ዲቮሽን ቁ.96/07
ሰኞ፣ ታህሳስ 6/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)
መሪን የሚጠራ!
እግዚአብሔርም ወደ እርሱ ዘወር ብሎ። በዚህ በጕልበትህ ሂድ፥ እስራኤልንም ከምድያም እጅ አድን እነሆ፥ ልኬሃለሁ አለው። (መሳ 6፡14)፡፡
እግዚአብሔርም ወደ እርሱ ዘወር ብሎ። በዚህ በጕልበትህ ሂድ፥ እስራኤልንም ከምድያም እጅ አድን እነሆ፥ ልኬሃለሁ አለው። (መሳ 6፡14)፡፡
መሪዎች ወደ አመራር የሚመጡበት በብዙ መልኩ ነው፡፡ ሁሉም
መሪዎች ወደ አመራር የሚመጡት እግዚአብሔር ስለጠራቸው አይደለም፡፡ ዘመድ የሚጠራቸው፣ ሀብት የሚጠራቸው፣ ጥቅማጥቅም የሚጠራቸው፣ ዝናና ክብር
የሚጠራቸው፣ ዕድልና አጋጣሚ የሚጠራቸው፣ ትምህርትና ሁኔታ የሚጠራቸው፣ አሉ፡፡
በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች የተጠሩ መሪዎች፣ የመጀመሪያው ራዕያቸውና የወደፊት ግባቸው በተጠሩበት ሁኔታ አንጻር ይጀምራል፣
ይደመደማል፡፡
ለምሳሌ፣ በዘመድ እና በቅርበት ተጠርተው ወደ አመራር የወጡ ሰዎች ዘወትር የሚያስቀድሙት ዝምድናንና ወገናዊነትን ነው፡፡
የሚያከናውኑት እንቅስቃሴ ሁሉ፣ የሚያከናውኑትን ስራ ሁሉ፣ የሚነድፉትን እቅድ፣ የሚይዙትን በጀት፣ …‹‹ለወገኔ ይጠቅማል ወይ?››
በሚል ሒሳብ ሠርተው ይተገብራሉ፡፡ ይሁንና፣ እነዚህ ሰዎች እንዳሰቡት
ሳይሆን፣ የተሳፈሩት ጀልባ ይገለብጣቸዋል፡፡
ገንዘብና ሀብት እንዲሁም ጥቅማጥቅም የሚጠራቸው ሰዎች ደግሞ የዘወትር ሕልማቸው ‹‹ከዚህ አገልግሎት ጥቅም አገኝበታለሁ
ወይ?›› ሊያገኙ የሚችሉትን ትርፍ ስሌት ይሠራሉ፡፡ እነዚህ መሪዎች አመራራቸውን ለጥቅማቸው ማስከበሪያ፣ ለሀብት ምንጭ ማፍለቂያነት
ያውላሉ፡፡ ይሁንና፣ እነዚህ ሰዎች እንዳሰቡት ሳይሆን፣ የገንዘብና ሀብት ጎርፍ ጠርጎ ይወስዳቸዋል፡፡
ዝናና ክብር የሚጠራቸው መሪዎች ደግሞ፣ ዘወትር አገልግሎታቸው የሚያስገኝላቸውን ማዕረግ፣ ከበሬታ፣ ተደማጭነትና ተቀባይነት
ያስባሉ፡፡ ይሁንና፣ እነዚህ ሰዎች እንዳሰቡት ሳይሆን፣ የዝናና የክብር፣ የማዕረግና የእልቅና ወጥመድ ጠልፎ ይጥላቸዋል፡፡
በእግዚአብሔር የተጠራ መሪ ግን እንዲህ አይደለም፡፡ በእግዚአብሔር የተጠራ መሪ ሌሎች እንደሚያዩ አያይም፡፡ በእግዚአብሔር
የተጠራ መሪ በሌሎች መነጽር አገልግሎቱን አይመለከትም፡፡ በእግዚአብሔር የተጠራ መሪ እግዚአብሔርን ያውቃል፣ እርሱን ይመለከታል፣
እንደፈቃዱም ያገለግላል፡፡
ወገኖች ሆይ፣ የመሪዎቻችን ጥሪ ምንጩ ከወዴት ይሆን? መሪ ሆይ፣ ወዴት ነህ?
--------------------------------
(ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክና ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡
ጌታ ይባርክዎ!)
No comments:
Post a Comment