ዲቮሽን
ቁ.103/07 ሰኞ፣ ታህሳስ 13/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)
ሳንወሰድ ደስ እናሰኘው!
ሄኖክ ሞትን እንዳያይ
በእምነት ተወሰደ፥ እግዚአብሔርም ስለ ወሰደው አልተገኘም። ሳይወሰድ እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘ ተመስክሮለታልና፤ ያለ እምነትም
ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና።
(ዕብ 11፡5-6)።
አማኞች
በዚህች ምድር ላይ ያለነው፣ ለመብላት ለመጠጣት፣ ለመተኛት ለመነሳት፣ ለማፍቀር ለማግባት፣ ለመውለድ ለመክበድ፣ ለመሥራትና ለመክበር
አይደለም፡፡ አማኞች በዚህች ምድር ላይ ያለነው እንደ አሕዛብ ሮኖ ኖሮ ለመሞት አይደለም፡፡ በዚህች ምድር ላይ ያለነው እግዚአብሔርን
ለማስደሰት ነው!
ወገኖች
ሆይ፣ አማኞች በዚህች ምድር ላይ ያለነው ከዚህች ምድር ላይ ከመወሰዳችን በፊት፣ ያለነው እግዚአብሔርን ለማስደሰት ነው! ከዚህች ምድር
ላይ በሞት ከመለየታችን በፊት እግዚአብሔርን ደስ እንድናሰኘው ነው!
ታውቃላችሁ፣
ሔኖክ ያደረገው ይህንን ነገር ነው! ሔኖክ ከምድር ላይ ከመወሰዱ በፊት፣ የሕይወቱ ዋና ሥራ የነበረው
እግዚአብሔርን ለማስደሰት ነው!
ወገኖች
ሆይ፣ የሰው ልጅ ሲወለድ ወደዚህች ምድር የሚቀላቀለው እያለቀሰ ነው! በተወለድንበት
ወቅት እኛ ስናለቅስ ሰዎች እልል ብለዋል! እኛ ስናነባ ሌሎቹ ስቀዋል! ነገር ግን፣ የምድር
ኑሮአችንን ጨርሰን ስንሄድ እኛ በተራችን ፈገግ እንላለን፣ ሌሎች ያለቅሳሉ!
ወገኖች
ሆይ፣ የምድሩ ሩጫችን አልቆ ተጠናቅቆ፣ ከመወሰዳችን በፊት፣ ምን እያደረግን ነው? በምድር ላይ ሳለን
እግዚአብሔርን ለማስደሰት ምን እየሠራን ነው?
ወገኖች
ሆይ፣ ሞተን ስንቀበር ከመቃብር በላይ የሚውል አገልግሎት በእጃችን አለ ወይ! በሞት የማይወሰን፣
ከሞትንም በኋላ ጮኾ የሚናገር ነገር እየሠራን ነው ወይ? ከሄድን በኋላ ከኋላችን ቀርቶ፣ የሚመሰከርለት የእምነት አገልግሎት፣
የእምነትም ሕይወት በእጃችን አለ ወይ?
ወገኖች
ሆይ፣ ሄኖክ ሞትን ሳያይ፣ ከምድር
ገጽ ላይ ከመወሰዱ በፊት የነበረው ኑሮ የተመሰከረለት ነው፡፡ የምስክርነቱም ምክንያት፣ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት በመቻሉ ላይ
ነው፡፡ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት የመቻሉም ሚስጥር የእምነት ኑሮ ነው!
ወገኖች ሆይ፣ ምድራዊ
ኑሮአችን እንዴት እየሄደ ነው? ምስክርነታችን እንዴትስ ያለ ነው? እግዚአብሔርን ለማስደሰት
ምን እየሠራን ነው? በእምነት እየኖርን፣ ጌታን ለማስደሰት መብቃት እንድንችል እግዚአብሔርን ይርዳን!
--------------------------------
‹‹የወንጌላዊ
እጮኛ›› በሺዎች የተደነቀ ልብ አንጠልጣይ መጽሐፍ እሁድ፣ ታህሳስ 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቀኑ በ9፡00 ይመረቃል፡፡
ካዛንቺስ ኡራኤል መካነየሱስ አጠገብ በሚገኘው የኢትዮጵያ ሕይወት ብርሃን ቤተክርስቲያን ዋና ጽ/ቤት እንዲገኙልኝና ይህንን
ታሪካዊ መጽሐፍ እንዲመርቁልኝ በአክብሮት ጋብዤዎታለሁ፡፡
No comments:
Post a Comment