ዲቮሽን
ቁ.101/07 ቅዳሜ፣ ታህሳስ 11/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)
ቃየላዊ
ወአቤላዊ !
አቤል ከቃየል ይልቅ
የሚበልጥን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በእምነት አቀረበ፥ በዚህም፥ እግዚአብሔር ስለ ስጦታው ሲመሰክር፥ እርሱ ጻድቅ እንደ ሆነ ተመሰከረለት፤
ሞቶም ሳለ በመሥዋዕቱ እስከ አሁን ይናገራል (ዕብ 11፡4)።
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን፣
ቃየል አርሶ አደር፣ አቤል አርብቶ አደር ነው (ዘፍ 4)፡፡ ገበሬው ቃየል ከእርሻው ፍሬ፣ በግ ጠባቂውም አቤል ከበጎቹ መስወዕት
አቀረበ፡፡ ሁለቱም ግለሰቦች ከየሥራቸው ውጤት መስዋዕት ማቅረባቸው ተገቢ ተግባር ነው፡፡ ነገር ግን፣ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚል፣
እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ሲመለከት፣ በቃየንና በመሥዋዕቱ ግን አልተደሰተም። ግን ለምን?
ወገኖች ሆይ፣ እግዚአብሔርም
በአቤልና በመሥዋዕቱ የተደሰተበት፣ በቃየንና በመሥዋዕቱ ግን ያልተደሰተበት ግልጽ ምክንያት አለ። ይኼውም፣ ቃየል ከእርሻው ፍሬዎች
እጁ ያገኘውን በዘፈቀደ ሁኔታ ሰብስቦ ሲያቀርብ፣ አቤል ግን ከበጎች መርጦ በኩራቶቹን፣ ከበኩራቶቹም መርጦ የሰቡትን ነው!
ታውቃላችሁ፣ እግዚአብሔርን
የሚያስደስተው ስጦታችን ሳይሆን መስዋዕታችን ነው! ወገኖች ሆይ፣ መስዋዕት ምንድነው!
መስዋዕት ማለት ከስጦታ መርጦ በኩር የሆነውን፣ ከበኩርም መርጦ ውድ የሆነውን ለጌታ መስጠት ነው!
ታውቃላችሁ፣ እግዚአብሔርን
የሚያስደስተው ስጦታችን ሳይሆን መስዋዕታችን ነው! ለጌታ ስንሰጥ ከራስ ወዳድነት ውጭ፣ ከስግብግብነት ውጭ፣ ከስስታምነት
ውጭ በእምነት ይዘን ስንቀርብ ጌታ ይደሰታል!
ታውቃላችሁ፣ የአቤል
መስዋዕት የተመረጠ ነው! ከሚያሳሱ በጎች፣ ከእነርሱም በኩራት፣ ከእነርሱም የሰቡት ተመርጠው
በእምነት ቀረቡ! በአቤል መስዋዕት ጌታ ተደሰተ! ይኼ የእግዚአብሔር ደስታ፣ ከዘፍረት ጀምሮ እስከዘላለም ድረስ
እየተወራለትና እየተዘመረለት ይኖራል!
ወገኖች ሆይ፣ በብሉይ
ኪዳንም ሆነ በአዲስ ኪዳን እግዚአብሔርን ማስደሰት የቻለ ስጦታ በመስዋዕት የተደረገ የእምነት ስጦታ ብቻ ነው!
ወገኖች ሆይ፣ አብርሃምን
አስቡ! ከብዙ ፈተና በኋላ በዕድሜው መጨረሻ የተወለደውን፣ ምትክና ምርጫ ምንም የሌለውን፣ አንዲያ ልጁን ለእግዚአብሔር ሊሰዋ መሠዊያ
ሠራ፥ እንጨት ረበረበ፣ ውድ ልጁን አስሮ በመሠዊያው፣ በእንጨቱ ላይ አጋደመ፡፡ ልጁንም ያርድ ዘንድ እጁን ዘረጋና ቢላዋ አነሣ።
ታውቃላችሁ፣ ጌታ
የሚወድደው እንዲህ ያለ ስጦታ፣ እንዲህ ያለ መስዋዕት ነው! ሽማግሌው አብርሃም ለልጁ ሳይሰስት፣ ሳይደብቅ ሳይከለክል በእምነት
ስለ ሰጠ እግዚአብሔር ባረከው፡፡ ለምድር አሕዛብ ሁሉ አባት አደረገው፡፡
ወገኖች
ሆይ፣ ባለ ሁለት ሳንቲሟን ድሀ መበለት አስቡ! በዕለቱ ከነበሩ ብዙ ባለሀብቶች ይልቅ እርሷ በምን ሒሳብ
ጌታን አስደሰተች?
