ዲቮሽን ቁ.92/07 ሐሙስ፣ ታህሳስ 2/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)
ጸሎተኛ መሪ !
… ‹‹ከምርኮ ወደ አገራቸው የተመለሱት ሰዎች በታላቅ መከራና ውርደት ላይ ይገኛሉ፡፡
የኢየሩሳሌም ቅጥር ፈራርሶአል፥ በሮችዋም በእሳት ተቃጥለዋል›› አሉኝ። ይህንም ቃል በሰማሁ ጊዜ ተቀምጬ አለቀስሁ፥ በሰማይም
አምላክ ፊት አያሌ ቀናት አዘንሁ፣ ጾምሁ፣ ጸለይሁም… (ነህ
1፡3-4)።
እውነተኛ መሪ ከራሱ ይልቅ ለሕዝቡ ይቆረቆራል፡፡ መንፈሳዊ መሪ የሕዝቡ መከራ፣ የሕዝቡ ውጣውረድ፣ የሕዝቡ እንግልት፣
የሕዝቡ ችግርና ውርደት እረፍት ይነሳዋል፡፡ ስለሆነም፣ የሕዝቡን መከራና ውርደት፣ የሕዝቡን ችግርና ስደት ይዞ ወደ እግዚአብሔር
ይቀርባል፡፡ የፈረሰውን ቅጥር፣ የወደቀውን አጥር፣ የተሰበረውን በር፣ ለእግዚአብሔር ያሳያል፡፡ በእግዚአብሔር ፊት በእንባና በሐዘን፣
በጾምና ጸሎት፣ በንስሐ ወድቆ ለሕዝቡ ይማልዳል፡፡
እውነተኛ መሪ የእንባ ሰው ነው! እውነተኛ መሪ ለእግዚአብሔር ቤት መፍረስ፣ ለእግዚአብሔር ሕዝብ ውርደት ያለቅሳል፡፡ እውነተኛ መሪ ስለተዋረደው ክብር፣
ስለቀዘቀዘው ፍቅር በእግዚአብሔር ፊት በእንባና በሐዘን፣ በጾምና ጸሎት፣ በንስሐ ወድቆ ለሕዝቡ ይማልዳል፡፡
ነህሚያን አስቡ! ነህሚያ የጸሎት ሰው ነበር፡፡ ነህሚያ በታላቅ አክብሮት በቤተመንግሥት የሚኖር ቢሆንም፣ የሕዝቡን ስድብና ንቀት፣ መከራና
ውርደት ሲሰማ መደሰት አልቻለም፡፡ የፈረሰውን ለመሥራት፣ የተዋረደውን ለማቅናት፣ ሌሊትና ቀን በእንባ ይጸልያል፡፡
ወገኖች ሆይ፣ ጸሎተኛ መሪዎች ለሕዝብ ተቆርቋሪዎች ናቸው፡፡ ጸሎተኛ መሪዎች ለሕዝባቸው መጽናናት፣ ለእግዚአብሔር ቤት
መሠራት ተቆርቋሪዎች ናቸው፡፡ ጸሎተኛ መሪዎች ለሕዝቡ መነሳት፣ ለክብሩ መሞላት ተቆርቋሪዎች ናቸው፡፡
ወገኖች ሆይ፣ ጸሎተኛ መሪዎች ለክብሩ መመለስ፣ ለቤቱ መታደስ ተቆርቋሪዎች ናቸው፡፡ ጸሎተኛ መሪዎች ለምድሩ ጉብኝት፣
ለመንፈሱ ሙላት ተቆርቋሪዎች ናቸው፡፡ ጸሎተኛ መሪዎች ለኃጢአት ንስሐ፣ ለምሕረቱ ለፍስሐ ተቆርቋሪዎች ናቸው፡፡
ታውቃላችሁ፣ ጌታችን ኢየሱስ በየዕለቱ በጸሎት ይተጋ ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ለሚሰጠው ትምህርት፣ ለሚያቀርበው ስብከት፣
ለድንቅ ለተአምራት በጸሎት መደገፍ ወሳኝ ሆኖ ካገኘው፣ መሪዎቻችን ደግሞ ምን ያህል አብልጠው በጸሎት ሊተጉ እንደሚገባ ግልጽ ነው፡፡
ታውቃላችሁ፣ ነህሚያ ሕዝብን ለማነቃቃት፣ አጥሩን ለመገንባት በጾምና ጸሎት መትጋት ካስፈለገው፣ መሪዎቻችን ደግሞ አብልጠው
ሊተጉ እንደሚገባ ነው፡፡
ታውቃላችሁ፣ ሥጋዊያን መሪዎች ከመንበርከክ ይልቅ፣ ከመጾምና ከመጸለይ ይልቅ፣ ወንበር ላይ ተቀምጠው ብይን ይሰጣሉ፡፡
ሥጋዊያን መሪዎች ከመጸለይ ይልቅ፣ በጠረጴዛ ዙሪያ ስብሰባ ተቀምጠው ይጨቃጨቃሉ፣ ይነታረካሉ፣ ይከፋፈላሉ፡፡ ሥጋዊያን መሪዎች ከመጸለይ
ይልቅ፣ በአጀንዳቸው ዙሪያ በቃለጉባኤ ይፈራረማሉ፡፡ ሥጋዊያን መሪዎች በድምጽ ብልጫ ሒደት ውሳኔ ለመስጠት እጆችን ሲቆጥሩ፣ የእግዚአብሔርን
እጅ ማየት ይረሳሉ፡፡
ወገኖች ሆይ፣ ስለጸሎት ከኢየሱስ እንማር፡፡ ጥርት ያለ ራዕይ፣ ጥርት ያለ አቋም፣ ጥርት ያለ አመራር መስጠት እንድንችል
ከኢየሱስ እንማር፡፡ ጌታችን ኢየሱስ፣ ከዕለቱ አገልግሎት በፊት በማለዳ ጸሎቱን ያደርሳል (ማር 1፡35)፡፡ ወሳኝ ለሆ ውሳኔ ሌሊቱን
ሙሉ ሲጸልይ ያድራል (ሉቃ 6፡12)፡፡ ዝናው በወጣ መጠን፣ ክብሩ በተገለጠ መጠን ራሱን ከሰው እየለየ ለአባቱ ይሰግዳል (ሉቃ
5፡16)፡፡ መንፈሳዊ መሪ ይህንን ያደርጋል፡፡
No comments:
Post a Comment