ዲቮሽን ቁ.91/07 ረቡዕ፣ ሕዳር 31/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)
‹‹ስድ›› መሪዎች !
ሙሴም በጠላቶቻቸው ፊት እንዲነወሩ አሮን ስድ ለቅቋቸዋልና ሕዝቡ ስድ እንደ ተለቀቁ ባየ ጊዜ፥ በሰፈሩ ደጅ ቆሞ።
የእግዚአብሔር ወገን የሆነ ወደ እኔ ይምጣ! አለ የሌዊም ልጆች ሁሉ ወደ እርሱ ተሰበሰቡ (ዘጸ 32፡25-26)።
መጽሐፍ ቅዱስ ታላቁ መሪ አሮንን ‹‹ስድ መሪ›› በማለት ይነቅፈዋል፡፡ አያችሁኝ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ
ጸሐፊ አሮንን ‹‹ስድ መሪ›› ለማለት አላፈረም፡፡ እውነቱን ነዋ! አሮን የሠራውን ስድነት የሚገልጽ ሌላ አቻ ቃል አላገኘለትማ!
ወገኖች ሆይ፣ ምን አይነት ጥፋት ቢሆን ነው?
ሙሴ ወደ እግዚአብሔር ተራራ በእግዚአብሔር ተጠርቶ ሲወጣ ሕዝቡም፣ መሪውም ያውቃሉ፡፡ ተራራው ሲናወጥ፣ የእቶን ጢስ ከሰማይ ሲወርድ፣ ነጐድጓድና መብረቅ ከባድም ደመና እጅግም የበረታ የቀንደ መለከት
ድምጽ በተራራው ላይ ሲነፋ፣ እግዚአብሔር በድምፅ ሲናገር መሪውም ሕዝቡን እያየ ነው፡፡
ወገኖች ሆይ፣ መላው የእግዚአብሔር ሕዝብ እንዲህ ያለ የአማልክትን አምላክ፣ የጌቶችን ጌታ ማምለኩን
አቁሞ፣ ከጆሮ ጉትቻ፣ ከእጅ ቀለበቶች ለራሱ የሚሆን ሕይወት አልባ አምላክ ሠራ፡፡ ሕይወት አልባውን አምላክ መቅረጽ ብቻም
ሳይሆን ማምለክ አማረው፡፡ ሕዝቡ ተሰብስቦ ለጣኦት አምልኮ የጣዖት አጀንዳ ውይይት ጀመረ፡፡
ወገኖች ሆይ፣ በሕዝበ ውሳኔው ለጣኦት አምልኮ ውሳኔ ተሰጠ፡፡ ድምጽ ተቆጠረ፣ ሕዝቡ አሸነፈ፡፡ የሕዝቡ
ጥያቄ ለመሪው ቀረበ – መሪውም ተቀበለ፡፡ ብረት ተቀጥቅጦ፣ አምላክ ተፈጠረ፡፡ ለተፈጠረው አምላክ ስግደት ተጀመረ፡፡
ታውቃላችሁ፣ መጽሐፍ ቅዱሳችን ይህንን እብደት፣ ይህንንም ውርደት ከ‹‹ስድ›› አመራር ውጭ
ሌላ ቃላት አልመረጠም፡፡
ታውቃላችሁ፣ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ስድ የሚለቅቁ ስድ መሪዎች አሉ፡፡ የእግዚአብሔር ስም
በአሕዛብ መካከል እንዲሰደብ በር የሚከፍቱ በርካታ ስድ መሪዎች አሉ፡፡ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ከእውነት የሚያወጡ፣ ከጽድቅ
የሚያስቱ ጣዖት የሚሠሩ ብዙ መሪዎች አሉ፡፡ ጌታን የሚያስረሱ ሐውልት የሚቀርጹ፣ ቀርጸው የሚያሰግዱ ብዙ መሪዎች አሉ፡፡
ታውቃላችሁ፣ ከመስመራቸው ወጥተው፣ ድንበራቸውን ለቅቀው፣ ዓላማቸውን ረስተው፣ አቅጣጫቸውን
ስተው፣ የሚመሩትን ሕዝብ አቅጣጫ የሚያስቱ፣ ስድ መሪዎች አሉ፡፡
ታውቃላችሁ፣ ጌታን አሳዝኖ ሕዝብን ለማስደሰት ጎንበስ ቀና የሚሉ ብዙ መሪዎች አሉ፡፡ በሰው
ለመወደድ፣ በሕዝብ ለመመረጥ መከራ የሚያዩ ብዙ መሪዎች አሉ፡፡ ሕዝብን ለማስደሰት ከመንገድ የሚወጡ፣ በዓመጻ ገበያ ጽድቅ በኃጢአት፣
እምነትን በክህደት እውነትን በውሸት የሚለውጡ ብዙ መሪዎች አሉ፡፡
ታውቃላችሁ፣ ሕዝብን ለማስደሰት ጌታን የሚያሳዝኑ ብዙ መሪዎች አሉ! ሄሮድስን አስቡ! (የሐዋ
12)። ንጉሡ
ሄሮድስ የጌታን ሐዋርያት አንዳንዶቹን አስሮ፣ ሌሎቹን ደብድቦ፣ ያዕቆብን ግን በሰይፍ ገደለ፡፡ ይህን በማድረጉ፣ አይሁድ ደስ ተሰኙ፡፡
ይህን ያየው ንጉሥ ለፋሲካው ዶሮ ጴጥሮስን አሰረው፡፡ ጌታ ግን ወኅኒ ቤቱን ከፍቶ የፋሲካውን ዶሮ ጴጥሮስን አዳነው!
ወገኖች ሆይ፣ ስድ መሪዎች ‹‹እግዚአብሔር ምን ይላል?››
ሳይሆን ‹‹ሕዝቡ ምን ይላል?›› በማለት ይጨነቃሉ፡፡ ስድ መሪዎች ‹‹እግዚአብሔር ምን
ይወዳል?››
ሳይሆን ‹‹ሕዝቡ ምን ይወዳል?›› በማለት ይጨነቃሉ፡፡ ስድ መሪዎች ከእግዚአብሔር ይልቅ
ሕዝቡን ያስቀድማሉ፡፡ ከእግዚአብሔር ይልቅ ሕዝቡን ይፈራሉ፡፡ ከእግዚአብሔር ይልቅ ሕዝቡን ይመርጣሉ፡፡
ወገኖች፣ ስድ መሪዎች በስድ አመራራቸው የእግዚአብሔርን ሕዝብ መረን ይለቅቃሉ፡፡ ስድ መሪዎች የእግዚአብሔርን
ሕዝብ መረን በመልቀቅ ከእውነት ያስታሉ፡፡ ከእውነት አስተው የእግዚአብሔርን ቁጣ ያቀጣጥላሉ፡፡
ታውቃላችሁ፣ ጃን ሲ ማክሴል ‹‹ለማናቸውም ነገሮች ትንሳኤና ውድቀት ምክንያቱ አመራር ነው››
ይላል፡፡ እውነቱን ነው፡፡ መልካም አመራር ሲኖር መልካም ውጤት ይኖራል፣ አመራር ሲከፋ ውጤቱ ይከፋል፡፡ ስለሆነም፣ እግዚአብሔርን
የሚፈሩ፣ ሕዝቡን መረን የማይለቅቁ መሪዎች እንዲነሱ ወደ ጌታ እንጩኽ!
--------------------------------
(ትምህርቱ
ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክና ሼር
ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)
No comments:
Post a Comment