Thursday, December 18, 2014

ኃይልን በእምነት ማግኘት !

ዲቮሽን .99/07     ሐሙስ ታህሳስ 9/07 ..
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


ኃይልን በእምነት ማግኘት !

ተስፋ የሰጠው የታመነ እንደ ሆነ ስለ ቈጠረች፥ ሣራ ራስዋ ደግሞ ዕድሜዋ እንኳ ካለፈ በኋላ ዘርን ለመፅነስ ኃይልን በእምነት አገኘች። ስለዚህ ደግሞ በብዛታቸው እንደ ሰማይ ኮከብ እንደማይቈጠርም በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ የነበሩት የሞተን ሰው እንኳ ከመሰለው ከአንዱ ተወለዱ (ዕብ 11፡11-12)።

ሳይንሱ እንደሚጀነጅነን ሴቶች ከአርባዎቹ የዕድሜ ክልል ጀምሮ የመውለድ ዕድላቸው እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ በሴቶች የሚሆነውም ልማድ በእነዚህ ዓመታት ክልል ውስጥ መቋረጥ ይጀምራል፡፡ ከዚህ ታሪክ በኋላ ልጅ መውለድ የማይታሰብ ይሆናል፡፡ ይህ አስተሳሰብ ‹‹ሳይንሳዊ ሐቅ›› ይባላል!

ወገኖች ሆይ፣ ይህ ‹‹ሣይንሳዊ ሐቅ›› ሳይንሳዊ ሐቅ እንጂ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐቅ አይደለምና፣ በእምነት ላቦራቶሪ ፍተሻ ሲደረግ ‹‹ፉርሽ ሐቅ›› ሆነ! ስለሆነም፣ ከሣይንሳዊ ጥናት ውጭ፣ ከሙያዊ መላምት ውጭ፣ ከሰዋዊ አስተሳብ ውጭ በሆነ ሁኔታ አብርሃምና ሣራ በዕድሜአቸው ሸምግለው ፈጽመው አርጅተው ሳሉ ኃይልን በእምነት አገኙ!

ታውቃላችሁ፣ ተስፋ የሰጠው የታመነ እንደ ሆነ ስለ ቈጠረች፣ ሣራ እግዚአብሔር ታመነች! ዕድሜዋ አልፎ እንኳ፣ ነገሯ ኤክስፓየር አድርጎ እንኳ ተስፋ የሰጠው የታመነ ነውና፣ እግዚአብሔር ታመነች!  አርግዞ ለመውለድ፣ ወልዶም ለማሳደግ ኃይልን በእምነት አገኘች!

ወገኖች ሆይ፣ አሮጊቷ ሣራ እግዚአብሔር ስለታመነች፣ ኃይልን በእምነት አገኘች! ከዚህም የተነሳ፣ የአሮጊቷ ማህጸን ልጅ መሸከም ቻለ! ይህም ብቻ አይደለም፣ አሮጊቷ ስትወልድ ሰበር ዜና ሆነ! ይህም ብቻ አይደለም፣ የአሮጊቷ ጡቶች በወተት ተሞልተው ልጅን ሲያጠቡ በሰዎች መካከል መደነቅ፣ መገረም መሣቅ መነጋገር የሀገር ሥራ ሆነ!

ወገኖች ሆይ፣ ኃይልን በእምነት ያገኙት አብርሃምና ሣራ፣ በዚያው በያዙት ተስፋ ቃል፣ በብዛታቸው እንደ ሰማይ ኮከብ እንደማይቈጠርም በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ የሆኑ ልጆች መባዛት ቀጠሉ!

ወገኖች ሆይ፣ ተስፋ ቃል ካለን፣ ጌታ ከተናገረን ጊዜው ቢሄድም፣ ጉዳዩ የቀረ ቢመስልም፣ ጊዜውን ጠብቆ መፈጸሙ አይቀርም! ተስፋ የሰጠው የታመነ ነውና፣ የተሰጠን ተስፋ ቃል ይፈጸማል እንጂ መሬት ላይ አይወድቅም! እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው ያስበናልና፣ እንደ ተናገረው ያደርግልናል፣ ኃይልን በእምነት ልናገኝ ይገባል፡፡ ለእምነት ኃይል ተሐድሶ በመንፈስ ቅዱስ ሙላት መደገፍ ይገባል!

ወገኖች ሆይ፣ ኃይልን በእምነት በማግኘታቸው ምክንያት የሞቱ ከሚመስሉ ሰዎች፣ በብዛታቸው እንደ ሰማይ ኮከብ እንደማይቈጠርም በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ የሆኑ ልጆች ከተወለዱ፣ የሞትን ከማንመስል ከእኛስ እንዴት ያለ ሥራ ይከናወን ይሆን?

ወገኖች ሆይ፣ ኃይልን በእምነት በማግኘታቸው ምክንያት አብርሃምና ሣራ በዕድሜአቸው ሸምግለው ፈጽመው አርጅተው ሳሉ የተሰጣቸውን ተስፋ ቃል ካገኙ፣ እንደ እነርሱ በዕድሜ ያላረጀንና ያልገረጀፍን ሰዎች እንዴት ያለ ነገር እንቀበል ይሆን?

--------------------------------
‹‹የወንጌላዊ እጮኛ›› የተሰኘውና በሺዎች የተደነቀው ልብ አንጠልጣይ መጽሐፍ ታህሳስ 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቀኑ በ9፡00 ይመረቃል፡፡ ካዛንቺስ ኡራኤል መካነየሱስ አጠገብ በሚገኘው የኢትዮጵያ ሕይወት ብርሃን ቤተክርስቲያን ዋና ጽ/ቤት እንዲገኙልኝና ይህንን ታሪካዊ መጽሐፍ እንዲመርቁልኝ በአክብሮት ተጋብዘዋል፡፡


No comments:

Post a Comment