Friday, December 19, 2014

ቤተሰብ ለማዳን !

ዲቮሽን .100/07     አርብ ታህሳስ 10/07 ..
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


ቤተሰብ ለማዳን !


ኖኅ ገና ስለማይታየው ነገር ተረድቶ እግዚአብሔርን እየፈራ ቤተ ሰዎቹን ለማዳን መርከብን በእምነት አዘጋጀ፥ በዚህም ዓለምን ኰነነ፥ በእምነትም የሚገኘውን ጽድቅ ወራሽ ሆነ(ዕብ 11፡7)።

እምነት ማለት ስለማይታየው ነገር መረዳትና ለተረዱት ነገር ወቅታዊ ምላሽ መስጠት ነው፡፡ ኖህ ወደፊት ስለሚሆነው ነገር ከእግዚአብሔር ማስጠንቀቂያ ተሰጠው፡፡ ኖህ ለደረሰው ማስጠንቀቂያ በእምነት ምላሽ ሰጠ – (1ኛ) ማስጠንቀቂያውን ለሰዎች መስበክ ጀመረ፣ (2ኛ) መርከብ መሥራት ጀመረ፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ኖህ ከእግዚአብሔር የደረሰውን ማስጠንቀቂያ ለ120 ዓመታት ቢሰብክም፣ በእነዚያ ለ120 ዓመታት ውስጥ ከቤተሰቡ በስተቀር አንድም ሌላ ሰው መልዕክቱን አልተቀበለም፡፡ ከቤተሰቡ በስተቀር አንድም ሌላ ሰው ምስክርነቱን ሰምቶ አልተመለሰም፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ኖህ ለ120 ዓመታት፣ ስለጥፋት ውሃ መምጣት ቢሰብክም፣ ለምልክት እንዲሆን በሰዎች ሁሉ ፊት መርከብ ቢገነባም፣ ሁኔታውን አይቶ መልዕክቱንም ሰምቶ ጆሮ የሰጠው የለም፡፡

ታውቃላችሁ፣ የእምነት ምላሽ ከራስ ይጀምራል! እውነተኛ አገልግሎት ከቤት ይጀምራል፡፡ ሰው ዓለሙን ሁሉ አትርፎ ቤተሰቡን ቢያጎድል ምን ይረባዋል? በራስ ላይ ያልሠራ እምነት፣ በቤተሰብ ላይ ያላፈራ አገልግሎት ምንስ ይጠቅመዋል? ቤተሰዎችን ያላዳነ ስብከት፣ ራስን ያላስመለጠ እምነት ፋይዳው በምን ይታወቃል ?

ወገኖች ሆይ፣ ለሰው ልጆች ሁሉ ወንጌል የመመስከር ኃላፊነት የተጣለብን ቢሆንም፣ የቅድሚያ ትኩረታችን ቤተሰብ በማዳን ላይ ይሁን! ዋናው ትኩረታችን፣ ቤተ ሰዎቻችንን ለማዳን መርከብን በእምነት ልናዘጋጅ ይገባል!

ወገኖች ሆይ፣ እምነታችንን ከቤት እንፈትሸው! ሰዎች ስብከታችንን ላለመስማት ጆሯቸውን ቢደፍኑ፣ ምስክርነታችንን ባይቀበሉ፣ ማስጠንቀቂያችንን ባይሰሙ፣ ነገር ግን ቤተ ሰዎቻችንን ሰምቶ ከዳነልን፣ አልከሰርንም ማለት ይቻላል!

ታውቃላችሁ፣ ዓለምን የሚኮንነው እምነታችን ነውና፣ ቤተሰባችንን ድኖ ከዓለም ጥፋት ሲያመልጥ ዓለም ይኮነናል፡፡ ምስክርነታችንን ጠልተው፣ ለስብከታችንም ፍጹም ጆሮ ዘግተው፣ የገፉን ሰዎች ሁሉ የኛን መዳን ሲያዩ ያኔ ይኮነናሉ! የጣሉትን ማንሳት፣ የናቁትን ማክበር፣ የነቀፉትን ማድነቅ፣ የጠሉትን መውደድ ይጀምራሉ! ስለሆነም፣ ቤተሰባችንን ለማዳን፣ እግዚአብሔርን እየሰማንና እግዚአብሔርን እየፈራን  ቤተሰባችንን በእምነት ልናዘጋጅ ይገባል!

--------------------------------

‹‹የወንጌላዊ እጮኛ›› የተሰኘውና በሺዎች የተደነቀው ልብ አንጠልጣይ መጽሐፍ ታህሳስ 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቀኑ በ9፡00 ይመረቃል፡፡ ካዛንቺስ ኡራኤል መካነየሱስ አጠገብ በሚገኘው የኢትዮጵያ ሕይወት ብርሃን ቤተክርስቲያን ዋና ጽ/ቤት እንዲገኙልኝና ይህንን ታሪካዊ መጽሐፍ እንዲመርቁልኝ በአክብሮት ጋብዤዎታለሁ፡፡

No comments:

Post a Comment