ዲቮሽን ቁ.93/07 አርብ፣ ታህሳስ 3/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)
መሪዎችና ጸሎት!
ለዘሩባቤል የተባለው የእግዚአብሔር ቃል
ይህ ነው። በመንፈሴ እንጂ በኃይልና በብርታት አይደለም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር(ዘካ 4፡6)
የታላቅ መሪነት መለኪያው የጸሎት ሕይወት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ የምናውቃቸው ታላላቅ መሪዎች የጸሎት ሰዎች ናቸው፡፡
የእነዚህ ታላላቅ መሪዎች የታላቅነት ምስጢር (1) ያለ እግዚአብሔር ምንም ማድረግ እንደማይችሉ በመረዳታቸው (ዮሐ 15፡5)፣ (2) የአመራር ጥበብ
ምንጩ እግዚአብሔር መሆኑን በማወቃቸው (ያዕ
1፡5)፣ (3) የሚያስጨንቃቸውን ሁሉ
በእግዚአብሔር ላይ በመጣላቸው
ነው (ዮሐ 5፡7)፡፡
መሪዎች ሆይ፣ ለዘሩባቤል የተባለውን የእግዚአብሔርን
ቃል አስቡ! በመንፈሱ እንጂ በኃይል በብርታታችን መምራት አንችልም፡፡ ሰው በኃይሉ አይበረታምና፣ ያለ ጌታ እርዳታ የአመራር ፍልስፍናችን፣
የማስፈጸም ስልታችን ፈጽሞ አይሠራም!
መሪዎች ሆይ፣ የፍቅርን ማሠሪያ አሽቀንጥረን
ጥለን፣ በጥል–በጦርነት፣ በግጭት–በፍጭት የእግዚአብሔርን ሕዝብ ልንመራ አንችልም፡፡ ተንበርክከን እንጂ ቆመን በመሟገት ጌታን አናክብርም፡፡
የእግዚአብሔር ድምጽ ሲጸልዩ እንጂ ሲጨቃጨቁ አይሰማም፡፡
መሪዎች ሆይ፣ በስብሰባዎቻችን ብዙ እንመኛለን፣
ለእኛ ግን አይሆንም፡፡ በብርቱ እንፈልጋለን፣ በብርቱ እንሻለን፣ ማግኘት ግን አንችልም፡፡ ብዙ እንጣላለን፣ ብዙ እንዋጋለን፡፡
አንለምንምና ለእኛ ግን አይሆንም!
መሪዎች ሆይ፣ የክፋት አጀንዳ በፋይላችን
ይዘን፣ የጥፋት ውሳኔ ውስጣችን አርግዘን፣ ያልተቀደሱ እጆች ለጸሎት አንስተን፣ ሺህ ጊዜ ሺህ ጸሎት፣ እልፍ ጊዜ እልፍ ልፋት ቢኖር
ጌታ አይሰማንም፡፡ ባልተቀደሰ ሞቲቭ፣ ባልተፈወሰ ሐሳብ ሺህ ጊዜ ሺህ ስብሰባ፣ እልፍ ጊዜ እልፍ ልፍለፋ ቢናደርግ ጌታ አይከብርበትም፡፡
መሪዎች ሆይ፣ ጸሎትና ቃሉን ትተን ማዕድን
ማገልገላችን፣ ታላቁን ተልዕኮ ትተን በሕንጻ ግንባታ ጊዜ ማጥፋታችን ሊታረም ይገባል፡፡ ለዳኑ ነፍሳት ደቀመዝሙርነትን፣ ለጠፉ ነፍሳትም
ወንጌል ሥርጭትን የማድረጉን ሥራ ወደጎን አድርገን፣ ትውልድ እየጠፋ፣ ሕዝብ እየተበተነ ቆመን ማየታችን ሊታረም ይገባል፡፡
መሪዎች ሆይ፣ ባለመጸለያችን ብዙ ተጎድተናል፡፡
ከምንጸልይ ይልቅ፣ በፕሮጀክት ቀረጻ ጊዜ ማጥፋታችን፣ በጥቃቅን ነገር አለመግባባታችን፣ ለግል ጥቅማችን መነካከሳችን፣ የመንግሥቱን
ሥራ አስተጓጉሎብናል፡፡
ታውቃላችሁ፣ ያለ ጌታ ወጥተን፣ የትም
አንደርስም፡፡ ያለ ጌታ መርተን ሕዝብን አናድንም፡፡ ያለ ጌታ ዘርተን ፍሬ አናገኝም፡፡ ያለ ጌታ እርዳታ የአመራር ዘይቤያችን፣
የማስፈጸም ስልታችን ሊሠራ አይችልም!
መሪዎች ሆይ፣ ‹‹እኔ የወይን ግንድ ነኝ
እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉም›› ያለው ጌታ ስለሆነ፣ ከጌታ ተጣብቀን መኖር እንድንችል፣ በአመራራችን
ማፍራት እንድንችል የእግዚአብሔርን አመራር በጸሎት እንፈልግ፡፡
--------------------------------
(ትምህርቱ
ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክና ሼር
ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)
No comments:
Post a Comment