ዲቮሽን
ቁ.130/07 እሁድ፣ ጥር 10/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)
የመግለጥ – አገልግሎት (#2)!
አሁን ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ወደ እናንተ መጥቼ በልሳኖች ብናገር፥ በመግለጥ
ወይም በእውቀት ወይም በትንቢት ወይም በትምህርት ካልነገርኋችሁ ምን እጠቅማችኋለሁ?(1ቆሮ 14፡6)፣ … ደግሞ የወንጌልን ምሥጢር
በግልጥ እንዳስታውቅ አፌን በመክፈት ቃል ይሰጠኝ ዘንድ ስለ እኔ ለምኑ፤ ስለ ወንጌልም በሰንሰለት መልእክተኛ የሆንሁ፥ መናገር
እንደሚገባኝ ስለ እርሱ በግልጥ እናገር ዘንድ ለምኑ (ኤፌ 6፡19-20)፡፡
ከላይ የተጠቀሱ የመግለጥ ዓይነቶች ሁለት ናቸው፡፡ (1ኛው) ‹‹የወንጌል
ምስጢር›› ሲሆን ይህም፣ ነባራዊ የሆነውን የወንጌልን ምስጢር ተርትሮ የመስበክን ወይም የማስተማርን ብቃት ያመለክታል፡፡ (2ኛው)
‹‹የእግዚአብሔር ምስጢር›› ሲሆን ይህም ቅጽበታዊ የሆነውን እግዚአብሔር ለሕዝቡ የሚገልጠውን ምስጢር ተረድቶ ለሰው የማስተላለፍ
ችሎታን ያመለክታል፡፡
ወገኖች ሆይ፣ የመግለጥ አገልግሎት በተፈጥሮው ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ
ነው! ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ ካልተደረገበት አገልግሎቱ በቀላሉ ለስህተት የመጋለጥ
ዕድሉ የሰፋ ነው! ለምሳሌ፣ በ1ኛ ሳሙኤል 16፡6 ላይ ነቢዩ ሳሙኤል ለንጉሥነት ውድድር
እጩ ሆነው ከቀረቡ ስድስት የእሴይ ልጆች መካከል ቁመተ ረዥሙና መልከ መልካሙ ኤልያብ የባለመግለጡን የሳሙኤልን ቀልብ አሸንፎ ነበር፡፡
ከዚህም የተነሳ ‹‹በእግዚአብሔር ፊት የቆመው ይህ ሰው በእርግጥ ለንጉሥነት የተመረጠ ነው›› ብሎ እስከማሰብ ደርሷል፡፡
እግዚአብሔር ግን ‹‹የለም፣ ነገሩ አንተ እንዳልከው አይደለም›› በማለት
የሳሙኤልን አመለካከት ሻረ፡፡ እግዚአብሔር ለንጉሥነት የመረጠው ዳዊት ከነቢዩ እይታ ውጭ ብቻ ሳይሆን ከአባቱም እይታ ውጭ ነበር፡፡
ወገኖች ሆይ፣ ባለመግለጥ ራዕዩን ከራሱ ክልልና ምልከታ አውጥቶ ከእግዚአብሔር
ፈቃድ ሥር ማኖር ይጠበቅበታል፡፡ የሚመለከታቸውን ነባራዊ ክስተቶች ለጊዜው ችላ በማለት አስቀድሞ የጌታን ሐሳብ ለማወቅ መጣር ይኖርበታል፡፡
ባለራዕይ በፊቱ የቀረቡ ሁናቴዎችን በማገናዘብ የራሱን ድምዳሜ ለመስጠት ከሞከረ ብዙ ነገር ያበላሻል፡፡
ወገኖች ሆይ፣ ሐዋርያ ጴጥሮስን አስቡ(የሐዋ 10፡9-14)፡፡ ሐዋርያ ጴጥሮስ
ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ራዕይ(መገለጥ) በራሱ መንገድ በመተርጎም የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ደርሶ ነበር!
