉ ስሜቱ እየነዳው ነው! ስለሆነም የቀኝ እግር ጫማውን አውልቆና ጫማው ላይ አፍጥጦ፣ <<ለማገልገል ስንቆም ሰዉ መልዕክታችንን ትቶ፣ ጫማችንን የሚያዳምጥ ይመስል እግር እግራችንን ያያል፡፡ አንድ ጊዜ አንድ አገልጋይ በማታው አገልግሎት ላይ ሲቆም ጫማው ከታች ተተርትሮ ኖሮ ጉዱን አላወቀውም፡፡  ከጉባኤው መካከል አንዱ ዓይኑን ጫማው ላይ ተክሎ መንቀል ሲያቅተው አስተዋለ፡፡ አገልጋዩም ያው የተለመደ እይታ መስሎት ቁብ አላለውም ነበር፡፡>>

<<አገልግሎቱን ጨርሶ ወደ ቤቱ ገብቶ ጫማውን ሊያወልቅ ጎንበስ ሲል ጉድ መሆኑን ያወቀው ያኔ ነው፡፡ በርግጥ ጌታ ለአዕምሮው ተጠንቅቆለት ስለነበር በአገልግሎቱ ወቅት ጫማውን ጎንበስ ብሎ እንዳያይ አድርጎት ነበር፡፡ አለበለዚያ ደንግጦ ማገልገል ያቅተው ነበር፡፡ ሕዝባችን ኢላማ ላለመሳት ድብ አንበሳ ላይ እንደሚያነጣጥር አዳኝ፣ በአገልጋዮች ጫማ ላይ ከማፍጠጥ ምንአለ በገንዘብ ቦርሳቸው ላይ ቢያፈጥጡና ለጫማ መግዣ የሚሆን ሳንቲም ቢሰጡ! ማፍጠጥ ብቻ!>> … (ምንጭ፣ የወንጌላዊው እጮኛ፣ ገጽ 70-71 የተቀነጨበ)

(ለቅምሻ ያህል 7 ዲቮሽኖች ከአዲሱ መጽሐፌ ቆርሼ አቅርቤላችኋለሁ፡፡ ሙሉ መጽሐፉን ከመጻሕፍት መደብሮች ገዝተው ያንብቡ፡፡ ጌታ ቢፈቅድ ከነገ ጀምሮ በሌላ ርዕስ እንገናኛለን፡፡ ጌታ ይባርካችሁ፡፡)

የመጽሐፉ ዋጋ 40 ብር ነው፡፡ በአዲስ አበባ የምትገኙ ወገኖች መጽሐፉ ያሉበት ድረስ እንዲመጣላችሁ ከፈለጋችሁ፣ በ0911 678158 ወይም 0911 813092 ይደውሉ፣ በሰዓታት ውስጥ ይመጣላችኋል፣ ነገር ግን ለትራንስፖርት 10 ብር ጭማሪ ይከፍላሉ፡፡ በውጭው ዓለም የምናየው የሚፈልጉትን ነገር ያሉበት ድረስ ደውሎ የማግኘት ባህል በእኛም ሀገር የማይሆንበት ምንም ምክንያት የለም፡፡
--------------------------------
‹‹የወንጌላዊ እጮኛ›› በሺዎች የተደነቀ ልብ አንጠልጣይ መጽሐፍ፣ ፒያሳ ከሚገኘው በእምነት መጻሕፍት መደብር ፒያሳ፣ በራዕይ መጻሕፍት መደብሮች፣ መካነየሱስ መጻሕፍት መደብር፣ የምሥራች ድምጽ መጻሕፍት መደብሮች፣ መሠረተክርስቶስ መዝሙር ቤት ስቴዲዮም ያገኛሉ፡፡


No comments:

Post a Comment