ዲቮሽን
ቁ.97/07 ማክሰኞ፣ ታህሳስ 7/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)
እምነት
ከትናንትና!
እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው። ለሽማግሌዎች
የተመሰከረላቸው በዚህ ነውና። ዓለሞች በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተዘጋጁ፥ ስለዚህም የሚታየው ነገር ከሚታዩት እንዳልሆነ
በእምነት እናስተውላለን (ዕብ 11፡1-3)፡፡
አንድ የጤና ዶክተር
አንድን ሕመምተኛ እንደሚያደርገው ሁሉ፣ የዕብራዊያን ጸሐፊ በዕብራዊያን ክርስቲያኖች ክርስትና ዙሪያ ያሉ ችግሮችን በጥልቀት ከመረመረ
በኋላ ለችግሮቹ መፍትሔ የሚሆኑ ምክሮች ይሰጣል፡፡
ከዕብራዊያን
ክርስትና ችግሮች መካከል ዋነኛው ችግር በእምነት የመጓዝ ችግር ነው፡፡ ምዕመኖቹ ብርሃን የበራላቸው፣ ሰማያዊውንም ስጦታ የቀመሱ፣
ከመንፈስ ቅዱስም ተካፋዮች ሆነው የነበሩ፣ መልካሙንም የእግዚአብሔርን ቃልና ሊመጣ ያለውን የዓለም ኃይል የቀመሱም ነበሩ፡፡
ይሁንና፣
ከቆይታ ብዛት ትክክለኛው መንገድ ጠፍቶባቸዋል፡፡ ተስፋ ያደረጉት ሊመጣ ስላለው የዓለም ኃይል ምን ሊሆን እንደሚችል ማረጋገጥ አልቻሉም፡፡
የምዕመናኑ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምን እንደሚመስልም ማወቅም አልቻሉም፡፡ ስለሆነም፣ የክርስትናውን መስመር መጠየቅ ጀምረዋል፡፡
ክርስትና
ከልማዳዊው ጉዞ ወጣ ያለና ወደ መለኮት ሙላት እስኪደርሱ ድረስ ዕለት ተዕለት በመንፈሳዊ ሕይወት እያደጉ መሄድን የሚጠይቅ ነው፡፡
ከዚህ አንጻር፣ የዕብራዊያን ክርስቲያኖቹ፣ የክርስትናን ጉዞ ከይሁድነት ጉዞ ጋር ሲያነጻጽሩት ይሁድነት የተሻለ መስሎ ታይቷቸዋል፡፡
ስለሆነም፣ አንዳንዶቹ ከክርስትናው የእምነት ጉዞ ወደኋላ የመመለስ አዝማሚያ እያሳዩ በመዋለል ላይ ናቸው፡፡
ወገኖች
ሆይ፣ ክርስትናን እንደማይሞከር አካብዴ ሐይማኖት የሚቆጥሩ ብዙ ምዕመናን አሉ፡፡ እንደ ቃሉ መመላለስ አቅቷቸው፣ እግዚአብሔርን
መምሰል ፈተና ሆኖባቸው ወደኋላ ለመመለስ ዳር ዳር የሚሉ ብዙ የቤተክርስቲያን ሰዎች አሉ፡፡
ታውቃላችሁ፣
የክርስትና መንገድ አንድ አቅጣጫ ብቻ ነው! ይህ መስመር ሌላ አማራጭም ሆነ አቋራጭ መንገድ የለውም !
ታውቃላችሁ፣
አማራጭና አቋራጭ ፍለጋ ከወዲያ ወዲህ የሚዋልሉ፣ በሁለት ምርጫ ላይ ያሉ ብዙ ምዕመናን አሉ፡፡ ምርጫ የሌለውን ትተው ምርጫ ወደሚሰጠው
ለመግባት ዳር ዳር የሚሉ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡
ታውቃላችሁ፣
ኃጢአትን ከጽድቅ ቀይጦ ወደሚይዘው፣ ከውጩ የክርስትና ምልክት፣ ከውስጡ አጋንንታዊ ሥራ ወደተሞላው፣ እግዚአብሔርን ከዲያብሎስ፣
ክርስቶስን ከቤልሆር ሊያስማማ ወደሚመኘው ለመግባት የሚዋልሉ አሉ፡፡
ወገኖች
ሆይ፣ የክርስትና ጉዞ ተስፋ የተሞላ ነው፡፡ የብድራታችንን ተስፋ ማግኘታችንን አስቀድመን የምናረጋግጠው በእምነት በመቆም ነው፡፡
በእምነት ስንቆም፣ ተስፋ የምናደርገውን ነገር መውረስ እንደምንችል እርግጠኛ መሆን እንችላለን፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡ በእምነት
ስንቆም፣ ተስፋ የምናደርገውን ነገር መውረስ እንደምንችል ለራሳችን እርግጠኛ ሆነን፣ ለሌሎች ማስረዳት እንችላለን፡፡
ወገኖች
ሆይ፣ የወደፊታችንን ነገር፣ ተስፋ የምናደርገውን ነገር መውረስ እንደምንችል በምን አረጋግጠን ለሰው እናስረዳለን? ሰዎች ሆነን፣
ነገ ምን ሊያስከትል እንደሚችል እንዴት እናውቃለን?
ታውቃላችሁ፣
የወደፊታችንን ለማረጋገጥ ያለፈውን ማስተዋል ነው! ነገ ስለሚሆነው ተስፋችን ለማወቅ የትናንቱን ነገር በእምነት
ማየት ነው! በትናንትናው ዘመን፣ ዓለማት የተፈጠሩት በቃሉ ትዕዛዝ ብቻ ከምንም ነው!
ታውቃላችሁ፣
ወንዝና ፏፏቴው፣ ባሕር ውቅያኖሱ፣ ጨረቃ ክዋክብቱ፣ ጸሐይ ፕላኔቱ፣ ተራራ ኮረብታው ሜዳና ገላጣው፣ አትክልት ፍራፍሬው፣ ሣሩና
አበባው፣ የሚታዩት ሁሉ የተገኙት ከማይታየው ምንጭ ነው!
ታውቃላችሁ፣
ትናንት ያልነበሩትን፣ ዛሬ ግን የሚታዩትን ፍጥረታት በማየት ተስፋ ስለምናደርገው ነገር ወደፊት መቀበላችንን እርግጠኛ መሆን፣ ለሌሎችም ማስረዳት እንችላለን፡፡
ወገኖች
ሆይ፣ ስለ ነገ መጨነቅ የትናንቱን መርሳት ነው! እግዚአብሔር ያልነበሩትን ሁሉ ወደ መኖር፣ የማይታዩትን ሁሉ
ወደ መታየት ካመጣ፣ ዛሬ ላይ ቆመን ነገን ስንመለከት፣ የትናንቱ አምላክ ለነገም ታማኝ እንደሆነ በእምነት ማረጋገጥ እንችላለን፡፡
ወገኖች
ሆይ፣ ትናንት የሌለውን ነገር ወደ መኖር ያመጣ ጌታ፣ ነገን ቀድሞት አልፎ መሥራት እንዴት ያቅተዋል?
ከምንም ነገር ዓለማትን ሁሉ በቃሉ የሠራ፣ የእኛን ጉዳይ መሥራት እንዴት ይሳነዋል?
--------------------------------
(ትምህርቱ
ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክና ሼር
ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)
No comments:
Post a Comment