ዲቮሽን
ቁ.114/07 አርብ፣ ታህሳስ 24/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)
የሙሉጊዜ አገልጋዮች ክፍያ – በኢትዮጵያ! 6
ነገር ግን አሁን ከጊዜ በኋላ ስለ እኔ እንደ ገና ልታስቡ ስለ
ጀመራችሁ፥ በጌታ እጅግ ደስ ይለኛል፤ ጊዜ አጣችሁ እንጂ፥ ማሰብስ ታስቡ ነበር። …የፊልጵስዩስ ሰዎች ሆይ፥ ወንጌል በመጀመሪያ
ሲሰበክ፥ ከመቄዶንያ በወጣሁ ጊዜ፥ ከእናንተ ብቻ በቀር ሌላ ቤተ ክርስቲያን በመስጠትና በመቀበል ስሌት ከእኔ ጋር እንዳልተካፈለች
እናንተ ደግሞ ታውቃላችሁ (ፊል 4፡10-15)
<<ሌላዋ የአገልጋይ
ሚስት በትዳር 30 ዓመት ያህል ቆይታለች፡፡ የትምህርት ደረጃዋ 6ኛ ሲሆን ለባልዋ 8 ልጆች ወልዳለታለች፡፡ የአገልጋዩ የወር ገቢ
1400 ብር ነው፡፡ ነገር ግን በመልካም ጊዜ የወለዱት የመጀመሪያ ልጃቸው ጥሩ ሥራ ስለያዘ ጥሩ ይደጉማቸዋል፡፡ አገልጋዩ በመንፈሳዊ
ሕይወቷ ስላሳደጋት ባሏን እንደ አባቷ ነው የምታየው፡፡ ቀደም ባሉት ዘመናት አንዳቸው ለሌላቸው ጥልቅ ፍቅር ስለነበራቸው፣ የሚያውቋቸው
ሰዎች ሁሉ <ፍቅር አያረጅም> የሚል ቅጽል ስም ሰጥተዋቸዋል፡፡>>
<<ከቅርብ ጊዜ
ወዲህ ግን፣ ሰውዬው ከቤተሰቡ ይልቅ አገልግሎት ያስቀድማል፡፡ በቤተክርስቲያን ሥራ ምክንያት ቤተሰቡን ጥሏል፡፡ የራሱንም ሆነ የቤተሰቡን
ሕይወት አይንከባከብም፡፡ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰበት ነው፡፡ ልጆቹም ስለእርሱ ሲናገሩ፣ <ለኛ ጊዜ የለውም፣ ሁልጊዜ አምሽቶ ይገባል፡፡ ወደቤት ሲመጣ ደግሞ የሆነ ያልሆነ ሥራ እንድንሠራ
ያዝዘናል፡፡ እኛ ደግሞ ስለሚደክመን አንግባባም፡፡ ከዚህም የተነሳ በእኛ ያዝናል፡፡ የማንታዘዝ ልጆች አድርጎ ይቆጥረናል> በማለት ሐዘናቸውን ገልጸዋል፡፡>>
<<የሁለት ልጆች
እናት የሆነች ሌላዋ የአገልጋይ ሚስት ደግሞ እጅግ ዝቅተኛ ኑሮ እንደሚኖሩ ከመናገሯም ባሻገር፣ <ባሌ የፍቅር ሕይወት በይፋ አይሰጠንም፡፡ ጊዜ የሚባል ነገር ጨርሶ የለውም፡፡ ዝምተኛነት ያጠቃዋል፡፡
ልጆቹ እንኳ በግድ ነው የሚያናግሩት፡፡ ቤቱን በመንፈሳዊ ነገር አያገለግልም፡፡ ባሌ ፍቅር ሊሰጠንና፣ ቤተሰቡንም ሊያገለግል ይገባል
ብዬ አምናለሁ፡፡ ሁልጊዜ ተጨንቀን መኖር የለብንም፡፡ መለወጥ አለብን፡፡ ከኑሮ ጫና የተነሳ ለእግዚአብሔር መኖር አልቻልኩም፡፡
በዚህም ምክንያት የሕሊና ወቀሳ አለብኝ፡፡ የአገልጋይ ሚስቶች ለቤተሰባችን ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኝ ሥራ በመሥራት ደስተኛ ኑሮ መኖር
አለብን> ስትል ተናግራለች፡፡>>
<<ሌላዋ የአገልጋይ
