Sunday, December 21, 2014

የእምነት ፈተና !



ዲቮሽን .102/07     እሁድ ታህሳስ 12/07 ..
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


የእምነት ፈተና !

እግዚአብሔር አብርሃምን ሊፈትነው ፈልጎ ልጅህን ሰዋልኝ ባለው ጊዜ፣ ዘሩ በእርሱ አማካይነት የሚበዛለት መሆኑን በማመን አስቀድሞ በተስፋው መሠረት ያገኘውን ልጁን በእምነት ለመሠዋት አላመነታም፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር ከሞት ሊያስነሳለት እንደሚችል አምኖ አንድ ልጁን ይስሐቅን ለመስዋዕትነት አቀረበው፡፡ እንዳመነውም ሆኖለት ልጁ ከሞት ዳነ (ዕብ 11፡17-18)።

እምነት እንደ ትምህርት፣ እንደ ኮርስም ነውና፣ እምነት ፈተና አለው፡፡ ፈተና ማለፍና መውደቅ አለውና፣ እምነትም ማለፍና መውደቅ አለው፡፡ በፈተና ማለፍና መውደቅ የሚወሰነው ትምህርቱን ወይንም ኮርሱን ጠንቅቆ በማወቅ ወይም ባለማወቅ እንደሆነ ሁሉ፣ የእምነት ማለፍና መውደቅ የሚወሰነው እግዚአብሔርን በማወቅና ባለማወቅ ነው፡፡

ታውቃላችሁ፣ የእምነት ፈተናን መውደቅ ማለት እግዚአብሔርን አለማወቅ ማለት ነው! እግዚአብሔርን የማያውቅ የእምነት ፈተናን መሻገር አይችልም!

ታውቃላችሁ፣ እግዚአብሔርን አለማወቅ ማለት ኃይልና ብቃቱን፣ ዕውቀት ችሎታውን፣ ክብርና ግርማውን አለማወቅ ነው! ጌታን አለማወቅ ፍቅሩን ቸርነቱን፣ ፍርድና ምሕረቱን፣ ሥርዓት አደራረጉን አለማወቅ ነው!

ወገኖች ሆይ፣ እምነት ፈተና አለው! የምንወደውን ነገር ሳንሰሰት ልንሠዋ፣ የምንፈልገውን አሳልፈን ልንተው፣ የጨበጥነውን ለቅቀን፣ የቋጠርነውን ፈትተን፣ ልንበትን፣ ልንዘራ እምነት ፈተና አለው!

ወገኖች ሆይ፣ እምነት ፈተና አለውና፣ እግዚአብሔር ሊፈትን ሲፈልግ ውዱን ነገራችንን ‹‹ሰውልኝ›› ይለናል! ተስፋ የምናደርገውን፣ ብዙ ልፋት ለፍተን፣ ብዙ ዋጋ ከፍለን፣ ወጥተንና ወርደን የሰበሰብነውን ‹‹ተዉልኝ›› ይለናል!

ወገኖች ሆይ፣ እምነት ፈተና አለውና፣ ለመቀበል መስጠት፣ ለማጨድም መዝራት፣ ለመውጣትም መውረድ ግዴታ ይሆናል!

--------------------------------

‹‹የወንጌላዊ እጮኛ›› የተሰኘውና በሺዎች የተደነቀው ልብ አንጠልጣይ መጽሐፍ እሁድ፣ ታህሳስ 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቀኑ በ9፡00 ይመረቃል፡፡ ካዛንቺስ ኡራኤል መካነየሱስ አጠገብ በሚገኘው የኢትዮጵያ ሕይወት ብርሃን ቤተክርስቲያን ዋና ጽ/ቤት እንዲገኙልኝና ይህንን ታሪካዊ መጽሐፍ እንዲመርቁልኝ በአክብሮት ጋብዤዎታለሁ፡፡

No comments:

Post a Comment