ዲቮሽን ቁ.94/07 ቅዳሜ፣ ታህሳስ 4/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)
የተቀባ የቁርጥ ቀን መሪ!
…መጥተውም ኢየሩሳሌምን ይወጉና ያሸብሩ ዘንድ ሁሉም በአንድነት ተማማሉ። ወደ አምላካችንም
ጸለይን፥ ከእነርሱም የተነሣ በአንጻራቸው ተጠባባቂዎች በሌሊትና በቀን አደረግን። ይሁዳም። የተሸካሚዎች ኃይል ደከመ፥
ፍርስራሹም ብዙ ነው ቅጥሩንም እንሠራ ዘንድ አንችልም አሉ (ነህ 4፡8-10)።
የእግዚአብሔር ሕዝብ ከጠላት ሰልፍ የተነሳ ሊሸበር፣ ልቡ ሊወርድና ጉልበቱ ሊደክም ይችላል፡፡ ከዚህ መሸበር፣ ከልብ
መውረድና ከጉልበት መዳከም የተነሳ የእግዚአብሔር ሕዝብ ‹‹ቅጥሩን እንሠራ ዘንድ አንችልም›› ወደሚል ድምዳሜ ሊደርስ
ይችላል፡፡ ይህ ሁኔታ ለመሪዎች ታላላቅ ከሚባሉ ፈተናዎች አንዱ ነው፡፡ ስለሆነም፣ የእምነት ፊታውራሪ፣ የተቀባ የቁርጥ ቀን መሪ
ያስፈልገናል!
ወገኖች ሆይ፣ የአንድ መሪ የመሪነት ብቃቱ የሚፈተነው የወደቀውን ሕንጻ በመገንባት ሳይሆን፣ የወደቀውን የእግዚአብሔርን
ሕዝብ ማንሳት በመቻሉ ላይ ነው፡፡ የወደቀው የእግዚአብሔርን ሕዝብ ሲነሳ፣ የወደቀው ሕንጻ ይገነባልና ነው፡፡
ወገኖች ሆይ፣ የእግዚአብሔርን ሕዝብ የእግዚአብሔር ሕንጻ ነው(1ቆሮ 3፡9)፡፡ ይህ ሕንጻ እንዲገነባ፣ ብቃት ያለው
መሐንዲስ ያስፈልገዋል፡፡ የዚህ መሐንዲስ ልዩ መጠሪያ ‹‹መንፈሳዊ መሪ›› ይባላል፡፡ የእግዚአብሔርን ሕዝብ መንፈሳዊ ሕይወት መገንባት
የማይችል መሪ መንፈሳዊ መሪ አይደለም፡፡
ታውቃላችሁ፣ ጠላት የእግዚአብሔርን ሕዝብ ጉልበት የሚያሳጣበት መንገድ አንዱ፣ ማሸበር ወይንም ማስፈራራት ነው፡፡ በነህሚያ
ጊዜ ያደረገውም ይህንኑ ነው! ጠላት ራሱን በማተለቅና የእግዚአብሔርን ሕዝብ በማሳነስ ያሸብራል፡፡ የችግሩን ዓይነት በማግዘፍና
የእግዚአብሔርን ሕዝብ በማሳጠር ያሸብራል፡፡ ነገር ግን፣ የሕዝቡን መንፈስ የሰበረው ያ ሽብር በነህሚያ አመራር ሊቀለበስ ችሏል!
ታውቃላችሁ፣ የተቀባ የቁርጥ ቀን መሪ ያስፈልገናል!
ወገኖች ሆይ፣ ጎልያድን አስቡ(1ሳሙ 17)! ጠዋትና ማታ የእግዚአብሔርን ሕዝብ በቃላት ጦርነት ያርበደብድ ነበር! ራሱን
አግዝፎ ተራራ በማሳከል፣ የእግዚአብሔርን ሕዝብ የጠጠር ያህል በመቁጠር ያሸብራቸው ነበር፡፡ ይህንን አደጋ የሚቀለብስ፣ እውነተኛ
መሪ አልነበረም፡፡ ነገር ግን፣ የሕዝቡን መንፈስ የሰበረው ያ ድንፋታ ዳዊት ሲነሳና ሊገለበጥ ችሏል፡፡ ታውቃላችሁ፣ የተቀባ የቁርጥ
ቀን መሪ ያስፈልገናል!
ወገኖች ሆይ፣ 12ቱን የሙሴ ሰላዮች አስቡ(ዘሁ 12)! አስሩ ሰላዮች የጠላትን ግዝፈት አጋንነው በማየትና የራሳቸውን
አቅም አለቅጥ በማውረድ፣ ያደረጉት ሪፖርት ሕዝቡን አሸበረ፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝብ ከሳማው ሪፖርት የተነሳ ልቡ ቀለጠ፡፡ ነገር
ግን፣ ኢያሱና ካሌብ በእግዚአብሔር ታምነው፣ ድንጋጤውን ገፍፈው፣ ሕዝቡን አረጋግተዋል! የእምነት ፊታውራሪ፣ የተቀባ የቁርጥ ቀን
መሪ ያስፈልገናል!
ወገኖች ሆይ፣ ጠላታችን ዲያብሎስ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ በየጊዜው የሚከፍተውን ጦርነት የሚቀለብስ፣ የሕዝቡን መንፈስ
የሚገነባ እውነተኛ መሪ ያስፈልገናል! የጠላትን ተግዳሮት፣ ጦርነትና
የማሸበር ስልት በእግዚአብሔር ሕዝብ ፊት ሆኖ ቆሞ የሚመክት፣ እውነተኛ መሪ ያስፈልገናል!
ወገኖች ሆይ፣ በኢኮኖሚ ጫና፣ በኑሮ ፈተና፣ በሕይወት መከራ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ጉልበት የሚያዝለውን ማናቸውም ተግዳሮት
በእምነት የሚዋጋ እውነተኛ መሪ ያስፈልገናል!
ወገኖች ሆይ፣ ሕዝቡን የሚያጽናና የምሥራች አብሣሪ፣ የሽብር ፍላጻ ቀስቶቹን ሰባሪ፣ የእምነት ፊታውራሪ፣ ወንጌልን መስካሪ፣
የተቀባ የቁርጥ ቀን መሪ፣ ያስፈልገናል!
--------------------------------
(ትምህርቱ
ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክና ሼር
ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)
No comments:
Post a Comment