የዕለቱ ሰጭዎች ካላቸው ሀብት ላይ መባቸውን ሲያቀርቡ፣ እርሷ ግን ያላትን አሟጥጣ መስዋዕት አቀረበች፡፡ ጉድለት እያለባት፣ የያዘቻትን
ጥሪት ጨርሳ ስትሰጥ ጌታችን ኢየሱስ ‹‹ይህች ሴት በድኻ አቅሟ፣ ያላትን መተዳደሪያ በሙሉ ሰጥታለችና፣ ከዚህች ሴት እጅ እንዲህ
ያለ ስጦታ መቀበል ግፍ ነውና ገንዘቧን መልሱ›› አላለም፡፡ ይልቁንም፣ በዚህ መስዋዕቷ ጌታ ማስደሰቱን ለሰው መሰከረ(ሉቃ 12፡41-44)፡፡
ወገኖች
ሆይ፣ ለመቄዶንያ አብያተ ክርስቲያናት የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ጸጋ አስቡ! በብዙ መከራ ተፈትነው ሳሉ፣ የደስታቸው ብዛትና የድህነታቸው
ጥልቅነት የልግስናቸውን ባለ ጠግነት አብዝቶአል! እንደ ዓቅማቸው መጠን ብቻ ሳይሆን፣ ከዓቅማቸውም የሚያልፍ መስዋዕትነት
ያለው ስጦታ እንኳ ወድደው እንደ ሰጡ፣ ይህም ጌታን ማስደሰቱን ቃሉ ይመሰክራል(2ቆሮ 8)፡፡
ወዳጄ ሆይ፣ ካለዎት
ነገር መካከል ታላቁንና ከፍ ያለውን መርጠው ለጌታ ሥራ ሰጥተው ያውቃሉ? በእጅዎ የያዙትን ነገር በጥሰው
በጌታ መስዋዕት ያቀረቡበትን ጊዜ ያስታውሳሉ? በዚህ ረገድ የሚነገርልዎት ነገር አለ? መስዋዕትነት ያለው ስጦታ በማቅረብ በእግዚአብሔር
ሕዝብ ዘንድ ለምሳሌ የሚነሳ፣ ለታሪክ የሚወሳ ነገር ሠርተው ያውቃሉ?
ታውቃላችሁ፣ መሞት
አይቀርምና፣ ከሞትን በኋላ የዛሬው ሀብታችን ንብረት ጥሪታችን ብዙ በሊታዎች ይከፋፈሉበታል! ከሞትን በኋላ የዛሬውን ሀብታችን ብዙዎች
ይሻሙታል፣ ይወጋገሩበታል፣ ይካሰሱበታል፣ ይጋደሉበታል! ይኼ እንዳይመጣ፣
ሀብት ንብረታችንን፣ ለእግዚአብሔር እንስጥ፣ በእጁም እናስቀምጥ!
ወዳጄ ሆይ፣ መባዎትን
ለማቅረብ መንፈስዎ የማይፈታ፣ እጅዎ በእምነት የማይዘረጋ ከሆነ እግዚአብሔር በስጦታዎ አይደሰትም!
ለአስራትና መባው፣ ለበኩራት ስጦታው ስስት፣ ስግብግብነት የሚጫነዎት ከሆነ አደጋ ላይ ነዎት!
ወዳጄ ሆይ፣ ስጦታ
ሲያቀርቡ ምርጡን ለራስዎት አስቀርተው ለጌታ ምራጩን የሚሰጡ ከሆነ፣ አደጋ ላይ ነዎት! ያገኙትን አስልተው ከሚያቀርቡ ይልቅ በዘፈቀደ
ሁኔታ እየሰጡ ከሆነ፣ አደጋ ላይ ነዎት! በቃየል መንፈስ ተጽዕኖ ተተብትበው እንዳይሆን ራስዎን ይመርምሩ!
--------------------------------
‹‹የወንጌላዊ
እጮኛ›› የተሰኘውና በሺዎች የተደነቀው ልብ አንጠልጣይ መጽሐፍ ታህሳስ 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቀኑ በ9፡00 ይመረቃል፡፡
ካዛንቺስ ኡራኤል መካነየሱስ አጠገብ በሚገኘው የኢትዮጵያ ሕይወት ብርሃን ቤተክርስቲያን ዋና ጽ/ቤት እንዲገኙልኝና ይህንን
ታሪካዊ መጽሐፍ እንዲመርቁልኝ በአክብሮት ጋብዤዎታለሁ፡፡
No comments:
Post a Comment