ሚስት በትዳር ሕይወት ለ14 ዓመት የቆየችና የ3 ልጆች እናት የሆነች የቤት እመቤት ነች፡፡ ያለችበትን ሁኔታ በሐዘን ስትናገር
<አገልጋይ ማግባት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ቀድሜ
ባውቀው ኖሮ፣ ሥራውን ትቶ ሙሉ ጊዜውን ለአገልግሎት ሲሰጥ፣ ቤቴን ጥዬ እወጣ ነበር፡፡ በርግጥ እግዚአብሔር ጅማሬንና ፍጻሜን እንጂ
በመካከሉ ያለውን ጉዞና ውጣ ውረድ አያሳይምና፣ በጸጋ ተቀብዬዋለሁ>> ትላለች፡፡
<<ሌላዋ የአገልጋይ
ሚስት ስትናገር <<ባለቤቴ በየዕለቱ በስራ ይወጣጠራል፡፡ ለቤተሰቡ
ጊዜ የለውም፡፡ ልጆቹን የሚያገኛቸው በቀናት ውስጥ ነው፡፡ ችግሮች ሲደርሱበት አይነግረኝም፡፡ የምሰማው ከሌላ ሰው በወሬ ወሬ ደረጃ
ነው እንጂ በቀጥታ አያማክረኝም፡፡ ሁለቱን ልጆቼን ጌታ ሸክም የሰጣቸው ሰዎች ያስተምሩልኛል፡፡ የባለቤቴ ገቢ እዚህ ግባ የሚባል
አይደለም፡፡>>
<<የዚህ አገልጋይ
የ19 ዓመቷ ሴት ልጅ ስትናገር <አባቴ ለእኛና ለእናታችን ያለው ፍቅር ደስ ይለኛል፡፡
ግን እናቴ ሁልጊዜ ስትሰቃይ ስለማይ ሳድግ እንደ አባቴ ሙሉ ጊዜዬን ለአገልግሎት አልሰጥም፡፡ አገልጋይም አላገባም፡፡ ግን የዝማሬ
ጸጋ ስላለኝ ጌታን በዝማሬ የማገልገል ፍቅር አለኝ> ትላለች፡፡>>
<<ሌላዋ የአገልጋይ
ሚስት፣ የኮሌጅ ዲፕሎማ ያላት ሲሆን 15 ዓመት በጋብቻ አሳልፋለች፡፡ በአንድ የግል ድርጅት ውስጥ በኃላፊነት ትሠራለች፡፡ ስለባሏ
ስትናገር የሚቀበለውን ለድሆች እየሰጠ ቤተሰቡን ይጎዳል፡፡ ለኛ ፈጽሞ ጊዜ አይሰጠንም፡፡ መማር እየፈለግን አያስተምረንም፡፡ እቤት
ሲመጣ ሁሌ ዝምተኛ ነው፡፡ ለቤቱ እንደ እንግዳ ነው፡፡ በዚህም ልቤ በጣም ያዝናል፡፡>>
<<ባሎች ሰፊውን
ጊዜ ለሚስቶቻቸው ቢሰጡ፣ አብረው መጸለይና ከቃሉ መማማር ቢችሉ ጥሩ ነው፡፡ ልጆቻችንን የምናስተምረው በማይረባ ትምህርት ቤት ውስጥ
ነው፡፡ ለውጥ ያስፈልገናል፡፡ አገልጋዮች በቂ መተዳደሪያ ሳይኖራቸው በእምነት ብቻ ትዳር ባይመሠርቱ መልካም ነው፡፡ አገልጋዮችም
እጮኞቻቸው ምርጫቸውን ከጠዋቱ እንዲያስተካክሉ አገልጋይነት የሚያስከፍለውን ዋጋ መናገር አለባቸው፡፡ ጥሩ ውሳኔ ማድረግ እንዲችሉ
ሁሉን ነገር በግልጽ መናገር አለባቸው> ትላለች፡፡>> … (ምንጭ፣ የወንጌላዊው እጮኛ፣ ገጽ 80-81 የተቀነጨበ)
--------------------------------
‹‹የወንጌላዊ እጮኛ›› በሺዎች የተደነቀ ልብ አንጠልጣይ መጽሐፍ፣ ፒያሳ ከሚገኘው
በእምነት መጻሕፍት መደብር ፒያሳ፣ በራዕይ መጻሕፍት መደብሮች፣ መካነየሱስ መጻሕፍት መደብር፣ የምሥራች ድምጽ መጻሕፍት
መደብሮች፣ መሠረተክርስቶስ መዝሙር ቤት ስቴዲዮም ያገኛሉ፡፡
No comments:
Post a Comment