Thursday, December 18, 2014

እምቢ በል!

ዲቮሽን .98/07     ረቡዕ ታህሳስ 8/07 ..
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


እምቢ በል!

ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርዖን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እምቢ አለ፤ ከግብፅም ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለ ጠግነት እንዲሆን አስቦአልና ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ፤ ብድራቱን ትኵር ብሎ ተመልክቶአልና (ዕብ 11፡24-26)።

መወለድ ቋንቋ ነውና የትም ልንወለድ እንችላለን፡፡ ማደግም ዕድል ነውና የትም ልናድግ እንችላለን! ነገር ግን የሰው ልጆች ሕይወት ዋናው የጨዋታ ክፍል የሚጀምረው ካደጉ በኋላ ነው፡፡ ልማትም ሆነ ጥፋት ሥራ የሚጀምረው ዕድገት ሲመጣ ነው!

ወገኖች ሆይ፣ ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርዖን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እምቢ አለ፡፡ ይህ ውሳኔው በሰው እይታ ስህተት፣ በእምነት ሲታይ ግን ትክክል ነበር!

ታውቃላችሁ፣ አንዳንዴ በልጅነታችን የሚጣበቀብንን ጭቃ ማስለቀቅ አስቸጋሪ ነው! እግዚአብሔር ካልረዳ በስተቀር፣ ከልጅነት የሚወረስ ልማድ እንደ ሽንፍላ ሲታጠብም ቢውል ቶሎ የማይለቅቅ ነው!

ወገኖች ሆይ፣ ሙሴ ካደገ በኋላ የንጉሡን ቁጣ ሳይፈራ፣ ግብጽን የተወው በእምነት ነው! አንዳንዴ እግዚአብሔር ከማይከብርበት ሕይወት ጥሰን ለመውጣት ስንሞክር ተግዳሮት ይበዛል፡፡ ጨክነን ስንወጣ ደግሞ በውሳኔያችን የሚከፉ፣ አቋማችንን የማይደግፉ ገዥዎቻችን አሉ፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ሙሴ በአቋሙ መጽናት የቻለው ‹‹የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ ስለ ጸና›› ነው። ወገኖች ሆይ፣ የዕብራዊያን ጸሐፊ ጮኾ የሚሰብከው ይህንን እውነት ነው!

ታውቃላችሁ፣ ሙሴ አሽንቀጥሮ የጣለው ሀብትና ማዕረግን፣ ዝናንና ክብርን ብቻ ሳይሆ የሀገር ንጉሥነትን ነው፡፡ ከግብፅ ንጉሥነት ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍን፣ ከግብፅ ብዙ ገንዘብ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር ብዙ መከራ መቀበልን ነው! በኃጢአት ከሚገኝ ጊዜያዊ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር ሐዘን መሸከምን ነው!  

ወገኖች ሆይ፣ የእግዚአብሔር ሰው ከጊዜያዊ ደስታ ይልቅ የሚዘልቀውን ሐሴት ይመርጣል! ከምድራዊ ሀብት ይልቅ ሰማያዊ ባለ ጠግነትን ያስባል! ከዛሬው ሁኔታ ይልቅ የወደፊቱን ብድራት ትኵር ብሎ ይመለከታል!

ታውቃላችሁ፣  ዛሬ ላይ ቆመን የእምነት መነጽር አድርገ የወደፊታችንን ስናይ፣ የሚጠብቀን ክብር፣ ከዛሬው ደስታ ይልቅ እጅግ የላቀ ነው! ለእርሱ ክብር ብለን በኃጢአት የሚገኘውን እምቢ በምንለው ፈንታ የተዘጋጀልን ብድራት እጅግ የላቀ ነው! ሙሴም ትኩር ብሎ ያየው ይህንን እውት ነው!

ወገኖች ሆይ፣ ሙሴ ካደገ በኋላ ስሙ በፈርዖን ልጅነት፣ በግብጽ ዜግነት እንዳይጠራ በእምነት እምቢ አለ! ታውቃላችሁ፣ ስማችንን በክፉ የሚያስጠራን ነገር እምቢ ልንል ይገባል! ስማችንን ከሚያቆሽሽ፣ ምስክርነታችንን ከሚያበላሽ ከማናቸውም ነገር ልንወጣ ይገባል፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ማንነታችንን ጥለን፣ ሕይወታችን ጥለን፣ ጽድቅ ቅድስናችንን ጥለን፣ ክብራችንን ጥለን የምናገኘውን ማናቸውንም ደስታ እምቢ ልንል ይገባል! ከባርነት ምድር፣ ጌታ ከማይከብርበት ነገር፣ በኃጢአት ከሚገኝ ዝና፣ ሀብትና ክብር፣ በእምነት ለቅቀን እንውጣ!

--------------------------------

(ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክና ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)

No comments:

Post a Comment