ዲቮሽን ቁ.88/07 እሁድ፥ ሕዳር 28/07
ዓ/ም
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)
የጴንጠቆስጤነት አቡጊዳ (#8) – ግርማ ሞገስ
ነገር ግን በሰው ሁሉ ፍርሃት ሆነ፥ በሐዋርያትም እጅ ብዙ ድንቅና ምልክት ተደረገ (የሐዋ 2፡43)
መንፈስ ቅዱስ በቅዱስን መካከል በሙላት በሚሰራበት ጊዜ፥ በአማኞች እጅ ብዙ ድንቆችና ምልክቶች ይደረጋሉ፡፡ ከድንቆቹም መካከል ሽባዎች ይተረተራሉ፥ ዓይነ ስውራን ያያሉ፥ ደንቆሮዎች ይሰማሉ፥ ዲዳዎች ይናገራሉ፥ አእምሮአቸውን የታመሙ ነጻ ይወጣሉ፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ፥ በሕዝብ ላይ የእግዚአብሔር ፍርሃት ይወድቃል፡፡ ለአማኞችም ግርማ ሞገስ ያመጣል፡፡
መንፈስ ቅዱስ በሙላት በሚሰራበት ጊዜ፥ በዊልቸር የሚሄድ ከዊልቸር ሲነሳ፥ በስትሬቸር የመጣ ከስትሬቸር ሲነሳ፥ በሰንሰለት የታሰረው ተፈትቶ ሲነሳ፥ ጎባጣው ሲቀና፥ ሰባራው ሲጠገን፥ በሕዝብ ዘንድ ታላቅ ፍርሃት ይወድቃል፡፡ ለአማኞችም ግርማ ሞገስ ያመጣል፡፡
ወገኖች ሆይ፥ መንፈስ ቅዱስ በአማኞች መካከል በሙላት መስራት ሲጀምር፥ ካንሰር፥ ስኳር፥ ትውመር፥ ጎይተር፥ ኤችአይቪ/ኤድስ ወዘተ ይጠፋሉ፡፡ ይህ ሲሆን የእግዚአብሔር ፍርሃት በሕዝብ ላይ ይወድቃል፡፡ ለአማኞችም ግርማ ሞገስ ያመጣል፡፡
መንፈስ ቅዱስ በአማኞች መካከል በሙላት መስራት ሲጀምር፥ አስማት፥ መተት፥ ሟርት፥ ድግምት፥ እና ማናቸውም ዓይነት እጋንንታዊና የጥንቆላ ስራዎች ይፈራርሳሉ፡፡ አጋንንት እየጮኹ ከሰዎች ሲለቅቁ፥ የእግዚአብሔር ፍርሃት በሕዝብ ላይ ይወድቃል፡፡ ለአማኞችም ግርማ ሞገስ ያመጣል፡፡
ወገኖች ሆይ፥ አማኞች በህብረት ጌታን ሲያምልኩ፥ በፍቅር፥ በሰላም በመንፈስ ቢመላለሱ፥ እንጀራ አብረው ቢቆርሱ፥ አብረው ቢጸልዩ ታላቅ የመንፈስ ቅዱስ መንቀሳቀስ ይሆናል፡፡ ይህ መንቀሳቀስ ሲሆን ደግሞ፥ በሰዎች ዘንድ የእግዚአብሔር ፍርሃት ያመጣል፡፡ ለአማኞችም ግርማ ሞገስ ያመጣል፡፡
ወገኖች ሆይ፥ ክርስትና በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ሀይል እንጂ፥ ለአማኞችም ግርማ ሞገስ እንጂ፥ የቃላት ጉዳይ አይደለም፡፡ ክርስትና ሕይወት እንጂ፥ ቃላት ማሳመሪያ፥ ቃላት ማዳመቂያ፥ ቃላት መሰንጠቂያ አይደለም፡፡ ክርስትና የቃላት መከራከሪያ፥ መነቋቆሪያ፥ መደነቋቆሪያ፥ መደነጋገሪያ፥ መደነባበሪያ፥ መደባበሪያና መበሻሸቂያ አይደለም፡፡
No comments:
Post a Comment