Tuesday, December 9, 2014

የጴንጠቆስጤነት አቡጊዳ(#9) –ያለንን ማካፈል!

ዲቮሽን ቁ.89/07     ሰኞ፣ ሕዳር 29/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)

የጴንጠቆስጤነት አቡጊዳ(#9) –ያለንን ማካፈል!

ያመኑትም ሁሉ አብረው ነበሩ፤ ያላቸውንም ሁሉ አንድነት አደረጉ። መሬታቸውንና ጥሪታቸውንም እየሸጡ፥ ማንኛውም እንደሚፈልግ ለሁሉ ያካፍሉት ነበር (የሐዋ 2፡44-45)።

ለጴንጠቆስጤነት ማንነት ሌላው መገለጫ ያለንን ለሌሎች ማካፈል ነው፡፡ ጴንጠቆስጤዎቹ ያላቸውን ለሌሎች ከማካፈላቸው በፊት ሁለት መሠረታዊ ነገር ነበራቸው፡፡ (1ኛ) አማኞች ከሁሉ አስቀድሞ አብረው ነበሩ፡፡ ይህ ማለት ቤተሰባዊ ኅብረት (fellowship) ነበራቸው ማለት ነው፡፡ (2ኛ) አማኞች ያላቸውን አንድ ላይ አደረጉ፡፡ ይህም ልክ እንደ መጀመሪያው ነጥብ ቤተሰባዊ መንፈስን የጠበቀ የንብረት አንድነት ነው፡፡

ታውቃላችሁ፣ ልባዊ አብሮነት ከሌለ ቤተሰባዊ ኅብረት አይመጣም፡፡ ቤተሰባዊ ኅብረት ካልመጣ ደግሞ ንብረታችንን ለእያንዳንዱ እንደሚያስፈልግ ሁሉ ማካፈል አይቻልም፡፡

ታውቃላችሁ፣ ጤናማ መስጠት የሚመነጨው ከጤናማ ኅብረት ነው፡፡ ህብረታችን ጤና ካጣ፣ መስጠታችን ጤና ያጣል፡፡ጤናማ ህብረት ማለት ልክ እንደ ቤተሰባችን ማለት ነው፡፡ የቤተሰብ አባላት አንዳቸው ለሌላቸው ፍላጎት ይቆረቆራሉ፡፡ የቤተሰብ አባላት አንዳቸው ከሌላቸው ጋር በእውነት ይዋደዳሉ፣ ይተሳሰባሉ፣ ይረዳዳሉ፣ ይደጋገፋሉ! የቤተሰብ አባላት ንብረታቸውን የጋራቸው አድርገው እንጂ፣ የግላቸው ብቻ አድርገው አያስቡም፡፡

ወገኖች ሆይ፣ በእጃችን ያለው ንብረት የእኛ ሳይሆን የጌታ ነው፡፡ ምዕመናን ንብረታቸው የጌታ መሆኑን ያውቃሉ፡፡ ስለዚህ ያላቸውን ለሌሎች መስጠት ቀላል ይሆንላቸዋል፡፡ እውተኛ አማኞች ያልሆኑ ደግሞ፣ ንብረታቸው የራሳቸው ብቻ አድርገው ስለሚቆጥሩ መስጠት የተራራ ያህል ዳገት ይሆንባቸዋል፡፡

ወገኖች ሆይ፣ በሀገራችን ያለው የአንጋፋዎቹ የወንጌል አማኞች ልማድ በመስጠት አካባቢ ትልቅ ችግር አለበት፡፡ በቤተክርስቲያን ውስጥ ብዙ ሰዎች እርስ በእርሳቸው ከልብ ሲረዳዱ እምብዛም አይታይም፡፡ አስራታቸውን እንኳ በታማኝነት ለመስጠት የሚቸገሩ ‹‹አማኝ ነን›› ባዮች ቁጥራቸው ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ወጣቶቹ አብያተክርስቲያናት፣ በመስጠት አገልግሎት አካባቢ መንፈሳዊ አይናቸው የተገለጠ ነው፡፡ የሚከተሏቸውም አባላት ስለመስጠት የተሻለ መረዳት አላቸው፡፡

ታውቃላችሁ፣ አንጋፋዎቹ የወንጌል አማኞች ወጣቶቹን አብያተክርስቲያናት በየጊዜው ሲነቅፉ ይደመጣል፡፡ የነቀፋቸው መሠረትም፣ የአባሎቻቸውን ገንዘብ ይዘርፋሉ የሚል ነው፡፡ ብዙዎች እንዲህ በማለት ይቃወሙ እንጂ፣ በወንጌላዊያን አብያተክርስቲያናት ውስጥ ሙሉ ጊዜያቸውን ሰጥተው የሚያገለግሉ አገልጋዮችና ቤተሰቦቻቸው ሲቸገሩ፣ ብዙ ጊዜ እንደሚታየው፣ በርካቶች ድጋፍ ማድረግ ቀርቶ ትኩረት አይሰጡም፡፡ ይህ እውነታ እየታወቀ፣ የራሳቸውን ችግር በራሳቸው መነጽር ማየት ትተው የሌሎችን ይነቅፋሉ፡፡


ወገኖች ሆይ፣ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ይላል፣ ‹‹ነገር ግን የዚህ ዓለም ገንዘብ ያለው፥ ወንድሙም የሚያስፈልገው ሲያጣ አይቶ ያልራራለት ማንም ቢሆን፥ የእግዚአብሔር ፍቅር በእርሱ እንዴት ይኖራል?›› (1ዮሐ 3፡17)

No comments:

Post a Comment