ዲቮሽን
ቁ.113/07 ሐሙስ፣ ታህሳስ 23/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)
የሙሉጊዜ አገልጋዮች ክፍያ – በኢትዮጵያ! 5
ነገር ግን አሁን ከጊዜ በኋላ ስለ እኔ እንደ ገና ልታስቡ ስለ
ጀመራችሁ፥ በጌታ እጅግ ደስ ይለኛል፤ ጊዜ አጣችሁ እንጂ፥ ማሰብስ ታስቡ ነበር። …የፊልጵስዩስ ሰዎች ሆይ፥ ወንጌል በመጀመሪያ
ሲሰበክ፥ ከመቄዶንያ በወጣሁ ጊዜ፥ ከእናንተ ብቻ በቀር ሌላ ቤተ ክርስቲያን በመስጠትና በመቀበል ስሌት ከእኔ ጋር እንዳልተካፈለች
እናንተ ደግሞ ታውቃላችሁ (ፊል 4፡10-15)
<<በአንዲት አጥቢያ
ውስጥ የምታገለግል በቅርብ የማውቃት አገልጋይ አለች፡፡ ዕድሜዋ 35 ሲሆን 12ኛ ያጠናቀቀች፣ ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት ነች፡፡
በአገልግሎት የአንድ ዓመት ልምድ አላት፡፡ የእርስዋና የባሏ የወር ገቢ 6000 ብር ነው፡፡ ለቤት ኪራይ 2000 ብር ታወጣለች፡፡
<<ሴት አገልጋዮች
ደህና ወርሃዊ ገቢ ያለውን ባል የማግባት ዕድል ካጋጠማቸው ጥሩ ኑሮ መኖር ይችላሉ፡፡ ወንዶቹ አገልጋዮች ግን በድህነታቸው ምክንያት
ወይ በዕድሜ የገፉ ወይ <ዲያስፖራ> ወይ <ላሜቦራ> ሴቶች ካላገቧቸው በስተቀር እዚህ አገር በሚኖሩ ወጣት ሴቶች ብዙም አይመረጡም፡፡>>
ዘርፉ ጣልቃ ገብቶ <<ሴቶች ጥሩ ትዳር የሚመሠርቱት እያስፈራሩ ነዋ! ጌታ አንተን ለኔ ሰጥቶኛል እያሉ>> በማለት ሳቀ፡፡
<<በዚህ በዚህ
እንኳ ወንዶቹ ይብሳሉ>> አለች የውብዳር አምሳለ፡፡ የሆነ ነገር ትዝ ብሏት
ከት ብላ ሳቀችና፣ ያሳቃትን ነገር ታጫውታቸው ጀመር፡፡
<<ከመልክ፣ ከቁመና፣ ከንግግር፣ ከትምህርት ወይም ከሌላ ምንም ነገር የሌለው ከባላገር የመጣ
ድሃ አገልጋይ ነበር፡፡ አገልጋዩ ቆሞ ሲያገለግልም ሆነ ተቀምጦ ሲያወራ ለዛ ቢስ ነው፡፡ በሁኔታው ያዘኑለት ሰዎች ጃኬት፣ ሱሪ
ወይም ኮት ቢሰጡት፣ በሄደበት ቦታ ሁሉ ስለልብሱ ያወራል፡፡ ቆሞ ሲያገለግልም ስለሰጪው ቸርነት፣ ስለልብሱ ጥራት ያወራል፡፡ ሲያወራ
ሰው ምን ይለኛል አይልም፡፡ የሚሰሙትም ሁሉ ፈገግ ይሉበታል፣ ጓደኞቹ
ሁሉ ይሳቀቁበታል፡፡>>
<<ግን የሚገርም
ነገር ሆነ፡፡ ባንክ ውስጥ የምትሠራ የሒሳብ ባለሙያ፣ በመልኳና በቁንጅናዋ ሞናሊዛ የሆነች ሴት ወደደችው፡፡ ወድዳም አልቀረችም፣
ጠቅልላ አገባችው፡፡ ይህ ሲሆን ታዲያ፣ ድሮ ይስቁበት የነበሩ ጓደኞቹ እንዲህ አሉ፡- <አምላክ ሆይ፣ ተደናግራ የምትወደንና የምታገባንን፣
እንደዚህች ዓይነት ሴት አደናግረህ ስጠን፡፡>>
<<ድሃ አገልጋዮች
ቢጤያቸውን ፈልገው ካላገቡ በስተቀር ድሃ አፍቅራ የምታገባ ከሺህ አንድ ሴት ብትገኝ ነው፡፡ ያቺም ብትሆን ወይ የእምነት ጀግና፣
ወይም የትዳር ጊዜዋ ያለፈባትና ተስፋ የቆረጠች መሆን አለባት፡፡ አሊያም የባሰባት ድሃ ወይም የተደናገረች መሆን አለባት፡፡ ከነዚህ
ሁኔታዎች ውጭ በጤናማው ዓለም ሴቶች በአገልጋዮች ሲጠየቁ ፈቃደኛ አይሆኑም፡፡>>
<<ባንድ በኩል
ሴቶቹ እውነታቸውን ነው፡፡ በምን ዕዳቸው በረሃብ ይጠበሱ! ከዚህም የተነሳ በኑሮ የተጨቆኑ ወንድ አገልጋዮች ትዳር ለመመሥረት ይቸገራሉ፡፡
ወይንም ያለምርጫቸው በዕድሜ ከማይመጣጠኑ፣ በእውቀት ከማይቀራረቡ ሴቶች ጋር አላቻ ጋብቻ ለመመሥረት ይገደዳሉ፡፡>>
<<ወንዶቹ አገልጋዮች
ድሃ ሴት ሲያገኙ፣ አማራጭ እየፈለጉ ቶሎ አያገቡም፣ ደህና ሲያገኙ ደግሞ ፋታ ነስተውና አዋክበው ቶሎ ያገባሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ
በዚህም በዚያም ሞክረው ስላልተሳካላቸው ለሥነልቦናና የሞራል ውድቀት ተዳርገዋል፡፡ የሚያውቅላቸውም የለም!>>
<<ብዙ አገልጋዮች
ተከራይተው የሚኖሩት ከቆሻሻ ሰፈር፣ የተጣለ መንደር፣ ኩሽና አጠገብ፣ መጸዳጃ ቤት አጠገብ ነው፡፡ የተሻለ ነው ሲባል ደግሞ መኖሪያቸው
በጠባብ ሰርቪስ ውስጥ ተጨናንቆ ነው፡፡ እርሷም ቤት ሆና፣ ለቤት ኪራይ የሚሆን ገንዘብ ለማግኘት ቀንና ማታ ማሰብ፣ መጨነቅ፣ አያሌ
ቀንም ያለምግብ በጾምና በጸሎት በማሳለፍ መክሳት የአገልጋይነት መታወቂያ ሆኗል፡፡>> …
(ምንጭ፣ የወንጌላዊው እጮኛ፣ ገጽ 65-67 የተቀነጨበ)
--------------------------------
‹‹የወንጌላዊ እጮኛ›› በሺዎች የተደነቀ ልብ አንጠልጣይ መጽሐፍ፣ ፒያሳ ከሚገኘው
በእምነት መጻሕፍት መደብር ፒያሳ፣ በራዕይ መጻሕፍት መደብሮች፣ መካነየሱስ መጻሕፍት መደብር፣ የምሥራች ድምጽ መጻሕፍት
መደብሮች፣ መሠረተክረስቶስ መዝሙር ቤት ስቴዲዮም ያገኛሉ፡፡
No comments:
Post a Comment