ነገሩ እንዲህ ነው፣ ሐዋርያ ጴጥሮስ ሲጸልይ ቆይቶ ይርበውና የሚበላ ይፈልግ ነበር፡፡ የሚበላ በሚፈልግ ሰው ስሜት ውስጥ የምግብ
ፍላጎቱ በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል፡፡
ወገኖች ሆይ፣ የረሀቡ ጉልበት እየበረታ ካልሄደና፣ አማራጭ ካልጠፋ በቀር
የተራበ ሰው ጥሩ አይነት ምግብ ይፈልጋል፡፡ በዚህ ዓይነት ጊዜ ላይ ነው፣ ጴጥሮስ ከወግና ባህል ያፈነገጡ አጸያፊ ምግቦችን በራዕይ
የተመለከተው፡፡ ይህም ሳያንስ ‹‹ጴጥሮስ ሆይ ተነሳና አርደህ ብላ›› የሚል ድምጽ ሰማ፡፡
ወገኖች ሆይ፣ የሐዋርያ ጴጥሮስ ወቅታዊ ስሜት ሙሉ በሙሉ በምግብ ላይ ያተኮረ
ስለነበር ራዕዩን በራሱ መንገድ ተረጎመ፡፡ የራዕዩ መልዕክት ምን እንደሆነ ከጌታ ጠይቆ ለመረዳት ጥረት አላደረገም፡፡ ነገር ግን
ራዕዩን በራሱ መንገድ ለመተርጎም ፈጠነ፡፡ ስለሆነም፣ ‹‹ጌታ ሆይ፣ ይህማ አይሆንም!
እኔ ያልተቀደሰ ወይም ርኩስ ነገር ፈጽሞ በልቼ አላውቅምና››(ቁ.14) ብሎ ምግቡን እንደማይሞክረው ከራሱ ድምዳሜ ላይ ደረሰ፡፡
ወገኖች ሆይ፣ ከጌታ የተሰጠው ምላሽ ግን፣ ከእርሱ ውሳኔ የሚቃረን ነበር፣
‹‹እግዚአብሔር ንጹህ ያደረገውን አንተ እንደ እርኩስ አትቁጠረው›› (ቁ.14) የሚል፡፡ በጴጥሮስ ወግና ባህል መሠረት አሕዛብ
እንደ ርኩሳን ይቆጠሩ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ለጴጥሮስ በሰጠው መገለጥ ውስጥ ሊያስተላልፍ የፈለገው ግልጽ መልዕክት አሕዛብን እግዚአብሔር
እንደተቀበላቸው የሚያመለክት ነበር፡፡ ሐዋርያው በወቅቱ ያልገባው መልዕክት ይኼ ነው!
ጌታ እግዚአብሔር ከአሕዛብ ወገን የሆነውን ቆርኔሌዎስን ወደ መንግሥቱ መቀበሉን
ለጴጥሮስ በሰጠው መገለጥ ሊያስረዳው ፈልጓል፡፡የሐዋርያው ባህልና ልምድ ግን ይህ አይነቱን ነገር አምኖ ለመቀበል የተዘጋጀ አይደለም፡፡
አንድ አይሁዳዊ ከሌላ ወገን እነዲተባበር ወይም እንዲቀራረብ ሕጋቸው አይፈቅድም(የሐዋ 10፡28)፡፡ አይሁዳዊያን አሕዛብን እንደ
ርኩሳን ይቆጥሯቸዋል፡፡ ነገር ግን ጴጥሮስ ማንንም ርኩስ ወይም ያልተቀደሰ ነው እንዳይል እግዚአብሔር አሳይቶታል(ቁ.28)፡፡
ወገኖች ሆይ፣ የመግለጥ አገልጋዮች በተመሳሳይ ሁኔታ ስህተት ውስጥ ሊወድቁ
ይችላሉ፡፡ አገልጋዮቹ ተጋልጋዮቹን የሚመለከቱበት የራሳቸው መነጽር ይኖራቸዋል፡፡ ተገልጋዩም አገልጋዩን የሚመለከትበት የራሱ የሆነ
ሌላ መነጽር ይኖረዋል፡፡ ብዙ ጊዜ ግን ሁለቱም ወገኖች ሶስተኛውን ባለመነጽር፣ ያውም እግዚአብሔርን የመዘንጋታቸው ነገር ይኖራል፡፡(ተፈጸመ)
-----
ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!
ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!
--------------------------------
‹‹የወንጌላዊ እጮኛ›› አዲስ መጽሐፍ፣ በገበያ ላይ ውሏል፡፡ ለተጨማሪ መረጃ
በ0911 678158 ወይም 0911 813092 ይደውሉ፡፡
No comments:
Post a Comment